ባለፉት አራት ወራት፣ ማለትም ከሐምሌ1/2013 እስከ ጥቅምት 30/2014 ድረስ ባለው ጊዜ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 338.5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ።
በዚህም ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ የቀጠለ ሲሆን፣ እስከ ጥቅምት 30/2014 ዓ.ም ድረስ 338 ሚሊዮን 588 ሺሕ 367 ብር መሰብሰቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
የተሰበሰበው ገንዘብ ከአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተገኘ ሲሆን፣ ገንዘቡ በቦንድ ግዥ እና በድጋፍ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች የተሰበሰበ መሆኑ ተመላክቷል። ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 180 ሚሊዮን 382 ሺሕ 135 ብር ከዳያስፖራ አባላት የተገኘ ሲሆን፣ 90 ሚሊዮን 866 ሺሕ 678 ብር ደግሞ ከአገር ውስጥ የቦንድ ግዢ እና ልገሳ የተገኘ ነውም ተብሏል።
እንዲሁም ቀሪው 67 ሚሊዮን 339 ሺሕ 553 ብር ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች እና በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች የተሰባሰበ እንደሆነ ነው የተጠቆመው።
በ2013 ዓመት አጠቃላይ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ በዓመቱ መጨረሻ ሐምሌና ነሐሴ ብቻ 201 ሚሊዮን ብር ገደማ ተሰብስቧል ነው የተባለው። በተያዘው በጀት ዓመትም እንዲሁ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 እስከ ጥቅምት 30/2014 ድረስ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ቦንድ ግዥና ልገሳ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ16 ቢሊዮን 67 ሚሊዮን 603 ሺሕ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን እና በዚህ ወቅትም አገሪቱ በሕልውና ዘመቻ ላይ ብትሆንም ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ከጽህፈት ቤቱ ለማወቅ ተችሏል።
በዚህም፣ ሕዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ ለማስቀጠል በተያዘው በጀት ዓመት የተለያዩ ሁነቶች፣ የ8100 አጭር መልዕክት፣ የኤስ ኤም ኤስ ሎተሪ እና ሌሎች ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ ነው የተባለው።
ከወራት በፊትም እንዲሁ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል እና በተለየ መልኩ ድጋፉን ለማጠናከር ‹‹It Is My Dam›› በሚል የሞባይል መተግበሪያ ይፋ መደረጉ አይዘነጋም።
የግድቡ ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማማንጨት እንደሚጀምር እና ለዚህም የሚያግዙ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውም ተሰምቷል። በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቅርቡ 700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምርና የሕዳሴ ግድቡ ግንባታም 24 ሰዓት ሙሉ በፈረቃ እየተከናወነ እንደሆነ፣ ግንባታውም በመልካም ሒደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 82 በመቶ መድረሱን፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014



