ሳቤላ ከድር በ‹ፎከስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጵያ› የቡድን መሪ ናቸው። ሳቤላ በፈለጉት ፍጥነት እግራቸውና እጃቸው በትክክል ማንቀሳቀስ የማይችሉ የአካል ጉዳተኛ ናቸው።
ሳቤላ የአካል ጉዳቱ የደረሰባቸው ገና በእናታቸው ማህፀን በነበሩበት ወቅት እንደሆነ ይናገራሉ። ሳቤላ ነገሮችን እያገናዘቡ ሲመጡ፣ ራሳቸውን ከጓደኞቻቸው ጋር ማነጻጸር ጀመሩ። እንደ ጓደኞቻቸው በፈለጉት ፍጥነት መሮጥ አይችሉም። አካላቸውም የተስተካካለ አለመሆኑንም አወቁ። ለምን እንደዚህ ሆንኩ? ለራሳቸው የሚጠይቁት ተደጋጋሚ ጥያቄ ነበር።
“የዘጠኝ ወር ነፍሰ-ጡር ነበርኩ፤ ከዕለታት በአንደኛው ቀን ዕቃ ለማንሳት በተንቀሳቀስኩበት ቅጽበት በሆዴ ወደቅሁ። የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ ሽሉ የመሞት ጉዳት ሳይደርስበት ለመወለድ በቃ። ከወለድኩ በኋላ ግን ቀስ በቀስ እያደግሽ ስትሄጅ የአካልሽ አቀማመጥ ትክክል አለመሆኑ እየለየለት መጣ” ሳቤላ ከእናታቸው የተረዱት የጥያቄያቸው ምላሽ ነበር።
ሳቤላ በጨቅላነት ዕድሜያቸው የጎደሎነት ስሜት ይሰማቸው ነበር። ነገር ግን፣ ለራሳቸው በሚለግሱት ተግሳጽና በቤተሰባቸው በሚደረግላቸው እንክብካቤ ቀስበቀስ በአእምሯቸው ዝር እያለ የሚያሸማቅቃቸውን የጎዶሎነት ስሜት ለመስበር ችለዋል።
‹‹እኔ ፈልጌ አላመጣሁት፤ ደግሞስ ያልተሰጠኝን ብቻ ለምን እመለከታለሁ! ካልተሰጠኝ ይልቅ የተሰጠኝ ይበዛል እኮ…›› ኹሌም የጎደሎነት ስሜት ሲሰማቸው ለራሳቸው የሚነግሩት ምክር ነው።
ሳቤላ ኹሌም የፈለጉትን መሥራት እንደሚችሉ ያምናሉ። ይህ በራስ መተማመናቸው ከአካል ጉዳተኞች ለየት ያሉ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ። “እንደሌሎች የኔ ዓይነት ሰዎች ጎደሎ ነኝ የሚለው ሐሳብ ቢያሸንፈኝ፣ የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ለልመና በቂ ነበር” የሚሉት ሳቤላ፣ ይህን ችግር ሠብረው በማለፍ በፊልም ሥራ ላይ ለመሳተፍ በቅተዋል።
ምንም ነገር ለማድረግ የሚወስነው የራስ ጥንካሬ ነው የሚሉት ሳቤላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ “ያልታበሱ እንባዎች” በሚል ፊልም እንደተሳተፉ ያስታውሳሉ። ለአካል ጉዳተኛ በፊልም ሥራ መሳተፍ ብዙ ፈተና እንዳለው ሳቤላ አልሸሸጉም። በመጀመሪያ የሠሩት ፊልም ላይ ልምምድ ሲያደርጉ፣ በታዳሚዎች ፊት ወድቀው በደም የተለወሱበትን ቀን የማይዘነጉት ትውስታቸው ነው።
የፊልም ሥራ በቃኝ ለማለት የዛን ጊዜው ክስተት በቂ ነበር የሚሉት ሳቤላ፣ ‹‹ለምንድነው ከችግር ላይ ችግር የምትፈልገው? አርፋ አትቀመጥም? ወዘተ.›› የሚለው የማኅበረሰቡ ጥያቄ በራሱ ከደረሰባቸው ችግር በላይ መሰናክል ሆኖባቸው እንደነበር ያወሳሉ።
ሆኖም ግን ሳቤላ ነቀፌታውን አጥብቀው ይወዱታል። “ተቃውሞ ያሠራኛል” የሚሉት ሳቤላ፣ ራሳቸውን በመቀበላቸው በፊልሙ ዓለም ለመሳተፍ በቅተው፣ በዚህ ወቅት ሌሎች የአካል ጉዳተኞችም በተመሳሳይ ሥራ እንዲሳተፉ ለማበረታታት ችለዋል።
በርግጥም የአካል ጉዳተኞች ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ እንዳልሆነ እራሳቸው ይናገራሉ። በጠቅላላው በአገሪቱ፣ በተለይም ወደ ገጠሩ አካባቢ ያሉ አካል ጉዳተኞች የማይታዩ፣ የማይዳሰሱ ነገር ግን ዝም ብለን በሕሊናችን የምናያቸው በርካታ ችግሮችን ያስተናግዳሉ ይላሉ ሳቤላ።
የአካል ጉዳተኞች በፊልም ሥራ የማሳተፍ ባህል እስካሁን ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ አሁን የሚስተዋለው እንቅስቃሴ የተደፋ አንገትን ቀና ለማድረግ በሚያስችል መጠን የተስፋ ብልጭታ እየታዬ ቢሆንም፣ አሁንም ገና ይቀረዋል ሲሉ አክለዋል።
ሳቤላ እንደሌሎች አካል ጉዳተኞች በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምርኮ ተይዘው ሌላ መክሊታቸውን አብረው መቅበር አይፈልጉም። ይልቁንም “የተመቻቸ መንገድ መፍጠር የሚቻለው ያልተመቸ መንገድ ላይ ሆኖ ነው” ባይ ናቸው።
“እሾህን በእሾህ” እንዲሉ፣ በሳቤላ ግንዛቤ መፍትሔ የሚፈጠረው ችግር ሲገጥም ነው። በመሆኑም አንዴ የተከሰተን ጉዳት እያሰቡ አንገት ከማቀርቀር፣ ችግሩ ከምንም ሥራ እንደማያግድ ለራስ መንገር የስኬት ቁንጮ ነው ይላሉ።
“መሥራት የሚቻለው በታጣው ነገር ሳይሆን ባለው ነገር ነው። በታጣ ነገር ላይ ሙጭጭ ማለት ያለውንም ማጣት ነው” ሳቤላ ኹሌም ለሕሊናቸው የሚያሳስቡት መልዕክት ነው። “አካል ጉዳተኛ ነኝ” ብሎ መደበቅ፣ መውጣት የሚችለውን ችሎታ በመደበቅ ሌላም ጉዳት መጨመር ነው ሲሉ ይመክራሉ።
አካል ጉዳተኞች በፊልም ሥራ እንዳይሳተፉ መንገዱን የሚዘጋባቸው፣ ‹‹የእኔን ፊልም ማን ያየዋል›› የሚለው የራሳቸው ዕሳቤ እንደሆነ ሳቤላ ተናግረዋል። ሳቤላንም በመጀመሪያ በፊልም ለመሳተፍ እንደ ተራራ ገዝፎ ታይቷቸው የነበረው “የእኔን ፊልም ማን ያየዋል?” የሚለው ጥያቄ ነበር።
እንደ ሳቤላ ገለጻ ከሆነ፣ እንዲያውም አካል ጉዳተኞች ፊልም ቢሠሩ ታሪክ የማይረሳው አሻራ በማስቀመጥ ሌሎችን ከማበረታታት በተጨማሪ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ የይቻላል መንፈስ እንደሚያሳድሩ መክረዋል።
ሳቤላ በመጨረሻም፣ አካል ጉዳተኞች በፊልም ሥራ ለመሳተፍ በመጀመሪያ ራሳቸውን መቀበል አለባቸው። ራሳቸውን ካልተቀበሉ በፊልሙ ዓለም መሳተፍ ይቅርና ከቤታቸውም ለመውጣት አይደፍሩምና ይህን ማድረጉ የመፍትሔ መንገድ ነው ሲሉ ነው ልምዳቸውን ያካፈሉን።
በአገራችን ብሎም በዓለማችን ውስጥ በአንድም በሌላም ምክንያት (በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ክስተት)፤ በርካታ የአካል ጉዳት ችግር የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።
በዓለማችን ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ብዛት አንድ ቢሊዮን እንደደረሰና በኢትዮጵያ ደግሞ 17.6 በመቶ የሚሆነው ማኅበረሰብ ክፍል የአካል ጉዳት ችግር እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል። በመሆኑም በአገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 20 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ይነገራል።
አብዛኛዎቹ የአካል ጉዳተኞች ከደረሰባቸው ጉዳት ይልቅ፣ በጉዳታቸው የተነሳ የሚከተሉት ለራስ ያለ አሉታዊ አስተሳሳብ ነጻነታቸውን ሲነጥቃቸው ማስተዋል የተለመደ ነው።
በአገራችን ከሚገኙት የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች መካከል ለድቃቂ ሳንቲም ፀሐይ ሲጠብሳቸው የሚውሉት፣ በአንድም በሌላም ምክንያት የተለያየ አካላቸው ጉዳት የደረሰበት ሰዎች ስለመሆናቸው መዲናችንን ተዘዋውሮ መመልከት ራሱ ችግሩን ለመረዳት ጊዜ አይወስድም።
የደረሰባቸው የአካል ጉዳት ሌላኛው መክሊታቸው እንዲቀበር ተጽዕኖ ያሳደረባቸው በርካታ ሰዎች ለድኅነት ተጋልጠው ይስተዋላሉ። ከሚታይ የአካል ጉዳት ጤነኛ የተባለው የማኅበረሰብ ክፍልም የአካል ጉዳተኞችን ምንም እንደማይሠሩ ሲመለከታቸው ይስተዋል።
የዓለም ባንክ በኢኮኖሚ ዙሪያ ካጠናው ጥናት መረዳት የሚቻለው፣ 20 በመቶ የሚሆኑት የዓለም ድሃ ሰዎች አንድ ዓይነት የአካል ጉዳት እንዳለባቸውና በራሳቸው ማኅበረሰብ ውስጥ በጣም ደካማ ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸውን ነው።
ይሁን እንጂ የአካል ጉዳተኞች ሆነውም እንደማንኛውም ሰው በራሳቸው የሥራ ዓለም ውስጥ የሚንቀሳቀሱ፣ የአካል ጉድለት እንከን ቢገጥማቸውም በአስተሳሰብ ልበ ሙሉ የሆኑ በርካታ የአካል ጉዳተኞች እንዳሉም ይነገራል።
በ1990 በዩናይትድ ስቴት በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ 12.2 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች በራሳቸው አነስተኛ የንግድ ሥራ እንደሚንቀሳቀሱና፣ 7.8 በመቶው ከፍ ያለ ደረጃ እንዳላቸው ተመላክቷል።
አካል ጉዳተኞች ወደ ሥራ እንዳይገቡ የሚያደርጋቸው፣ “እኔ አልጠቅምም” የሚል የዝቅተኝነት ስሜት ችግር መሆኑን የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሲያወሱ ይደመጣል።
አንድ አካል ስለጎደላቸው ብቻ ምንም ነገር እንደማይሠሩ አድርገው የሚደመድሙ ሰዎችም፣ ከልመና አልፈው ወደ ሥራ ለመግባት የግንዛቤ ዕጥረት ችግር ጎልቶ ይታይባቸዋል።
“እኔ ምን አቅም አለኝና በሥራ እሠማራለሁ” የሚሉት በመዲናዋ ውስጥ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ላስቲክ ዘርግተው በመለመን የሚኖሩ አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው አንድ እግራቸውን በመኪና አደጋ ያጡት አለሙ ታደሰ ናቸው።
የትምህርት ዕድል አግኝቼ ቢሆን በአንድ የሥራ ዘርፍ ገብቼ እሠራ ነበር፤ የቢሮ ሥራ ካልሆነ በስተቀር ሌላው ሥራ አካል ጎዳተኞችን የሚጋብዝ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች እንደሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ትምህርት ቤት ገበተው የመማር ዕድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል።
የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌደሬሽን መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኞች በትምህርት ገበታ እንዳልተሳተፉ ትምህርት ሚኒስቴር ማሳወቁን ያመላክታል።
የደረሰባቸውን ጉዳት ተቀብለው ባላቸው ነገር በመጽናናት በሌላ ሥራ ከመሠማራት የታቀቡ ሰዎችን መመልከት የተለመደ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት በ2021 ያወጣው መግለጫ እንደሚያመላክተው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ነጥብ አንድ በመቶ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል ያላገኙ ናቸው።
አካል ጉዳተኞች በፊልም ሥራ ውስጥ ተሳትፈው መሥራት ቢችሉም እንኳን፣ ይህን የማግኘት ዕጣቸው አነስተኛ ነው የሚሉት የፊልም ድርስት (እስክሪፕት) እየጻፍኩ እገኛለሁ ያሉን በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙት አይነ-ስውሩ ሲሃን ጀማል ናቸው።
አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኞች ምንም እንደማይሠሩ እራሳቸውን ስላሳመኑት በፊልም ሥራ እንኳ መሳተፍ አልቻሉም ያሉን ሲሃን፣ በኢትዮጵያ የሚሠሩት አብዛኛዎቹ ፊልሞች፣ በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ ቢያተኩሩ እንጂ፣ የችግሩን ገፈት ቀማሾች በሥራ ያሳተፉ አይደሉም ነው ያሉን።
በመሆኑም አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ሰዎች በፊልም ሥራ ላይ የተለያየ ገጸ ባህሪን ተላብሰው ቢሠሩ መልካም ነው ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን።
የችግሩን መፍትሔ በተመለከተም፣ አዲስ ማለዳ ፎከስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጵያ ከተሰኘ አካል ጉዳተኞችን በፊልም ሥራ ለማሳተፍ በሒደት ላይ ነኝ ካለ ድርጅት አንቀሳቃሾች ጋር ቆይታ አድርጋለች።
በቆይታዋም አካል ጉዳተኞች በፊልም ሥራ እንዲሳተፉ የሚያስችል ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች። ይኸውም ፎከስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች የፊልም ፌስቲቫል ይዞት የመጣው በአትኩሮት እየሠራሁበት ነው ያለውም “አካል ጉዳተኞችን ማካተት” የተሰኘው እንቅስቃሴ ነው።
በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት የሚያደርግ የፊልም ፌስቲቫል ጀምረናል የሚሉት የፎከስ ኦን አቢሊቲ ኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል አስተባባሪ (ኮኦርዲኔተር) ቤዛዊት ዳምጠው ናቸው።
ቤዛዊት እንደተናገሩት ከሆነ፣ ፌስቲቫሉን እንድናዘጋጅ ያነሳሳን ትልቁ ዓላማ ከዚህ በኋላ የሚሠሩት ፊልሞች አካል ጉዳተኞች ላይ አተኩረው እንዲሠሩና አካል ጉዳተኞችም ይህን ዕድል ተጠቅመው እንደማንኛውም ሰው በፊልሙ ሥራ እንዲሳተፉ ለማድረግ ነው ይላሉ።
በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ 20 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች አሉ የሚሉት ቤዛዊት፣ አካል ጉዳተኞች በፊልም ሥራ እንዲቀላቀሉ፣ ማኅበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች በሥራ መሳተፍ አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ለማበረታታት እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



