ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ካርዶችን በወረቀት መተካት ጀመረ

Views: 348

ኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከውጪ አገራት የሚያስገባውን የሞባይል የአየር ሰዓት መሸጫ ካርድ በኤሌክትሮኒክ ቮቸር ዲስትሪብዩሽን (ኢቪዲ) የተሰኘ እና በወረቀት የሚታተም አዲስ አገልግሎት መተካት ጀመረ።

በአንድ ወር ውስጥ ሦሰት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የአየር ሰዓት ሽያጭ የሚያከናውነው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኹለት መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ የሚሆነውን በዚህ አዲስ ስርአት አከናውኗል። የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ደረሰኝ መልክ የቀረበው ይህ አገልግሎት፣ የምስጢር ቁጥሮቹ ያልተሸፈኑ እና ከመደበኛው የሞባይል ካርድ ዋጋ ላይ የአምስት በመቶ ስጦታም ያለው ነው።
ይህ አገልገሎት በኅዳር ወር የተጀመረ ሲሆን፣ በታኅሳስ ወር 200 ሚሊዮን ብር እና በጥር ወር 211 ሚሊዮን ብር ሽያጭ መከናወኑን በኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ሃጂ ተናግረዋል።

ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ 5000 ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ አገልግሎቱ በተለይ የምስጢር ቁጥርን የማይደብቅ በመሆኑ እንደታሰበው በአጭር ጊዜ ስኬታማ መሆን አልቻለም። ይህንን ለማሻሻልም ቴሌኮሙ እነዚህን ማሽኖች በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት መታሰቡንም መሐመድ ገልፀዋል። እነዚህ ማሽኖች ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅትም ቀጥታ ደንበኛ በሚገዛበት ጊዜ ብቻ መታተም እንዳለበት ተደንግጎ አከፋፋዮችም በዚሁ አግባብ ግብይቱን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

በቀጣይም ከባንኮች ጋር በመተባበር የኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖችን በመጠቀም የአየር ሰዓትን ለመሸጥ ዝግጅት በመደረግ ላይ ሲሆን፣ በሁሉም ባንኮች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ታውቋል። በተጨማሪም ደንበኛው ያለሰው እርዳታ በራሱ አገልግሎት የሚገዛበትን ‹ሰልፍ ሰርቪስ› የተባለ አዲስ ማሽንም ወደ ሥራ እንደሚያስገባ መሐመድ ገልጸዋል።

‹‹ደንበኞች የሚፈልጉትን ያህል የአየር ሰዓት ለማግኘት ገንዘባቸውን አስገብተዉ የአየር ሰዓቱን መቀበል የሚያስያችል ማሽን ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ተክለን ወደ ሥራ እናስገባለን›› ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም 17 በመቶ የሞባይል የአየር ሰዓት የሽያጭ አገልግሎቱን በኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ዘዴዎች ያደረገ ሲሆን፣ ድርጅቱ በዓመት ከዉጭ በስድስት ሚሊዮን ዶላር ያስገባ የነበረውን በ25 በመቶ ወይም የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ችሏል።

ቴሌኮሙ ‹ይሙሉ› የተሰኘ ኤሌክትሮኒክ የአየር ሰዓት መሸጫ ስርአት ዘርግቷል። በዚህም በተለይ ቸርቻሪ ባለሱቆች የተሻለ ጥቅም ቢያገኙበትም፣ ከሚወስደው ሰዓት አኳያ ሌሎች ሥራዎቻቸውን በማስተጓጎል ምክንያት እንደማይጠቀሙበት ይገልፃሉ። ይህንንም ለማሻሻል አዲስ መተግበሪያ ተዘጋጅቶ ከኹለት ሳምንት በፊት ለሻጮች መተላለፉን መሐመድ ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የአራተኛው ትውልድ ሲሪየስ የሆነውን ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ (Long Term Evolution-Advanced) የኢንተርኔት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ከጥር 25/ 2012 ጀምሮ በሥራ ላይ ማዋሉ የሚታወስ ሲሆን፣ የ4ጂ ኢንተርኔት አገልግሎቱ ከ2ጂ እና ከ3ጂ የተለየ ተጨማሪ ክፍያ እንደሌለዉም መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ድርጅቱ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ በስድስት ወራት ውስጥ 22.04 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንና የእቅዱን 104 በመቶ ማሳካት መቻሉን፣ ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ32 በመቶ እድገት ማሳየቱን በስድስት ወር ዘገባዉ አስቀምጧል።

የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት 45 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 44 ነጥብ 03 ሚሊዮን፣ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ 22 ነጥብ 74 ሚሊዮን ደርሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com