ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ መልካም ግንኙነት ያላቸው ጎረቤት አገሮች ከመሆናቸው በላይ፣ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎቻቸው በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ታሪካቸው ያስረዳል።
በኹለቱ አገራት መካከል ለዘመናት በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተው ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ችግሮች እየገጠሙት እንደሚገኝ ይገለጻል። በተለይም ሱዳን መረጋጋት ተስኗት በሽግግር መንግሥት መመራት ከጀመረች በኋላ፣ ሱዳንን የሚመራው የሽግግር መንግሥት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በድንብር ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ሠላማዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻክር እያደረገ ነው በሚል ከኢትዮጵያ በኩል ክስ ይቀርበበታል።
ሱዳን፣ ኢትዮጵያ ከህወሓት ጋር ጦርነት በመገጠመችበት ማግሥት ኅዳር/2013 የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ መግባቷን ተከትሎ የያዘችውን መሬት ለቃ እንድትወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቢወተውትም እሰካሁን ድረስ ለቃ አልወጣችም።
ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ በድንብር አካባቢ ወታደሮቼ ላይ ጥቃት ፈጽሞብኛል በማለት፣ በድንበር አካባቢ ቅኝት እያደረገች ነው። ኢትዮጵያ በበኩሏ ሠርጎ ገብ ታጣቂዎች ላይ አንጂ ሱዳን ወታደር ላይ ያደረስኩት ጥቃት የለም ብላለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ ሠርጎ ለመግባት የሚሞክሩ ታጣቂዎች በሱዳን በኩል በተደጋጋሚ በመምጣታቸው፣ ሱዳን ኢትዮጵያን ማጥቃት ለሚፈልጉ ቡድኖች እንደ መሸጋጋሪያ ደልድይ እያገለገለች መሆኑን ባለመያዎች ይገልጻሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በመልካም ጉርብትና እና የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ለዘመናት የዘለቀ ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮቸ መሆናቸውን ከኹለቱ አገራት የጋራ ታሪክ መረዳት ይቻላል። ለዘመናት በመልካም ግንኙነት የዘለቀው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መጥቷል።
የኹለቱ አገራት ግንኙነት ከመልካም ጉርብትና ወደ እርስ በእርስ መካሰስ የተቀየረው በተለይ ከአንድ ዓመት በፊት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሕወሓት ጋር ጦርነት በገጠመችብት ጊዜ ነበር።
ሕወሓት መቀመጫውን በትግራይ ክልል ባደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24/2013 ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተጠቅማ ሱዳን ኢትዮጵያን ላይ ትንኮሳ እያደረሰች መሆኑን በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ ከሕወሓት ጋር ጦርነት በገጠመችበት ማግስት ከዓመት በፊት በህዳር ወር የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንብር ጥሶ በመግባት በድንበር አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ማፈናቀሉ የሚታወስ ነው። ሱዳን በወቅቱ የኢትዮጵን ድንበር ጥሳ በመግባቷ በኹለቱ አገራት የነበረው መልካም ግንኙነት እንዲሻክር ማድረጉን ከመንግሥት እስከ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይሰማል።
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻክር የሚያደርጉ ተግባራትን እየፈጸመች መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህም እንደ ማሳያነት የሚነሳው ሱዳን ከሕዳሴው ግድብ ድርድር ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ የምታሳየውን ተገቢ ያልሆነ ተቃርኖን በማንሳት ነው።
በኹለቱ አገራት መካከል በሕዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ከሚታዩ አለመግባበቶች አሁን ላይ በድንበር አካባቢ እስከሚታዩት ችግሮች ድረስ አያሌ ጉዳዮች እልባት ያላገኙ ናቸው። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ከተቋረጠ ወራቶች ያስቆጠረ ሲሆን፣ ሱዳን የህዳሴው ግድብ ድርድርን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ አንዱ ክልል የሆነው ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ቀደም ሲል የሱዳን አካል ነበር በማለት ያነሳችው ሀሳብ ሱዳን ችግሮችን በመግባበት ከመፍታት ይልቅ በማባባስ ላይ ተጠምዳለች የሚሉ ትችቶች ሲቀርቡ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ለሱዳን እና ለኢትዮጵያ ግንኙነት መሻከር እንደ ዋና ምንክያት የሚነሱት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የድንብር ጉዳዮች ናቸው። በኹለቱ አገራት መካከል በኹለቱ ጉዳዮች ላይ እየተባባሰ የመጣው ውጥረት ዓለም አቀፉን የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ካሳሰቡ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።
ከሰሞኑ ደግሞ ይህንኑ ችግር የሚያባብሱ ጉዳዮች የተከሰቱ ሲሆን፣ በኹለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ሱዳን ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ጦር ጥቃት ድርሶባቸዋል በማለት ክስ አቅርባለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ የኢትዮጵያ ጦር በሱዳን ላይ ያደረሰው ጥቃት የለም ብላለች።
ሱዳን ደርሶብኛል ያለችውን ጥቃት ምክንያት በማድረግ ጦሯን ወደ ድንበር የማስጠጋት እና አካባቢውን የመቃኘት አዝማሚያ እያሳየች ነው ተብሏል። በኹለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በሻከረበት በዚህ ጊዜ ሱዳን ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን በግዛቷ ሲንቀሳቀሱ እና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት እንደ ድልድይ ሲጠቀሟት መታየቱ ሌላ ትኩሳት ሆኗል።
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ችግር በተወጠረችበት በአሁኑ ወቅት ሱዳን በድንበር አካባቢ ከምታደርገው ትንኮሳ በተጨማሪ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው ለመግባት የሚሞክሩ ታጣቂዎች መደበቂያ መሆኗ ደግሞ ከሰሞኑ የተባባሰ ጉዳይ ሆኗል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወሓት ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ የክልሉ ወረዳዎች የተለያዩ “ተላላኪዎቹን” በማሠማራት ጸጥታውን ለማደፍረስ ሙከራ ማድረጉን የክልሉ መንግሥት ገልጿል። ከሱዳን ሰርገው የገቡ ታጣቂዎች በቅርቡ በክልሉ ድንበር አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በጋራ በወሰዱት እርምጃ መደምሰሳቸውንና የተማረኩት ደግሞ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ይዘው መገኘታቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።
ከሰሞኑ ሱዳን እንደ ድልድይ ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማጥቃት እየሞከሩ የሚገኙ ሰርጎ ገቦች ሁኔታ ሱዳን ለጸረ-ሠላም ኃይሎቹ ከምትሰጠው ሽፋንና ድጋፍ ባሻገር የአገሪቱ ወታደሮች ጭምር ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመግባት በጦርነቱ መሳተፋቸውን ከተማረኩ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት እትሟ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሱዳን አዋሳኝ አካባቢ ከሚኖሩ ዜጎች ከሱዳን ሰርገው የሚገቡ ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን መዘገቧ የሚታወስ ነው። በክልሉ ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ያለውን የጸረ-ሠላም እንቅስቃሴ ለመመከትና እርምጃ ለመውሰድ የጸጥታ አካላት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ላይ ተደርቦ የመጣው የሱዳን ትንኮሳ ለኢትዮጵያም ይሁን ለቀጠናው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ እና በሱዳን ግንኙነት ላይ በሚሰሩ ጥናቶች ተሳትፎ ያላቸው በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዓቀፍ ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አለሙ አስፋው ጉዳዩ ቀላል የማይባልና ትኩረት የሚሻ መሆኑን ይገልጻሉ።
የኢትዮ ሱዳንን ግንኙነት በቅርበት የሚከታተሉት አለሙ አሰፋው(ረ/ፕ) ኹለቱን አገራት በኢኮኖሚና በሕዝብ ለሕዝብ ያላቸው ቁርኝት ለምስራቅ አፍሪካ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ተስፋ የተጣለበት እንደነበር ያስታወሳሉ። ይሁን እንጂ፣ አሁን ላይ በኹለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ችግር እንደገጠመው ይገልጻሉ።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ከህዳሴው ግድብ ድርድር አስከ ድንበር ውዝግብ ያለው ጉዳይ አሁን ላይ በሱዳን በኩል ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ማስገባት ለሚፈልጉ አካላት በር የከፈተ ጉዳይ መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ እልባት ያላገኘ የውሃ እና የድንበር ውዝግብ ጉዳይ ቢኖሯቸውም፣ ውዝግቡ በተለያዩ ጊዜያት ከፍ ዝቅ እያለ ከመቀጠል ውጭ እና አልፎ አልፎ ከሚታዩ በድንበር አካባቢ ከሚኖሩ የአርሶ አደሮች ግጭት የዘለለ አለመሆኑን አለሙ ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጂ፣ አሁን ላይ የሚታየው የድንበር ይገባኛል እና የውሃ ጉዳይ በድንበር አካባቢ ከሚኖሩ የኹለቱ አገራት አርሶ አደሮች አልፎ አገር ለአገር መሆኑን ይገልጻሉ። ችግሩ ከደንበር አካባቢ ከሚገኙ አርሶ አደሮች በላይ ከፍ ማለቱ እና ኢትዮጵያ አሁን በገጠማት ችግር ላይ ተደርቦ የመጣ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ተገንዝቦ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
ሌላኛው ስማቸው አንዳይጠቀስ ያሳሰቡ የምስራቅ አፍሪካ ጅኦፖለቲካ ተንታኝ በጉዳዩ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሱዳን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያሳየች ያለችው አዝማሚያ ለቀጠናው ስጋት የሚሆን መሆኑን ይገልጻሉ። በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው መልካም ግንኙነት ወደ ውዝግብ እንዲመራ ያደረገው የሱዳን መንግሥት አለመረጋጋት ነው ይላሉ።
ሱዳን የተረጋጋ መንግሥት መመስረት አለመቻሏን ተከትሎ አሁን ላይ የምትመራው በወታደራዊ እና በሲቪል ጥምር የሽግግር መንግሥት ሲሆን፣ በቅርቡ የሱዳን ወታደራዊ መሪው ሌ/ጄ አብዱል ፈታ አል ቡርሃን የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ማስወገዳቸው የሚታወስ ነው።
በጦር መሪው አል ቡርሃን የተደረገው መፈንቅለ መንግሥት አሁን ላይ ወደ ነበረበት የሽግግር መንግስት የተመለሰ ሲሆን፣ ድጋሚ በተመሰረተው የሽግግር መንግሥት የሱዳን ዜጎች ተቃውሞ እያሰሙ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ተንታኙ እንደሚሉት የሱዳን የሽግግር መንግሥት በየጊዜው በዜጎቹ የሚደርስበትን ትችት ለማርገብ እና የራሱን ፍላጎት ለሟሟላት የኢትዮ ሱዳንን የድንበር ጉዳይ በማራገብ አጀንጃ ለመፍጠር እንደሚጠቀምበት ይገልጻሉ።
በዚህም አሁን ላይ በሱዳን በኩል የሚታየው ዝንባሌ የሱዳንን ሕዝብ ፍላጎት የማይወክል መሆኑን ተንታኙ ይገልጻሉ። የኹለቱ አገራት ግንኙነት ከዚህ በፊት በነበሩት የሱዳን መንግሥታት መልካም የሚባል እና በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ መሰረት ያደረገ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይነስ መምህሩ አለሙ በበኩላቸው፣ አሁን ያለው የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን ከማጠናከር ይልቅ በወታደራዊ ትንኮሳዎች እና ለጣልቃ ገቦች በር በመክፈት ላይ ተጠምዷል ይላሉ። ይህም የሚያሳየው የሱዳንን ህዝብ ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚጣጣሩ ቡድኖች አላማ መጠቀሚያ መሆኑን ይጠቁሟሉ።
“ከአልበሽር በኋላ በሱዳን መንግሥት አለ ማለት አይቻልም” የሚሉት አለሙ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ በሱዳን ህዝብ በኩል ያለው ስሜት ሰላማዊ ወዳጅነት ነው ይላሉ። ይሁን እንጅ ጉዳዩ በኢትዮጵያ በኩል ትልቅ ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።
የኢትዮ ሱዳን ድንብር ያልተቋጨ የቤት ሥራ
ሱዳን እና ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየ እልባት ያላገኘ የድንብር የይገባኛል ጥያቄ ያላቸው ሲሆን፣ የድንበር መስመር ለማስመር የተጀመሩ ሥራዎች እስካሁን እውን መሆን አልቻሉም። ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚጋሩት ድንበር ርዝመት 750 ኪሎ ሜትር መሆኑ ይነገራል፣ ነገር ግን ይህ ድንበር ግለጽ ወሰን አልተወሰነለትም። ኢትዮጵያ እና ሱዳን እስካሁን ድረስ ተግባብተውበት የቆዩት በ1895 ባደረጉት የድንበር ስምምነት መሆኑ ይገለጻል። ሌላኛው ስምምነት 1965 የተደረገ ሲሆን፣ በወቅቱ በተደረገው ስምምነት ኹለቱ አገራት ያላቸውን የድንበር ውዝግብ በሕጋዊ መንገድ ለማስመር ቢግባቡም እስከዛሬ ድረስ ሳይፈፀም ቆይቷል።
የኹለቱ አገራት የድንበር ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት የጋራ የኢትዮ-ሱዳን የድንብር ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን፣ ሱዳን የዛሬ ዓመት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት የተወሰደብኝን መሬት አስመልሻለሁ ማለቷን ተከትሎ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽን ኹለቱ አገራት 1965 ለድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን መግለጹ የሚታወስ ነው። በስምምነቱ መሰረት አገራቱ በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ እስከሚያስቀምጡ ድረስ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ያስገድዳል።
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ በሰላማዊ ውይይት ላይ የተመሰረተ እልባት እንደሚያስፈልገው ይገለጻል። ጉዳዩ እልባት ካላገኘ ከኹለቱ አገራት ያለፈ ችግር እንዳለም ይነገራል። የባህርዳር ዩኒቨርሰረቲ መምህሩ አለሙ እንደሚሉት፣ በኹለቱ አገራት መካከል ያለው የድንበር ግንኙነት በሕዝብ ለሕዝብ እና በኢኮኖሚ የተሳሰረ በመሆኑ ችግሩ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ይጠቁማሉ።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ በሱዳን በኩል የሚታየው፣ በኃይል ደንበር ጥሶ የመግባት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ በኢትዮጵያ አካባቢውን በልዩ ትኩረት የመከታተል እና በድንበር አካባቢ የሚገኙ አካባቢዎችን ደህንነት በጥብቅ ማጠናከር ይገባል ይላሉ። ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ እና በወቅቱ እልባት የማይሰጠው ከሆነ አገርን እስከመበተን ሊደርስ እንደሚችል የሚገልጹት አለሙ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት ከሚሰጣቸው የውስጥ ጉዳዮች እኩል ትኩረት ስጥቶ በፖለቲዊ እና ድፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ከመስራት እስከ ወታደራዊ ዝግጅት የሚደርስ ሥራዎችን በአንክሮት መስራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።
የምስራቅ አፍሪካ ተንታኙ በበኩላቸው፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ እልባት ማግኘት በቀጠናው ሰላም ላይ ያለው ሚና ጉልህ መሆኑን ይገልጻሉ። ይሁን እንጅ አሁን የሚታየው ሁኔታ በጅምሩ ካልተቀጨ በቀጠናው ላይ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካላት አራጋቢነት ተጨምሮ ወዳልተፈለገ ግጭት ሊመራ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ በሱዳን ጦር እና ሱዳንን ከለላ አድርገው ሰርገው የሚገቡ የታጠቁ ኃይሎች የሚደርስባትን ትንኮሳ በጥብቅ ክትትል ምላሽ መስጠት እንዳለባት አለሙ ይገልጻሉ። በሱዳን በኩል የሚታየው አሁናዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚያዋስኗት በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎችን በፖለቲካ እና በወታደራዊ ደህንነት በጥብቅ ማጠናከር አለባት ብለዋል።
ከሰሞኑ በሱዳን በኩል በተሰማው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ፣ ኹለቱ አገራት በታሪክ በድንበር፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩች የዘመናት ትስስር ያላቸው አገሮች መሆናቸውን በመጥቀስ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የአገራቱን ግንኙነት ከግምት በማስገባት በሱዳን ተወሮ የሚገኘውን መሬት ጉዳይ የዘመናት የታሪክና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ከግምት ያስገባ መፍትሄ ለማፈላለግ ጥረት እያደረገች መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
ሱዳን የኢትዮጵያ የጀርባ ትኩሳት
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ግንኙነት መሻከር ላይ በዋነነት የሚነሱት የታለቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የድንብር ጉዳይ ሲሆን፣ ኹለቱም ጉዳዮች አስካሁን ውሳኔ አላገኙም። ሱዳን በእነዚህ ጉዳዮች በህዳሴው ድርድር ላይ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ተቃራኒ ሀሳብ በማንጸበረቅ እና በድንበር ጉዳይ ደግሞ የጋራ ስምምነቶችን በመጣስ ድንበር አልፋ ከመግባት ኢትዮጵያን ማጥቃት የሚፈልጉ ታጣቂዎችን ሽፋን እስከመስጠት የደረሰ መሆኑን መንግሥት ይገልጻል።
አሁን ያለው የሱዳን መንግሥት የሚያራምዳቸው ሀሳቦች የኢትዮጵያ የሱዳንን ህዝብ እንደማይወክሉ እና ከጀርባ ሌላ አካል መኖሩን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይሰማል። ከሰሞኑ በድንበር አካባቢ እየሆነ ያለው ጉዳይ ደግሞ ሱዳን ለአሸባሪ ድርጅቶች ሽፋን እየሰጠች በግዛቷ እየተንቀሳቀሱ እድል መስጠቷ ከጀርባዋ ሌላ ተደራቢ ቡድኖች እንዳሉ አመላካች መሆኑ ይገለጻል።
ኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻውን ማካሄድ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ከሱዳን በኩል ሰርገው የሚገቡ፣ “የሽብር ቡድኑ የጥፋት ኃይሎች” ጥቃት ለማድረግ ሲሞክሩ መቆየታቸውን መንግሥት ከሰሞኑ ባወጣው መግጫ ጠቁሟል።
በሱዳን በኩል ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚሞክሩ ከሱዳን ጅርባ ሌላ ቡድን እንዳለ የሚገልጹት የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህሩ፣ ከሱዳን ጅርባ ካሉ ቡድኖች መካከል ሕወሓት አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ። መምህሩ እንደሚሉት ሕወሓት ሱዳንን መሽጋገሪያ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት በተደጋጋሚ ሙከራ ከማድረጉ በስተጀርባ የውጭ ኃይሎች ድጋፍ እንደሚኖር ይገልጻሉ።
በመሆኑም በኢትዮጵያ እና በሱዳን በኩል የሚታየው አሁናዊ ችግር ተደራርቦ የመጣ መሆኑን በመገንዘብ ከዲፕሎማሲ እስከ ጠንካራ ወታደራዊ ዝግጅት የሚሻ መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።
የኹለቱ አገራት የድንበር ውዝግብ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚፈልግ መሆኑን የአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ጥናት አንስቲትዩት አካል የሆነ ፒስ ኤንድ ሴኩሪቲ ካውንስል ሪፖርት የኹለቱን አገራት የድንበር ውዝግብ በሚመለከት ባስነበበው ጽሑፍ ይጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014



