አይበቃም?

Views: 291

ከሰሞኑ በሴቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ብሶባቸው ታይተዋል። በተለይም በቤት ውስጥ ጥቃት ‹ባል ሚስቱን ገደለ› የሚል ዘግናኝ ዜና ሰምተናል። ከማውገዝ፣ ደጋግሞ ከመናገርና ከማሳሰብ ውጪ ምን ይደረግ ይሆን? እንደተለመደው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንጩኽ ይሆን? ስድብ ይሻላል? እህቶቻችን እንደ ቅጠል ሲረግፉ እየተከተልን በሰልፍ እንቅበራቸው? ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹ሕጉን እዩልን› እንበል? ነው ወይስ እንታጠቅ?

ስለ ሕግ እውቀት የለኝም። ነገር ግን የቤት ውስጥ ጥቃትን በሚመለከት ብዙ የሚቀረው እንደሆነ ዝምታው ያስታውቃል። ጀብዱ ይመስል ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች ዝና እንጂ ፍርዱና የተጣለባቸው ቅጣት አይነገርም። በእርግጥ አንዳንዴ ባይነገር ያሰኛል፤ እያመኑት ክህደት ከፈጸመ ሰው ይልቅ ፍትሕን እንዲሰጥ የተጠበቀ የሕግ ውሳኔ የባሰውን ሊያስቀይም ስለሚችል።

ቦጋለች ገብሬ (ነፍስ ይማር) በከንባታ የሴቶችን ግርዛት ብዛት መቀነስ የቻለ እንቅስቃሴ ካደረጉና ውጤታማ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ በተለያዩ የሴቶች መብቶች እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ላይ ቅስቀሳና እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር። ብዙ ጊዜ ደጋግሜ በማነሳው በአንድ የሥራ አጋጣሚ የቤት ውስጥ ጥቃትን በሚመለከት ባሰናዱት መድረክ ላይ ለመገኘት እድሉ ገጥሞኝ ነበር።
በከንባታ አካባቢ የሴቶች ጥቃት ከፍተኛ ደረጃ ደረሰ የሚባል ነው። ያውም የሃይማኖት ትምህርት ያስተምራሉ በሚባሉ ሰዎች የሚደረገው ጥቃት አስፈሪና አሳፋሪ ነው። ታድያ ቤት ውስጥ ጥቃትን በሚመለከት ግንዛቤ ለመፍጠር በተዘጋጀ ክዋኔ ላይ፣ በአዳራሹ ተሳታፊ የነበሩ ሴቶች አብዘኞቹም ተመሳሳይ በሆነ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አንዲት ሴት ተነስታ ተናገረች።

‹‹አባቴ እናቴን በጭካኔ ገድሏታል። ያንንም በዐይኔ አይቻለሁ። አሁን በእስር ቤት ይገኛል። ግን ከእስር ቤት ፈቃድ እየተሰጠው በከተማዋ ለአንዳንድ ጉዳዮች ሲወጣ አየዋለሁ። ይህ ፍትህ ነው ወይ?›› ስትል ትጠይቃለች። የቤት ውስጥ ጥቃት ሲባል ወንድ በሴት ላይ የሚያደርሰው ብቻ የሚመስለው፣ ሴቶች ብቻ ሊጮኹለት የሚገባ ጉዳይ የሚመስለው የከፋ ሞኝ ነው። ምክንያቱም ዳፋው ለቤተሰብ ሁሉ የሚተርፍ ስለሆነ።

የልጆች መበተንና ሥነ ልቦና መሰበር፣ ያለ አሳዳጊ መቅረት ይከተላል። ይህ ብቻ አይምሰላችሁ! በየእያንዳንዳችን አእምሮ እየታተመ የሚሄደው አስከፊ ክስተት በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ስጋትን፣ አለመተማመንን፣ መፈራራትን፣ ጥላቻን የሚዘራ ነው። ልዩነቱ መቼ ተገልጦ እንደሚታይ አለማወቃችን ብቻ ይመስለኛል።

የቤት ውስጥ ጥቃት ገበና ነው፤ በብዙ ሴቶች ሕይወት ውስጥ። አደባባይ አውጥተው አይናገሩትም። ባሎቻቸው ይህን ዓይነት ጸባይ እንዳላቸው ቀድመው እያወቁ እንዳገቡ¡ አልያም የባላቸው ወላጅና አሳዳጊ ሆነው ስለ ክፉ አመሉ ይጠየቁበት ይመስል፣ ኃላፊነት ይሰማቸዋል። ከሚደርስባቸው ጉዳት ይልቅ ሐሜቱን ይፈራሉ። ስህተቱና ጥፋቱ የራሳቸው እንደሆነ እያሰቡ ያፍራሉ።

ይሄ ሁሉ ታድያ ‹መቻል› በሚባል ማሸጊያ ተጠቅልሎ፣ አብዛኛውን ትዳር እንዳይወድቅ ለመደገፍ በሴቶች ጫንቃ ላይ ያረፈ ማስደገፊያ ነው። ይህ የቤት ውስጥ ጥቃት ግን አድጎና ደርጅቶ መሣሪያ ሲያስመዝዝ አይተናል።

ብዙዎች ታድያ ይህን ትተው ምክንያቱን ይጠይቃሉ። ምን አድርጋው ነው ይላሉ? ምን ታደርገዋለች? ደግሞስ ምንስ ብታደርገው እጁን አንስቶ በሕይወቷ እንዲፈርድ ማን ሥልጣን ሰጠው? ደግሞ ስናውቅ የተከዳች፣ የተተወች፣ የተገፋች፣ አላውቅልሽም የተባለች፣ የተደፈረች፣ የተደበደበች ሴት መሣሪያ መዝዛ መች ገድላ ታውቃለች? ሞት የሚያንሳቸው ምንም በማታውቅ ትንሽ ልጅ ላይ ሳይቀር ስንት በደል አድርሾች መኖራቸውን አናውቅም?

ከሁሉም ከሁሉም ግርም የሚለኝ ግን የሕግ ዝምታ፣ የፍትሕ ፀጥ ማለት ነው። እነሱም ‹እየቻሉት!› ይሆን እንዴ? መችስ ነው ይህ የሚያበቃው?
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com