ሙሥና ገንዘብ መዝረፍ ወይም ጉቦ መቀበል ብቻ አይደለም። አንድ በኃላፊነት የተመደበ አካል ኃላፊነቱን ለራሱ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ካደረገው ወይም ኃላፊነቱን ተጠቅሞ አግባብ ያልሆነ ሥራ ከሠራ ይህም ሙሥና ነው ተብሎ ይታመናል። ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ተቋማትና መንግሥታትም ሳይቀር ሙሥና እንደሚፈጽሙ ይነገራል። በዚህም፤ ተገቢ ያልሆነ የደረጃ ዕድገት፣ አቅምን ያላገናዘበ ደሞዝ፣ ብሎም ተገቢ ላልሆነ ዓላማ መቆም በሙሥና ዝርዝር ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በሙሥና ክፉኛ ከተፈተኑና እየተፈተኑ ካሉ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል። በተለይ በ 2010 ለውጥ ከመደረጉ ቀደም ብሎ በነበሩት ሦስት ዐሥርት ዓመታት የነበረው ሥርዓት፣ አገሪቱን በሙሥና እንዳጎሳቆላት በተደጋጋሚ ይነሳል። ከ1983 በኋላ፣ በሦስትና በአራት ወራት ውስጥ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የዘረፉ ባለሥልጣናት መኖራቸውን በወቅቱ መረጃውን ያውቁ ከነበሩ አካላት መረዳት ይቻላል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ኹኔታ እንደወትሮው የመንግሥት ሥራዎች በመደበኛ ጊዜያቸው የአሠራር ሒደታቸውን ጠብቀው የሚከወኑበት ወቅት አይደለም። ሥራ ያቆሙ የመንግሥት ቢሮዎች አሉ፤ እንዲሁም ደግሞ በትንሽ የሰው ኃይል ሥራቸውን የሚሠሩ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ይኖራሉ። ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረው አደረጃጀት አንዳንድ ሰዎች ልምዱ በሌላቸው የሥራ ቦታና ኃላፊነት ላይ ተመድበው በጊዜያዊነት እየሠሩ ሊሆንም ይችላል።
ይህም ከመደበኛ አሠራር ወጣ ብሎ ሥራን መከወን እና ሌሎች በጦርነት ወቅት የሚከሠቱ አዳዲስ ሥራዎች ጉቦ ለመስጠትና ለመቀበል ለሚፈልጉ አካላት መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ተከትሎ በጥርጣሬ የሚታሠሩ ሰዎች አሉ። በዚህም ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው የሕግ አካላት እጅ መንሻ ተቀብለው እስረኛ እንደሚፈቱና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መስተጓጎል እንደሚፈጥሩ ይሠማል። በሌላ በኩል፣ በየቦታው ለተፈናቃይ ወገኖችና ለወታደሩ ከበርካታ አቅጣጫዎች ዕርዳታ ይሰበሰባል። የመንግሥት በጄት ከተያዘለት ዕቅድ ተዛውሮ ለጦርነት ወጭ ሲደረግ፣ እንዲሁም ለሌላ ዓላማ የተበጀቱ በጄቶች ሲታጠፉ ይስተዋላል። በዚህ ጊዜ ወትሮም ግልጸኝነት የሚጎድለው አሠራር ለምዝበራ በእጅጉ እንደሚጋለጥ መገመት አያዳግትም።
በኢትዮጵያ ሙሥና ሥር የሰደደ መሆኑ ግልጽ ነው፤ በዚህም ሙሥናን ለመዋጋት ኃላፊነት የተጣለባቸው በርከት ያሉ ተቋማት መኖራቸው ደግሞ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ኃይል፣ ጸረ-ሙሥና እና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፍርድ ቤቶችናና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው ተቋማት ይጠቀሳሉ።
በዚህም አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ሙሥናን ለመከላከል፣ ዋና ዋና የሚባሉ የሚመለከታቸው ተቋማት በየድርሻቸው ምን እየሠሩ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማብራሪያ ጠይቃለች።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ጀይላን አብዲ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከወቅቱ ጋር በተያየዘ ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ወይም ቤታቸው ሲፈተሽ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያና ሌላም ነገር ተገኝቶባቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን ጉቦ ተቀብለው የሚፈቱ ፖሊሶች መኖራቸውን ጥቆማ ደርሶናል ብለዋል። ሆኖም የሚደርሱንን ጥቆማዎች በኹለት መልኩ ነው የምናያቸው ያሉ ሲሆን፣ አንደኛ፣ ጥቆማዎቹ ትክክለኛ መሆናቸውን እናጣራለን። በዚህም እስረኛን በገንዘብ ከማስፈታት ጋር በተያያዘ፣ ትክክለኛ በሆኑ ጥቆማዎች ላይ ተነስተን፣ እስካሁን ከአምስት በማይበልጡ ሥነ-ምግባር በጎደላቸው የፖሊስ አባላት ላይ ዕርምጃ ወስደናል ነው ያሉት። ኹለተኛ፣ አሁን ላይ የሽብርተኞችን ዓላማ በሚገባ እያከሸፈ ያለው በዋናነት ፖሊስ በመሆኑ፣ ሕዝብ እንዳይተባበረውና መረጃ እንዳይሰጠው፣ የፖሊስን ገጽታ በማበላሸትም ኹሉንም ሌባ ለማስመሰል ከጉቦ ጋር በተያያዘ ሐሰተኛ ጥቆማዎች ይቀርባሉ ብለዋል።
በዚህም መረጃዎች በልክ መታየት አለባቸው ያሉት ጀይላን፣ በፖሊስ ውስጥ የሚሠሩ የሙሥና ወንጀሎችንም ጥቆማ ከደረሰን አጣርተን ዕርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ አንልም ሲሉ ገልጸዋል። ሕዝብ የፖሊስ ዐይንና ጆሮ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሕዝብ ውስጥ የሚሠራውን የሙሥናም ይሁን ሌላ ወንጀል፣ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት ከተቻለ ወንጀል የሠሩ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ ኹሌም ዝግጁ ነን። ሕዝቡም ለፖሊስ ሊተባበር ይገባል ባይ ናቸው። እስካሁንም በሕዝቡ ጥቆማ በርካታ ጉዳዮችና ወንጀለኞች እንደተያዙ አመላክተዋል።
የፌደራል ፀረ-ሙሥና እና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን፣ የፀረ-ሙሥና ሕግ ምክር ትግበራና ልምድ ቅመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ገዛኸኝ ጋሻው በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ በዋናነት የሚሠራው ሙሥናን መከላከል፣ ሥነ-ምግባር ግንባታ፣ ጥናትና ሥልጠና ማዘጋጀት መሆኑን ገልጸው፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናትን ሀብት መመዝገብም ሌላው ሥራው ነው ብለዋል። ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ጋር በሚገናኝ የሚፈጠሩ የሙሥና ወንጀሎችንም ይሁን ሌሎች በሙሥና የተጠረጠሩ አካላት ካሉ አጣርቶ ለሕግ ለማቅረብ የሚመለከተው ፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
ሆኖም ካለው ሰፊ የሙሥና ወንጀል አንጻር፣ ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ሲሠራ አይስተዋልም በሚል ወቀሳ ቢቀርብበትም፣ ከተቋቋመ እስካሁን በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠርና ሙሥናን ለመከላከል የአቅሙን እየሠራ ነው ብለዋል። አሁን ላይ ጦርነቱ ግንባር ላይ ቢሆንም፣ ሙሥናን መከላከልም ሌላኛው ግንባር ነው ብለዋል። ስለሆነም ከዚህ በፊትም በርካታ የሙሥና ወንጀሎችን እንዲጋለጡ አድርገናል፤ በቅድመ መከላከልም ሳይፈጸሙ ያስቀረናቸው አሉ ነው ያሉት። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተሠራ ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ 300 የሚደርሱ ባለቤት አልባ ሕንጻዎች እንደተገኙ መረጃዎች አሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ጉዳዩ ግን የሚመለከተው የከተማ አስተዳደሩን ነው ብለዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጠበቃ ዳንኤል ፍቃዱ እንዲሁ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ምክንያት ሙሥና ነክ የሆኑ ድርጊቶች በስፋት መኖራቸውን እስማማለሁ ካሉ በኋላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁም ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችል አመላክተዋል። ዐዋጅ ቁጥር 5/2014 ላይ አንድ ሰው በፖሊስ ከተጠረጠረ ይታሠር ይላል፣ ይህ ደግሞ አንድ ሰው ጠርጥሬሀለሁ ተብሎ የሚታሠር ከሆነ ያ ሰው ሊያሥረው ከመጣው አካል ጋር በገንዘብ ለመደራደር መሞከሩ አይቀሬ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በሌሎች ሕጎች ምክንያታዊ ጥርጣሬ ካለ ነው ሰዎች የሚታሠሩት ያሉት ጠበቃው፣ ፖሊስ የተሰጠው ሥልጣንም በጣም የተለጠጠ በመሆኑ ለሙሥና በር ይከፍታል ባይ ናቸው። የታሠሩ ሰዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ለሕግ አለመቅረባቸውም እንዲሁ ሌላው ለሙሥና ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን አመላክተዋል።
ዐዋጁ ውስጥ በግልፅ፣ ይህን ያደረገ ይህን ያህል የቅጣት መጠን ይጠብቀዋል የሚል ባለመኖሩ በደፈናው ይህን አታድርግ ከማለት ይልቅ ሙሥና እንዳይባባስ ከተፈለገ ግልጽ የሆነ ሕግ ያለው ዐዋጅ ማስቀመጥ እንደሚገባ አስምረውበታል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሆነው የሚያገልግሉት አወል ሱልጣን እንደገለጹት፣ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከተጣለ በኋላ ፖሊስ ከጉቦ ጋር የተያያዙና ሌሎች የተለያዩ ጥቆማዎች እንደሚደርሱትና ምርመራዎች እንደሚደረጉ ጠቁመው፣ እስካሁን ክስ ተመስርቶበት ፍርድ ቤት የቀረበ አካል አለመኖሩን ተናግረዋል። ፖሊስ በቂ ጥርጣሬ ካለው ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚችል ገልጸው፣ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ካላቀረበ የመፍታት ግዴታም የለበትም፣ ይህ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ምክንያት ተነስቶለታል ብለዋል። ይህም የሚሆነው ዐዋጁን ተከትሎ ፖሊስ ካለበት የሥራ ጫና አንጻር ሊሆን እንደሚችል አንስተው፣ ያለ ምክንያት ግን ተጠርጣሪውን ለአንድ ሰዓትም ለሕግ ሳያቀርብ ማቆየት እንደማይችል አመላክተዋል።
ሙሥናን የሚከላከሉ ተቋማት ጠንካራ መሆን አለባቸው፤ ጥቆማ እስከሚደርሳቸው መጠበቅም የለባቸውም። ሕዝቡም እያየ ነው ሙስና የሚፈጸመው ስለዚህ ማጋለጥ ይኖርበታል የሚሉ ሐሳቦችንም ሰንዝረዋል። ትራፊክ ፖሊስ ከሚቀበለው 50 እና 60 ብር ጀምሮ በሚሊዮን እስከሚዘርፉ ሌቦች ድረስ ተግባራቸው ከሕዝቡ የተሰወረ አይደለም። እጅ በእጅ ሲቀባበሉ ባያዩ እንኳን አዝማሚያውን አይተው ጥቆማ ቢሰጡ ፖሊስ አስቀድሞ ለመከላከል ሥርዓት ይዘረጋል ነው ያሉት።
ሌላው ፣ በሰሞኑ ወደ ደሴና ኮምቦልቻ ያቀና አንድ ጋዜጠኛ ስሜ ባይጠቀስ በማለት በቦታው ተገኝቶ የታዘበውን ለአዲስ ማለዳ አጋርቷል። በዚህም ከአዲስ አበባ ለወታደሩ ቁሳቁስ ይዘው የመጡ አንዳንድ ሰዎች ስጦታውን የሚሰጡበት መንገድ እጅግ ሥነ-ምግባር የጎደለው መሆኑን አንስቶ፣ ከአዲስ አበባ አንድ ክፍለ ከተማ የመጣች አንዲት ሴት ሽርጥ ስትሻማ ተመልክቻለሁ ይላል። በዚህም የምለብሰው የለኝም፣ ብርድ አለ ስጭኝ እያለ የሚለምናትን ወታደር እምቢ በማለት መልሳ ይዛው ስትሄድ መመልከቱን ነው የገለጸው።
በብርድ እየተኮራመቱ ለሚዋጉ ወታደሮች ተብሎ የመጣውን መውሰድ ይቅርና የራስንም መስጠት ይገባ ነበር ያለው ጋዜጠኛው፣ በርካቶችን አስመሳይነትና ስግብግብነት ስለተጠናወታቸው ባገኙት አጋጣሚ ኹሉ የራሳቸውን ጓዳ መሙላት እንደሚፈልጉ ይገልጻል። ያለፈው ሥርዓት ትልቅ የሌብነት ሥነ-ልቦና ትቶ ማለፉንም ነው ያነሳው።
እንዲሁም፣ ሌላ ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በአንድ ምሽት የተመለከተውን ጉዳይ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጽ፣ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከወጣ በኋላ አንድ ምሽት ሦስት ሰዓት አካባቢ መታወቂያ ያልያዙ በርካታ ሰዎችን ያስቆሙ ፖሊሶች ለደቂቃዎች ካስቆሟቸው በኋላ፣ ያላችሁን ስጡና ወደ ቤታችሁ ግቡ አሏቸው፤ እነሱም ከኪሳቸው ያላቸውን ሰጥተው ሲገቡ በቅርብ ሆኜ ዐይቻለሁ ብሏል።
ሙሥና አገርን ወደኋላ በመጎተት የሚስተካከለው አይኖርም። አገርን ለማልማትም ሆነ ለማጥፋት ሙሥና ላይ ያለ አመለካከት ዋና ጉዳይ እንደሆነ ከበርካታ አገሮች መረዳት ይቻላል።
ሙሥና ሰዎችን በመንግሥት አግልግሎት ተስፋ ማስቆረጥ፣ ማበሳጨት፣ ላልተፈለገ ዓላማ እንዲነሳሱ ማድረግን፣ የመሳሰሉ ተግባራትን ሊያስከትል ይችላል። ስለሙሥና ወንጀሎች ዐዋጅ ቁጥር 881/2007 ላይ የተቀመጠውም ይህን የሚያረጋግጥ ነው። ‹‹ማንኛውም
የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ ላይ ያለበቂ ምክንያት ያልወሰነ፣ ያዘገዬ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ በሙሥና ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፤ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራትም ሊቀጣ ይችላል›› የሚል ተገቢ ሕግ ቢኖርም፣ ሕጉን ተረድቶ የሚሞግት ማኅበረሰብ አለመኖሩ፣ እንዲሁም ሕጉን የሚያስፈጽም ብቁና በቂ አካል መታጣቱ ሙሥና በኢትዮጵያ ተንሠራፍቶ እንዲዘልቅ ምክንያት መሆኑ የብዙዎች ዕምነት ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



