የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኞች እሁድ ሥራ እንድንገባ መደረጋችን መብታችንን የሚጥስ ነው አሉ

0
842

አቢሲኒያ ባንክ የዕረፍት ቀን በሆነው እሁድ ሠራተኞቹ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ተከትሎ የባንኩ ሠራተኞች መብታችን እየተጣሰ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ባንኩ መብታችንን ጥሷል ያሉት ሠራተኞች፣ እስካሁን ከሦስት ሳምንታት በላይ የዕረፍት ቀናቸውን እሁድ በሥራ እንዲያሳልፉ መደረጋቸውን ጠቁመዋል። ባንኩ ሠራተኞቹን በዕረፍት ቀናቸው ማለትም እሁድ በሥራ ገበታ ላይ እንዲገኙ ትዕዛዝ ሲሰጥ ሠራተኞች ተለዋጭ የዕረፍት ቀን እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያቀረቡ የባንኩ ሠራተኞች እንደገለጹት ከሆነ፣ ባንኩ የቀረበለትን የተለዋጭ የዕረፍት ቀን ጥያቄ ምንም ምላሽ ሳይሰጥበት ከእሁድ እስከ እሁድ እያሠራን ነው ብለዋል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ለሦስት ሳምንታት ከእሁድ እስከ እሁድ በሥራ ላይ የነበሩ የባንኩ ሠራተኞች፣ ያለ ፈቃዳቸው እሁድ በሥራ ላይ እንዲገኙ ከመደረጋቸው በተጨማሪ፣ በዕረፍት ቀናቸው የሠሩበት አበል እንዲታሰብላቸው ለሚሠሩበት ቅርንጫፍ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ሠራተኞቹን ከእሁድ እስከ እሁድ በሥራ ላይ እንዲገኙ ያደረጉ የባንኩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች፣ “የባንኩን ጥቅም እንጂ የሠራተኞችን መብት እያከበሩ አይደለም” ያሉት ሠራተኞቹ፣ “በሕግ የተደነገገ የአሠሪ እና ሠራተኛ ሕግን በጣሰ ሁኔታ እያሠሩንም ቢሆን፣ የዕረፍት ቀናችንን እንጠቀማለን ብለው እሁድ በሥራ ገበታ ላይ ያልተገኙ ሠራተኞች ከሥራ የመባረረ ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል። ስለዚህ ሥራ ከማጣት ዕረፍት ማጣት ይሻላል ብለን እየሠራን ነው” ብለዋል።

ባንኩ ከዚህ በፊት ሠራተኞቹን በመደበኛ የሥራ ስዓት የሚያሠራ ሲሆን፣ አሁን ላይ ሠራተኞቹ ከእሁድ እስከ እሁድ እንዲሠሩ እያደረገ ያለው፣ የፋይናንስ ተቋማት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የአገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቻቸውን ዝርዝር መረጃ አሟልተው እንዲመዘግቡ እና የደንበኞቻቸውን መረጃ እንዲያጣሩና እንዲያደራጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ለባንኮች ባስተላለፉው መመሪያ፣ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ በተፈጠረው የሥራ ጫና ነው ተብሏል።

ብሔራዊ ባንክ ያስተላለፈው መመሪያ ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ የማጣራትና የማደረጃት ሥራቸውን በስድስት ወራት ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ጊዜ ተስጥቷቸዋል ተብሏል። መመሪያውን ተከትሎ ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ እያደራጁ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ባንኮች አረጋግጣለች።

አዲስ ማለዳ ከባንኩ ሠራተኞች የቀረበላትን ቅሬታ ይዛ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባንኩ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጧት ጥያቄ አቅርባ ለባንኩ የሰው ሀብት አስተዳደር ድብዳቤ እንድታስገባ በተሰጣት አቅጣጫ መሠረት ኅዳር 16/2014 ድብዳቤ ብታስገባም፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ስዓት ድረስ ምላሽ አላገኘችም።

መመሪያው የተላለፈው ለኹሉም ባንኮች መሆኑን ተከትሎ ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ በማደራጀት ላይ ቢሆኑም፣ እስካሁን ከአቢሲኒያ ባንክ ውጭ ሠራተኞቹን በዕረፍት ቀን ሥራ ላይ እንዲገኙ ያደረገ ባንክ የለም።
የአሠሪና ሠራተኛን መብትና ግዴታ የሚደነግግው የአሠሪና ሠራተኛ ዐዋጅ ቁጥር 1156/2011 በሳምንት የዕረፍት ቀን የሚሠራ የትርፍ ስዓት ሥራ፣ ለመደበኛ የሥራ ስዓት ከሚከፈለው ደሞዝ በኹለት ተባዝቶ እንደሚከፈለው ተደንግጓል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here