ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማጓጓዝ የሚከፈለው የትራንስፖርት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎች ገለጹ፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉና መቀመጫውን አዲስ አበባ ከተማ ያደረገ ኢንተርናሽናል አስመጪ እና ላኪ ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከአንድ ዓመት በፊት የአንድ ኩንታል መጫኛ ዋጋ ከ120 ብር በታች ነበር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን 170 ብር ደርሷል ነው ያሉት፡፡
ይህም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ወደብ ድረስ ሲሆን፣ አንድ የጭነት መኪና 400 ኩንታል የሚይዝ በመሆኑ 68 ሺሕ ብር ገደማ ሊያስከፍል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው የመርከብ ትራንስፖርትም እንዲሁ ከፍተኛ ወጭ እንደሚያስወጣ ገልጸዋል፡፡
ከሌሎች ቅሬታ አቅራቢዎችም ተመሳሳይ ሐሳብ የሚነሳ ሲሆን፣ ወደፊትም ችግሩ በምን መልኩ እንደሚፈታ አይታወቅም ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
በወጭና በገቢ ንግድ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሠማራው ‹የፍሬተርስ ኢንተርናሽናል› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ረዳት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዘሚካኤል ዳንኤል፣ የማጓጓዣ ዋጋ መወደዱን ገልጸው፣ ለዚህ በምክንያትነት ያነሱትም በዋናነት ምርት የሚልኩ አካላት መብዛትንና የመኪና መለዋወጫ (spare part) ዋጋ መወደዱን ነው፡፡ አያይዘወም የጭነት መኪኖች የመግዣ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩም ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም የጎማ ዋጋ መወደድ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የሹፌር አበል፣ የማውረጃና መጫኛ ክፍያ እና ሌሎች የሥራ ማስኬጃ ወጭዎች ተደማምረው የማጓጓዣ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ወደፊትም ዋጋው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ይሄዳል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በነበሩት ዓመታት አስመጭዎች የሚከፍሉት የጭነት ዋጋ ላኪዎች ከሚከፍሉት በዕጥፍ የበለጠ እንደነበር የገለጹት ረዳት ሥራ አስኪያጁ፣ አሁን ግን የላኪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ላኪዎች ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ወደብ ድረስ ለጭነት የሚከፍሉት ዋጋ እየጨመረ እንደሄደና ክፍተቱም እየጠበበ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በዚህም ከሦስት ዓመት በፊት ለተመሳሳይ ጭነት አስመጭዎች 160 ብር ገደማ፣ ላኪዎች ደግሞ 60 ይከፍሉ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ አስመጭዎች ከ200 እስከ 250 ሲከፍሉ፣ ላኪዎች ደግሞ ከ150 እስከ 170 ብር እንደሚከፍሉና ዋጋቸው ወደ መቀራረቡ እያመራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የንግድ ልውውጥ ተመኑ ከ23 በመቶ ወደ 48 በመቶ ማደጉም እንዲሁ የትራንስፖርት ዋጋ ንረት ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ለቡና ጭነት የትራንስፖርት ዋጋው እንደሚጨምር፣ እንዲሁም ከጥንቃቄ እና ከታማኝነት አንጻር ውድ ዕቃዎች ከገበያ ከፍ ባለ ዋጋ እንደሚጫኑም አመላክተዋል፡፡
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዘርፉ ኃላፊ የሆኑት አለማየሁ ወልዴ፣ መንግሥት ከ1984 ጀምሮ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነጻ ገበያ በመሆኑ በዚህ ጣልቃ አይገባም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ አክለውም፣ አስመጭና ላኪዎች ዕቃዎቻቸውን ዝቅተኛ ዋጋ ከሚያስከፍላቸው አካል ጋር በመዋዋል ወይም ጨረታ በማውጣት ማጓጓዝ ይችላሉ ብለዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትም የሚያደርጉት ይህን ነው ያሉት አለማየሁ፣ በዚህ ዘርፍ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚና የተሽከርካሪ ዕጥረት ሲያጋጥም በግዥ እንዲገባ ማመቻቸትና ድጋፍ መስጠት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዓለም የነዳጅ ዋጋን፣ የመኪና እና የመለዋወጫ ዋጋን መንግሥት መቆጣጠር እስካልቻለ ድረስ አላግባብ በዘርፉ ተሠማርተው ተገቢ ያልሆነ ነገር የሚፈጽሙትን ከመቆጣጠር ውጭ የጭነት ዋጋን ለመተመን የሚደረግ ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014


