በሱማሌ ክልል እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ ማዕድንና ነዳጅ ኩባንያዎች የተሰበሰበ 50 ሚሊዮን ብር ለሱማሌ ክልል መበርከቱ ተሰማ።
የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በሱማሌ ክልል እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የማዕድንና ነዳጅ ኩባንያዎች የተሰበሰበ 50 ሚሊዮን ብር ለሱማሌ ክልል አበርክተናል ሲሉ መናገራቸው ተነግሯል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ገንዘቡ እንደ ትምህርት ቤት እና ጤና ተቋማት ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የሚውል መሆኑንም አመላክተዋል።
ማዕድን የአገርና የሕዝብ ሀብት ነው ያሉት ታከለ፣ ዋናው ተጠቃሚ መሆን ያለበትም ሕዝብ ነው ሲሉ በጽሑፋቸው አስፍረዋል።
ታከለ ኡማ ማዕድን የሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ከማዕድንና ነዳጅ ሀብቱ በሥራ ዕድልም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ የተመራ ልዑክ ጂግጂጋ የገባ ሲሆን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድና ካቢኔያቸው አቀባበል ማድረጋቸው ተዘግቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014


