በአዲስ አበባ የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች ድጋፍ ባለማግኘታችን ችግር ላይ ነን አሉ

0
736

በጦርነቱ ምክንያት ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩት ተፈናቃዮች፣ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ተፈናቃዮች ወደ አዲስ አበባ የገቡት ተፈናቃዮች ከደብረ ብርሃን እንዳያልፉ ከመከልከላቸው በፊት ሲሆን፣ ድጋፍ እያገኙ ባለመሆናቸው የመሠረታዊ ፍጆታ ዕጥረት እንደገጠማቸው ነው የተናገሩት።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ ተፈናቃዮቹ ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች መጥው አዲስ አበባ ከተማ መኖር ከጀመሩ ከኹለት ወር በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዕርዳታ ያገኙት አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ተፈናቃዮችን ለማገዝ በአዲስ አበባ ከተቋቋመው የሰሜን ወሎ ተወላጆች ድጋፍ ሠጭ ኮሚቴ አንድ ሺሕ የምንሆን ሰዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው ድጋፍ ያገኘነው የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ በወቅቱ ድጋፍ ማግኘት ያልቻሉና ከዚያ ወዲህ የመጡት ሰዎች ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ ድጋፍ እንዳላገኙ ነው ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት።

ከተፈናቃዮች መካከል ባዬ ፈንታው የተባሉት ግለሰብ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከመጡ አንድ ወር እንደሆናቸው ገልጸው፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላገኙ ነው ምስክርነታቸውን የሰጡት።
ግለሰቡ አክለውም፣ ከአራት ቤተሰቦቻቸው ጋር ከዘመድ ቤት ተጠግተው እንደሚኖሩ ያመላከቱ ሲሆን፣ “የኑሮ ውድነት የራስ ምታት በሆነበት በዚህ ዘመን፣ በሰዎች ላይ ጥገኛ በመሆኔ እየተሳቀኩ ነው የምኖረው” ሲሉ ነው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት መጠለያ ስለሌለ ብዙዎች የመጠለያ ችግርም እንዳለባቸው አስተያየት ሰጭው ገልጸው፣ ጦርነቱ ተቋጭቶ ወደ አካባቢያቸው እስከሚመለሱ የሚመለከተው አካል ዕርዳታ ያደርግላቸው ዘንድ ጠይቀዋል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት አለም አበባው የተባሉ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው፣ “እኔ ከቤተሰብ ጋር ነው ተጠግቸ የምኖረው ነገር ግን፣ ማረፊያ አጥተው በመርካቶ፣ በመገናኛና በሌሎችም የተለያዩ ቦታዎች የሚንከራተቱ ሰዎችን ተመልክቻለሁ” ሲሉ ነው የአይን ዕማኝነታቸውን የሰጡት።

ድጋፍ ያስፈልገናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ በአሁኑ ወቅት እየኖሩ ያሉት ከፊሉ ቤት ተከራይተው፣ ከፊሉ ከዘመድ ቤት ተዳብለው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በየቦታው ተጠግተው መሆኑን ነው አዲስ ማለዳ መረዳት የቻለችው።
አዲስ ማለዳ እስካሁን ድጋፍ ሲያደርግ ከነበረው በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የሰሜን ወሎ ተወላጆች ኮሚቴ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቆይታ አድርጋለች።

የራያ ተወላጆች የሽማግሌዎች ሰብሳቢ አዲሱ በሬ በበኩላቸው፣ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ በአዲስ አበባ በሚኖሩ የሰሜን ወሎ ተወላጆች የተቋቋመው ኮሚቴ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በድጋሚ ዕርዳታ አለማድረጉን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው አዲስ አበባ ለሚገኙ አንድ ሺሕ ዜጎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው ዕርዳታ ያደረግነው የሚሉት አዲሱ፣ በድጋሚ ድጋፍ ያላደረጉት ብዙ ተፈናቃዮች ባሉበት በደሴ፣ በዞብል፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ድጋፍ እያደረግን ስለሆነ ነው ብለዋል።

ትኩረታችን ደሴ ወዳሉት ተፈናቃዮች ነው ያሉት አዲሱ፣ ድጋፍ አላገኘንም የሚሉት ሰዎች ወደ ደሴ ሒደው ማግኘት ይችላሉ ሲሉ አመላክተዋል። አያይዘውም ለድጋፍ ያሰባሰብነውን ኹለት ሚሊዮን ብር ብዙ ድጋፍ ፈላጊ አለ ብለን ወዳመንበት ወደ ደሴ ከተማ ሰሞኑን ልከናል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ የሚኖሩትን ተፈናቃዮች በተመለከተ የመጠለያም ሆነ የምግብ ፍጆታ ድጋፍ ለማድረግ የታሰበ ነገር ስለመኖሩ መረጃ የለኝም የሚሉት አዲሱ፣ በመሆኑም ተፈናቃዮቹ ድጋፍ እያደረግንበት ወደዳለው አካባቢ ሒደው ዕርዳታ ማግኘት ይችላሉ ሲሉ ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ የሚገኘው የሰሜን ወሎ ተወላጆች ኮሚቴ፣ በሳለፍነው ጳጉሜ 3/2013 ለአንድ ሺሕ ተፈናቃዮች 11 ሺሕ ኪሎ ግራም መኮረኒ ዕርዳታ ማድረጉን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here