የአዋሳ ሚሊኒየም ፔፕሲ ፋብሪካ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ

0
775

የሞሐ ለስላሳ አክሲዮን ማኅበር የአዋሳ ፔፕሲ ፋብሪካ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ተገለጸ።
ለሥራ ማቆም አድማው እንደመነሻ ምክንያት የሆነው፣ ሠራተኞች ሲጠብቁት የነበረው ዓመታዊ የደሞዝ ጭማሪ በያዝነው ዓመት እንደማይደረግ በመገለጹ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በሞሐ ለስላሳ መጠጦች ሥር ካሉ ስምንት ፋብሪካዎች መካከል ትልቁ እንደሆነ የሚነገርለት በአዋሳ የሚገኘው ሚሊኒየም ፔፕሲ ፋብሪካ፣ ሠራተኞቹ ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
በ1990 በተመሠረተው ፋብሪካ ውስጥ ከአምስት ዓመት በላይ ያገለገሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፋብሪካው ሠራተኛ፣ ድርጅቱ አትራፊ ሆኖ ሳለ፣ ዓመታዊ የደሞዝ ዕድገትን ሠራተኛወን ሳያማክር ለመከልከል በማናለብኝነት መወሰኑ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሌላ የፋብሪካው ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በተለያየ መልኩ የአስተዳደር ሠራተኞች ጥሩ ገቢ ስለሚያገኙ የኑሮ ውድነት ስለማይፈትናቸው በፈለጉት ሰዓት ሠራተኛውንም ሆነ የሠራተኛ ማኅበሩን ያላማከለ ውሳኔ ስለሚያሳለፉ ቅር መሰኘታቸውን እና ይሄን የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አክለውም፣ ከአስተዳደር ሰዎች ማስፈራሪያ ያሚመስሉ ይዘቶች ያሏቸው መልዕክቶች ለሠራተኞች እየደረሱ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተመሳሳይም ፣በተክለኃይማኖት እና ንፋስ ስልክ ፋብሪካዎች ያሉ ሠራተኞች ተመሳሳይ ዝንባሌ ላይ እንዳሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከአስተዳደር ሠራተኞች በቀር የአዋሳ ፋብሪካው ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዳልተመለሱ ተገልጿል።

በተለይም በተክለኃይማኖት ፋብሪካ ተቀጥረው የሚሠሩ የጽዳት ሠራተኛ እንደሚገልጹት ከሆነ፣ ከደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ውጪ የፋብሪካው አስተዳደር ሠራተኞችን ሳያነጋገር፣ ለአገር መከላከያ መዋጮ በሚል የአንድ ወር ደሞዝ በስድሰት ወር ክፍያ እንዲያዋጡ የሚያዝ ደበዳቤ መለጠፉ እንዳስቆጣቸው ተናግረዋል።

አክለውም፣ ኃላፊዎች በ10 ሺሕዎች ደሞዝ በሚከፈላቸው ፋብሪካ ውስጥ እታች ካለን ሠራተኞች እኩል የአንድ ወር ደሞዝ ያለ ሠራተኛው ይሁንታ እንቆርጣለን ማለት አምባገነናዊነት ሲሉ ነው የገልጸሉ።
የሠራተኛ ማኅበር አባላትንም ስንጠይቅ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው ይሉናል ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ አተያየት ሰጭው የገለጹት። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የሞሐ ለስላሳ ፋብሪካዎች አ.ማ. ካሉት

ፋብሪካዎች መካከል በመቀሌ ከተማ የሚገኘው ፋብሪካ እስካሁን ያለበት ደረጃ እንደማይታወቅ እና የደሴ ፋብሪካውም በሽብርተኝነት በተፈረጀው የህወሓት ቡድን አደጋ ሳይደርስበት እንዳልቀረ ለአዲስ ማለደ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የለስላሳ ፋብሪካው በውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት ለለስላሳ ማምረቻ ዋና ግብዓት የሚሆኑ ‹ኮንሰንትሬት› ማስገባት እየተቸገረ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በተለይም የአገር ውስጥ ስኳር አቅርቦት በቂ ባለመሆኑ ለተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ መዳረጉ ተገልጿል።

ኃላፊው አክለውም ፋብሪካው የሚከፍለው ‹ኤክሳይስ ታክስ› 25 በመቶ እንዲሆን መወሰኑ እና በጥሬ ዕቃ ዋጋ ንረት ምክንያት ከፍተኛ ችግር እየገጠመው ነው ብለዋል።
እነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ተደራርበው ድርጀቱ አጣብቂኝ ውስጥ በመሆኑ የተፈጠረ አለመግባበት መሆኑን ገልጸው አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት ውይይት እያደረገ ነው ተብሏል።

በምግብ መጠጥ እና መድኃኒት ኢንዱስተሪ ልማት ኢንስቲትዩት በተደረገ ጥናት እና በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አማካይነት የለስላሳ ፋብሪካዎች ከሚጫወቱት ትልቅ የሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር የኤክሳይስ ታክስ ቅናሽ እንዲደረግ ለገንዘብ ሚኒስቴር መቅረቡ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ የለስላሳ ኢንዱስተሪ መስክ እስከ ስድስት ሺሕ ለሚጠጋ ማኅበረሰብ ቋሚ እና አስከ መቶ ሺሕ ለሚጠጋ ማኅበረሰብ ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የኢንስቲትዩቱ ጥናት ያመለክታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here