በአማራ ክልል በሚገኙ ጥብቅ ሥፍራዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

0
1699

በአማራ ብሔራዊ ክልል በሚገኙ ጥብቅ የእንስሳትና የብዝኅ-ሕይወት መገኛ ቦታዎች ላይ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የእሳት ቃጠሎ መድረሱን እና የደን ምንጠራ መካሄዱን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ የዱር እንስሳት ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር አብርሃም ማርዬ፣ በሰሜን ሸዋ በሚገኘው መንዝ ጓሳ ጥብቅ ሥፍራ የእሳት ቃጠሎ መከሰቱን ማወቅ ችለናል ብለዋል። በተጨማሪም በተጠቀሰው ቦታ ለቱሪስቶች አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አራት የማኅበረሰብ ‹ሎጅዎች› መዘረፋቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ግን፣ የእሳት ቃጠሎው ስላደረሰው የጉዳት መጠንም ሆነ ስለተዘረፉት ሎጅዎች ዝርዝር መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል። የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ያልተቻለው፣ በአካባቢው ያለው ሠላም አስተማማኝ ባለመሆኑና ቦታው ውስጥ መውጫ ያጣው ወራሪ ቡድን ተደብቆ ሊሆን ስለሚችል ነው ብለዋል።

መንዝ ጓሳ ጥብቅ ሥፍራ 7800 ሔክታር መሬት ስፋት ያለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ የሰረኔ ቆቅ፣ እንዲሁም በዓለም ላይ በጥቂት ከፍተኛ ቦታዎች ብቻ የሚገኙ የአስታና የአምጃ ዛፎች፣ ብቸኛው በደጋማ አካባቢ የሚበቅለው የጓሳ ሳርን በውስጡ የያዘ ነው።

በቦረና ሳይንት ወረኺመኑ ብሔራዊ ፓርክም እንዲሁ የደን ምንጠራ በማካሄድ ወደ እርሻ የገቡ አካላት ስለመኖራቸው መረጃ መኖሩን ዳይሬክትሩ ተናግረው፣ ከጦርነቱ ለመደበቅ ጫካ ገብተው ምንጠራ ያካሄዱ አካላት ሊኖሩ እንደሚችልም ገልጸዋል። ይሁን እንጅ እስካሁን በትክክል የደን ምንጠራውን ማን እንዳካሄደውና ምን ያህል ደን እንደተመነጠረ ማወቅ እንዳልተቻለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አስተማማኝ ሠላም ሲረጋገጥ ጉዳቱ በባለሙያዎች ተረጋግጦ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በደን ስብጥሩ ኹሉንም የያዘ ነው የተባለለት የቦረና ሳይንት ወረኺመኑ ብሔራዊ ፓርክ፣ የዝግባ ዛፍ፣ ጽድ፣ ጓሳ ሳርና አስታ ዛፍን ጨምሮ ከ460 በላይ የደጋና የወይና ደጋ የዕፅዋት ዝርያዎች አሉበት። 15,262 ሔክታር መሬት ስፋት ያለው ይህ ፓርክ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀይ ቀበሮና ጉሬዛ በብዛት እንደሚገኙበትም ለማወቅ ተችሏል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ላሊበላ አካባቢ የሚገኘው የአቡነ ዮሴፍ ጥብቅ ሥፍራም እንዲሁ መተላለፊያ ስለሆነ፣ የተበታተኑ የህወሓት ኃይሎች ለመውጣት ሲሞክሩ ጉዳት ሳያደርሱ እንዳልቀሩ አመላክተዋል። የአቡነ ዮሴፍ ጥብቅ ስፍራ 8500 ሔክታር መሬት ስፋት ያለው እና የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እንዲሁም የምኒልክ ድኩላ፣ የመሳሰሉ የዱር እንስሳትንና የተፈጥሮ ሀብት አቅፎ ይዟል።

በእነዚህ ቦታዎች በርካታ የዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት የሚገኝ ሲሆን፣ የዱር እንስሳቱ በተፈጥሮ አደንን ስለሚፈሩ በሚሰሙት የጥይት ድምጽ ክፉኛ ሲረበሹ መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ግልጽ አድርገዋል። አያይዘውም መዋያ እና ማደሪያ የሆነው መኖሪያ አካባቢያቸው ከተጎዳ፣ የዱር እንስሳቱም እንደተጎዱ ነው የምንቆጥረው ሲሉ ገለጸዋል። የመኖሪያ አካባቢያቸው መጎሳቆልና መቆራረጥ በዱር እንስሳቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትልም ነው ዳይሬክተሩ ያነሱት።

በጦርነቱ ወቅት ጊዜ ኖሮት በዱር እንስሳቱ ላይ ሕገ-ወጥ አደን የፈጸመ አካል ሊኖር እንደማይችል ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፣ የሞቱና የጠፉ፣ በአጠቃላይ ጉዳት የደረሰባቸው የዱር እንስሳት ካሉ ወደፊት በሚደረገው ጥናት የሚገለጽ ይሆናል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ብዙ ‹ስኳውቶች› እና የጥበቃ ሠራተኞች ግንባር ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ከጦርነት በተለቀቁ አካባቢዎች ላይ ሠላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንደተረጋገጠ ቅድሚያ ጥበቃውን በማጠናከር፣ የተጎዱ ሥፍራዎች ወደቀድሞ ኹኔታቸው እንዲመለሱ ያለምንም ቅደመ ኹኔታ እንሠራለን ብለዋል።

ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በቀጥታ ጥቃት እንዳልደረሰበትና በቅርቡ ለቱሪስቶች ክፍት እንደሚሆን ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን መጎብኘት የሚፈልግ አካል ቢኖር መጎብኘት እንደሚችል የፓርኩ ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ማሳወቁን ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here