መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበቦረና በተከሰተው ድርቅ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ለአደጋ መጋለጣቸው ተገለጸ

በቦረና በተከሰተው ድርቅ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ለአደጋ መጋለጣቸው ተገለጸ

በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት፣ በዞኑ በሚገኘው ቦረና ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ለአደጋ መጋለጣቸው ተገልጸ። በድርቁ ምክንያት በአካባቢው ከፍተኛ የግጦሽና የውኃ እጥረት በመኖሩ እንስሳቱ ለአደጋ መጋለጣቸው ተሰምቷል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ የዱር እንስሳት ፓርኮች እና ኢኮቱሪዝም ዳይሬክተር መሐመድ ኑር ጀማል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያና ኬንያ ብቻ ከሚገኙ የሜዳ አህያ ዝርያዎች አብዛኞቹ በቦረና ብሔራዊ ፓርክ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ አሁን ላይ በዞኑ ባለው ድርቅ ምክንያት የዱር እንስሳቱ የውኃ እጥረት እንዳጋጠማቸው አመላክተዋል።

ከዚህ አካባቢ እና ከምስራቅ አፍሪካ ውጭ ሌላ አገር የማይገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ናቸው ለአደጋ የተጋለጡት ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እንስሳቱ በዞኑ በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅ የተነሳ ድርቁን የለመዱና ከቤት እንስሳት በበለጠ ድርቅ የመቋቋም አቅም ያላቸው ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ውኃ ፍለጋ ከፓርኩ መውጣት ጀምረዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በዞኑ የዱር እንስሳት የሚገኙት በቦረና ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን፣ የሜዳ አህያ፣ አንበሳ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ እና ሌሎች ወደ 42 የሚደርሱ አጥቢ እንስሳት ፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል። እንዲሁም በፓርኩ 286 የሚደርሱ የአዕዋፍ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አራቱ ብርቅዬ ወፎች መሆናቸውም ተመላክቷል።

ዳይሬክተሩ በፓርኩ ውስጥ ያሉት ዕፅዋት በብዛት ቆላማ የአየር ንብረት ላይ የሚበቅሉ የቆላ ግራሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ በፓርኩ ውስጥ ያለው ሳር መድረቁን ገልጸዋል። ይህም ቅጠል ከሚበሉት ውጭ ሳር የሚግጡ የዱር እንስሳትን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ነው ያመላከቱት።

ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ለዱር እንስሳት በቂ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የአካባቢው ማኅበረስብም ቀን ለቤት እንስሳት ውኃ በሚያቀርብበት ቦታ ላይ ለዱር እንስሳቱም ውኃ እንደሚያስቀምጥና በዚህም እስካሁን የሞተ እና የተሰደደ የዱር እንስሳት አለመኖሩን አንስተዋል።

በቀጣይም፣ በዞኑ ቋሚ የውኃ አቅርቦት እንዲኖር በሚደረገው ጥናት ውስጥ የዱር እንስሳትንም ታሳቢ በማድረግ በመኖሪያ ክልላቸው እያሉ ውኃ የሚያገኙበት ዘዴ ከተመቻቸ ይሰዳዳሉ የሚለው ስጋት እንደማይኖር አንስተው፣ በአንጻሩ በኬንያ የሚገኙት የዱር እንስሳት ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ እንደሚችሉ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ የተነሳ፣ ቀደም ብሎ የተከስተው ድርቅ ወደፊትም ሊቀጥል እንደሚችል ተመላክቷል። አሁን ላይ በየቦታው የሚቆራረጥ ዝናብ የሚዘንብ ቢሆንም፣ ዝናብ የሚገኘው ከመስከረም እስከ ኅዳር ባሉት ወራት የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቁ ለወራት ሊዘልቅ መቻሉ ነው የተገለጸው።

ይህን ታሳቢ በማድረግም ለቤት እንስሳት ከሚደረገው ጎን ለጎን የዱር እንስሳትንም ከአደጋ ለመታደግ መኖና ውኃ ለማቅረብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። መፍትሔ ካልተበጀለት፣ በቤት እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ድርቅ በዱር እንስሳትም ላይ እንዲሁ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

በ2005 የተመሠረተው ቦረና ብሔራዊ ፓርክ 3741 ካሬ ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ የተለያዩ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎችንና አዕዋፋትን በውስጡ የያዘ ነው። በኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ ምክንያት ቀደም ብሎ ተስተጓጉሎ የነበረው የፓርኩ የቱሪስት ፍሰት አሁን ላይ ባለው የጸጥታ ምክንያት መቋረጡን ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች