በሰሜን ሸዋ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች፣ ለእኛ ተብሎ ከዕርዳታ ሰጭዎች የሚመጣውን ድጋፍ በአግባቡ እያገኘን አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በዚህም ከሚመጣው የዕርዳታ ቁሳቁስ ሕዝቡ አልወሰደም እንዳይባል ብቻ ተቀናንሶ ይሰጠናል እንጂ፣ ዕርዳታው በፍትሐዊነት ለሚገባው አካል እየደረሰ አይደለም ነው ያሉት።
መሠረት (የአባቷ ስም እንዲጠቀስ የማትፈልግ) የምትባል የከተማዋ ነዋሪ እንደገለጸችው፣ ጥቅምት ላይ ይሰጣል ተብሎ 64 ሺሕ ኩንታል ገደማ የስንዴ ዱቄት ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ለሕዝቡ ገባ ተብሎ የተነገረው ግን 49 ሺሕ ብቻ ነው። እንዲሁም ዕርዳታ ሊሰጣችሁ ነው በማለት እስከ ስምንት ቀን ምዝገባ ያካሒዳሉ፣ በመሀል ሌላ ባለሀብት ዕርዳታ ጭኖ ይመጣል፤ በዚህ ጊዜ ቀድሞ የገባውን ዕርዳታ ሙሉ ለሙሉ ይደብቁታል ብላለች።
እንደማስረጃም ጥቅምት 2/2014 የቀበሌ 02 ነዋሪዎች ዕርዳታ ተቀብለው፣ የቀበሌ 03 ነዋሪዎች፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሳይቀር፣ ዕርዳታው ስላለቀ ምንም ዓይነት ድጋፍ የለም ተባሉ። ሆኖም ግን በቅርብ ቀናት ውስጥ የህወሓት ታጣቂዎች ከተማዋ ሲገቡ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ውስጥ በርካታ የድጋፍ ዓይነት በድብቅ ተከማችቶ አግኝተው በተሳቢ መኪኖች ጭነው ሲወስዱ ማየቷን አንስታለች። በዚህም በኅዳር ወር ዕርዳታው እንደተዘረፈ እና ሕዝቡ ምንም እንዳላገኘ ነው የጠቆመችው።
የተለያየ ዓይነት ድጋፍ የሚመጣ ቢሆንም፣ የሚሰጠው ኹሉም ዓይነት ሳይሆን ወይ ምግብ ነክ የሆነው አልያም አልባሳት ነክ የሆነው የድጋፍ ዓይነት ተቀንሶ ነው ስትል የምትናገረዋ መሠረት፣ ሌሊት ከ4 ሰዓት በኋላ የሚዘረፈው ዕርዳታ ደብረ ብርሃንና ኮምቦልቻ ከተሞች እንደሚሸጥ ጠቅሳለች። በዚህ ሣምንትም የዕርዳታ ቁሳቁስ ጭነው የመጡ አካላትን ሕዝቡ እናንተ ከሄዳችሁ አይሰጡንም፤ እዚሁ እያላችሁ ይሰጠን ፤ ካልሆነ ግን ከመኪና መራገፍ የለበትም ብሎ ሲቃዎም እንደነበር አውስታለች።
ጀማል ይማም የሚባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ለሕዝቡ ድጋፍ የሚያቀርቡ አካላትን አመስግነው፣ የሚመጣው ድጋፍ ለተጎጅዎችና መድረስ ላለበት አካል እየደረሰ አለመሆኑን እና በወቅቱ መከፋፈል ያለበትም በመጋዘን ተከማችቶ ለዝርፊያ እየተዳረገ ነው ብለዋል። የከተማዋ አመራር የመጣውን ድጋፍ ከዕርዳታ ሰጭዎች ከመረከብና አሰጣጡን ከመቆጣጠር ውጭ ሰጭ መሆን የለበትም የሚሉት ጀማል፣ ይህን ማድረግ ያለባቸው የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶች ሊሆኑ ይገባል በማለት ይገልጻሉ።
በዚህ ሳምንት ለአንድ ቤተሰብ አስር ኪሎ ዱቄት ሲሰጥ ተመልክቻለሁ ያሉት ጀማል፣ ይህም የሆነው ካለው የዕርዳታ ዱቄት ማነስ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። የሚመጣውን ቁሳቁስ ለግላቸው ለመዝረፍ የሚሞክሩ አካላት ቅንነት ቢያድርባቸው ፍራሾችን ባዷቸውን ለቀሩ ሆስፒታሎች፣ ኮምፒዩተሮቹንም ለኮሌጁ በማስገባት የሕዝቡ መገልገያ የሆኑ ተቋማት መልሶ መገንባት ይቻል ነበር ባይ ናቸው።
ዳምጠው ጋሻው የተባሉ ሌላ የከተማዋ ነዋሪም እንዲሁ የሚመጣው የዕርዳታ ቁሳቁስ አሠጣጥ በጣም እንደሚያሳዝናቸው ገልጸው፣ በዚህ የተነሳ ስብሰባ ላይ አመራሮችን እስከ መቃወም መደረሱም ጠቁመዋል። አያይዘውም መረዳት ከፈለጉ እንደሕዝቡ ተመዝግበው ዕርዳታ ማግኘት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ዕርዳታ ሰጭዎችም ከደከሙ አይቀር ሕዝቡ አያመሰግንም ብለው በተሳሳተ መረጃ ዕርዳታ መስጠት ከማቆማቸው በፊት ያመጡት ቁሳቁስ በሚገባ ለነዋሪው መድረሱን ቢከታተሉ መልካም ነው ብለዋል።
የአጣዬ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ተመስገን አደፍረስ የነዋሪዎች ቅሬታ በዚህ ሳምንት የተጀመረውን የእርዳታ ስርጭት አያካትትም ያሉ ሲሆን፣ ከኅዳር ወር በፊት በነበረው ላይ ከሆነ፣ አመራሩ የማህበረሰቡን ጥያቄ በመነሻነት በመያዝና ግምገማ በማካሄድ በቀጣይ የሥርጭት ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ተስማምቶ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት።
የሚቀርበው ዕርዳታ ካለው ተረጅ ቁጥር አንጻር በጣም ውስን መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው፣ ዕርዳታውም የተሟላ ስለማይሆን፣ ስንዴ ይመጣና ከስንዴ ጋር መቅረብ ያለባቸው ተጓዳኝ ነገሮች ስለማይኖሩ በሥርጭቱ ላይ ችግር መፍጠሩን ይገልጻሉ። ማኅበረሰቡ ያላግባብ የመጠቀም ፍላጎት አለው ካሉ በኋላ፣ አመራሩም ለተጎጅዎች ከማድረስ ይልቅ ወደ ግል ፍላጎት የማዘንበል ችግር እንደታየበት ሳያነሱ አላለፉም።
የሚመጣው የዕርዳታ ቁሳቁስ በማታ እየወጣ በድብቅ ይሸጣል የሚለውን የነዋሪዎችን ቅሬታ በተመለከተም ምክትል ኃላፊው ሲናገሩ፣ በቆላ ስንዴ ለምግብነት ስላልተለመደ ሰው ለነጋዴዎች ይሸጠዋል፣ በዚህም ከማኅበረሱ የገዙትን ስንዴ ጭነው ለመውጣት የሞከሩ ነጋዴዎች በሌሊት ኬላ ላይ ተይዘው ነበር ። ማህበረሰቡም እኛን የሚወቅሰው ይህን አይቶ በተሳሳተ መረጃ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014



