• የውኃ መሠረት ልማቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል
በአማራ ክልል ነጻ በወጡ በኹሉም አካባቢዎች ያሉ የውኃ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በሚባል ኹኔታ ዘረፋና ወድመት የተፈጸመባቸው በመሆኑ፣ በተለይ በከተሞች ያለውን ከፍተኛ የውኃ ዕጥረት ለመቅረፍ፣ በጊዜያዊነት ውኃ በሚጭኑ ቦቴዎች ውኃ ለማኅበረሰቡ እያቀረበ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
የክልሉ ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አደም ወርቁ እንደገለጹት፣ አሁን ላይ ከህወሓት ኃይሎች ነጻ በወጡ በብዙ ቦታዎች የመብራት አገልግሎት ስለሌለ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እስከሚገኝ ድረስ ላለው የውኃ ችግር በአስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት፣ የተለያየ መጠን ያላቸው የውኃ ማጠራቀሚያ ሮቶዎች በየከተሞቹ እየተሠራጩ ነው ብለዋል። በዚህም ውኃ በቦቴ ከጉድጓዶች በመቅዳት እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ኃላፊው ይህ የሆነበትን ዋነኛ ምክንያት ሲያነሱ፣ በኹሉም ከተሞች የውኃ መሳቢያ ፓምፖች እና ጀኔሬተሮች በመዘረፋቸው፣ በመውደማቸው፣ እንዲሁም የመብራት አገልግሎት ባለመኖሩ ቀድሞ ሲል አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የውኃ ተቋማት ከጥቅም ውጭ በመሆናቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለአብነትም በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ውኃ ማጠራቀሚያ ሮቶዎች ተሰራጭተው፣ በኹለት ቦቴ መኪኖች ውኃ በማቅረብ ሕብረተሰቡ ውኃ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከችግሩ ክብደት አንጻር ሁኔታው በመንግሥት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑም፣ ከውኃ ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የተለያየ ዓይነት ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን፣ በተደረገ የገንዘብ ድጋፍም ጀኔሬተሮች፣ ፓምፖችና ነዳጅ መገዛቱን ገልጸዋል። ሮቶዎችን በማቅረብም የተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕገዛ እያደረጉ መሆኑን ነው ያብራሩት። አክለውም የግል ባለሀብቶች ከፍተኛ ዕገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመብራት አገልግሎት ከሌለ ውኃ ማቅረብ ያስቸግራል ያሉት ኃላፊው፣ በተለይ በሰሜን ውሎ ያሉ አካባቢዎች መብራት የሚያገኙት አላማጣ ከሚገኝ ማሠራጫ በመሆኑ፣ መብራት በቶሎ ይለቀቃል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ውኃ በቦቴ ማቅረቡ ለሳምንታት ሊዘልቅ እንደሚችል አመላክተዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ቢሮው ነጻ በወጡ አካባቢዎች ባደረገው ምልከታ አንድም ከተማ ያልወደመ እና ያልተዘረፈ የውኃ ተቋም የለም ካሉ በኋላ፣ በየከተሞች በብዙ ብር ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የውኃ ተቋማት በሙሉ ወድመዋል፤ የተሻለ የሚባል እንኳን የለም ነው ያሉት።
የነበሩት አብዛኞቹ የውኃ ተቋማት ከጉድጓድ ውኃ የሚወጣባቸው ናቸው። በአንድ ከተማ ውስጥ ብቻ በርከት ያሉ ጉድጓዶች ተቆፍረው አገልግሎት ይሰጡ ነበር፤ ሆኖም የኹሉም ጉድጓዶች ከመሬት በታች የተቀበሩ ፓምፖችና ከመሬት በላይ የተተከሉ ጀኔሬተሮች ተዘርፈዋል፤ የተረፉትም ወድመዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ በምተገኘዋ ደብረ ዘቢጥ ከተማ የነበረ ትልቅ ጀኔሬተር ባትሪውን ነቅለው ከወሰዱ በኋላ፣ በጥይት ደብድበው እንዳይጠገን እና ከጥቅም ውጭ እንዲሆን አድርገውታል ሲሉ አብነት በመጥቀስ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የላሊበላ ከተማ የውኃ ጽሕፈት ቤትም እንዲሁ በውስጡ የነበሩ ኮምፒዩተሮች፣ በሚሊዮን ገንዘብ የተገዙ ፓምፖች እና የኤሌክትሮ-መካኒካል ዕቃዎች መዘረፋቸውን እና መውደማቸውን አስረድተዋል።
ኃላፊው ነጻ በወጡ አካባቢዎች የወደሙ የውኃ ተቋማት በክልሉ አጠቃላይ በሚገነባው የውኃ መሠረተ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይታወቃል ሲሉ ገልጸው፣ ሆኖም ግን ቢሮው በወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው የምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ዋና ትኩረት ሰጥቶ የውኃ ተቋማቱን ለመጠገንና መልሶ ለመገንባት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
በአካባቢዎቹ የመብራትም ይሁን የነዳጅ የኃይል አቅርቦት አለመኖሩ ዋነኛ ችግር መሆኑን አመላክተው፣ በአንድ ከተማ ብቻ እስከ አምስት የሚደርሱ የውኃ መሳቢያ ፓምፖችና ጄኔሬተሮች የሚያስፈልጉ በመሆኑ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል ሲሉ አብራርተዋል። የአንድ ጄኔሬተር ዋጋ ከ2.3 እስከ 3 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የፋይናንስ ችግር መኖሩንና ዕቃዎቹን በቀላሉ ገበያ ላይ ማግኘት እንደማይቻልም ነው ያነሱት።
በዚህም ኃላፊው ህወሓት በክልሉ መሠረተ ልማት ላይ ያደረሰው ጉዳት አስከፊ በመሆኑ ሕብረተሰቡም ችግሩን በመረዳት መተባበር እንዳለበትና በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014


