ኢትዮጵያ የምትጠቀምበትን ወደብ ወደ 10 ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ

0
1067

ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸውን ወደቦች ከስድስት ወደ 10 ከፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ።

በአሁኑ ሰዓት የወጪ እና ገቢ ጭነት አገልግሎት የሚሰጡ የውኃ ወደቦችና እና የደረቅ ወደብ ኮሪዶሮች በቁጥር ስድስት ሲሆኑ፣ በቀጣይ ወደ ዐስር ከፍ ለማድረግ የዐስር ዓመት ዕቅድ መያዙን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሺ ፈቃደ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ እና ሠፊ የቆዳ ሽፋን ያላት ትልቅ አገር በመሆኗ፣ ‹ሎጅስቲክስ› የሚያደርሰውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የማንጠቀመው የወደብ አማራጭ አይኖርም ብለዋል።

በዚህም ከሦስት ዓመት በፊት በርበራ ወደብን፣ እንዲሁም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ የታጁራ ወደብን መጠቀም የተጀመረ ሲሆን፣ አምና 98 በመቶ የነበረው የጅቡቲ ወደብ አጠቃቀም በዚህ ዓመት ወደ 77 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል። ወደፊትም ሌላ አማራጭ ወደቦችን በማስፋት አልያም በርበራና ታጁራ ላይ ያለውን የመጠቀም አቅም በማሳደግ ጅቡቲ ላይ ያለውን ድርሻ ለመቀነስ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ፖርት ሱዳንም አሁን ባለው ኹኔታ የቆመ ቢሆንም፣ ወደፊት መረጋጋት ሲኖር እንጠቀምበታለን ሲሉ የሺ ፈቃደ ገልጸዋል።
እንዲሁም በኬንያ ‹ላሞ ኮሪዶር› የሚሰኝ መኖሩን አንስተው፣ ወደፊት የኤርትራ ወደቦችን ለመጠቀምም በኢትዮጵያ በኩል ዝግጅት መኖሩን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

በሎጅስቲክስ ቋንቋ ውስብስብነት፣ ጊዜ እና ዋጋ ወሳኝ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በዋናነነት የወደብ አማራጮችን ማብዛት ውስብስብነቱ እንዲቀላጠፍ፣ የምናወጣው ጊዜና ገንዘብም እንዲቀንስ ያደርጋል ነው ያሉት። ከዚህ በፊት የጅቡቲ ወደብ ላይ በነበረው መጨናነቅ መኪና ገብቶ ዕቃ ለማውጣት እንኳን አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸው፣ በርበራና ታጁራ ወደቦችን መጠቀም ሲጀመር ይህ ችግር በአንጻሩም ቢሆን መቃለሉን አንስተዋል።

ይህም የጭነት ዕቃ መዘግይትን እና በመዘግይት የሚወጡ አላስፈላጊ ተጨማሪ ወጭዎችን ከመቅረፍ ባሻገር፣ የወደብ ኪራይን በተመለከተ ለመደራደር በር ይከፍታል ባይ ናቸው። አማራጭ ስናገኝ ቀድሞ የምንጠቀምበት ወደብ ስለሚፈራ ቅናሽ ማድረጉ አይቀርም ካሉ በኋላ፣ በርበራና ታጁራን መጠቀም ከተጀመረ ወዲህ ጅቡቲ ወደብ በአንዳንድ ዕቃዎች የወደብ ኪራይ ላይ ቅናሽ ማድረጉን አንስተዋል።

ለወደብ አማራጭ ፍለጋ ርቀት ዋና ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ በሎጅስቲክስ አንድ ኪሎ ሜትር በቀነሰ ቁጥር የሚቀንሰው ገንዘብ ትልቅ መሆኑን እና የሚወስደው ጊዜም እንደሚቀንስ ነው የጠቆሙት። በርበራና ታጁራ ወደቦችም በዚህ ረገድ ያስገኙት ጥቅም ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም፣ የአማራጭ ወደቦች መብዛት ከውጭ የሚገቡ እና የሚወጡ ምርቶችን በአነስተኛ ዋጋ እና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ አጽንዖት ሰጥተውበታል። አንድን ዕቃ በጅቡቲ ወደብ በኩል ጎንደር እንዲደርስ ከማድረግ ይልቅ፣ በፖርት ሱዳን በኩል እንዲገባ ማድረግ ቢቻል ከፍተኛ የሆነ የገንዘብና የጊዜ ለውጥ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት።

ስለዚህም፣ በቀጣይ በየአካባቢው በቅርበት የአማራጭ ወደቦችን ቁጥር በማሳደግ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ የኬንያ ወደቦችን እንዲጠቀም፣ በርበራና ታጁራ ወደቦች ለሶማሌና ለምሥራቅ ኢትዮጵያ እንዲያገለግሉ፣ የኤርትራ ወደቦች ደግሞ ለሰሜን ምስራቅና ለሰሜን ኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ እንዲሁም ምዕራብ ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን በኩል የወደብ አግልግሎት እንዲያገኝ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here