ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከታወቀ ከሣምንታት በኋላ አሳሳቢነቱ መጨመሩ እየተነገረ ነው። ባለፉት ሣምንታት ከዴልታ ዝርያ ያን ያህል የከፋ አይሆንም ብለው በመናገር የዘርፉ ምሁራንም ሆኑ ፖለቲከኞች እየተሠሰተ የነበረውን አላስፈላጊ ሥጋትና መረበሽ ለመቀነስ ሲጥሩ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን፣ አዲሱ ዝርያ ያስከተለው ለውጥ ገሃድ እየወጣ ሲመጣ አደገኛነቱንም ሆነ ሥጋቱን መደበቁ እንደማያዋጣ የተረዱት ይመስላል።
አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ከ እስካሁኖቹ የባሰ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር ስለሌለ አገራትም ሆኑ ሕብረተሰቡ ሳይሸበር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሕይወቱን እንዲቀጥል ሲመከር ነበር። አላስፈላጊ ዕገዳዎች እንዲቆሙ ሲባልም ዝርያው በስድስቱም ክፍለ-ዓለማት መከሠቱን በማስረዳት ከእንግዲህ ወደእኛ እንዳይገባ ብሎ እንቅስቃሴን ማገዱ እንደማያዋጣ ተነግሯል። ይህ ቢሆንም ግን፣ ለምሳሌ ቻይና ከግማሽ ሚሊየን የሚልቁ ቫይረሱ በማኅበረሰባቸው ውስጥ የገባባቸውን ዜጎቿን ወሸባ ውስጥ መክተቷ ተሰምቷል። የመጀመሪያውን ዙር ወረርሽኝ በዚህ ዓይነት መንገድ በጥሩ ሁኔታ የተወጣችው ቻይና፣ አሁንም ከሌላው በተሻለ ልትቋቋመው ትችላለች ቢባልም ውጤታማነቱን እናያለን በሚል ሒደቱን በጥርጣሬም ያዩት መኖራቸው ተጠቁሟል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ፣ አዲሱን ዝርያ አገራቸው እንዳይገባ ለማገድ በአገራት የሚደረጉ ክልከላዎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ እንደማያዋጡ ነው። ከሳምንት በፊት ወደ 70 የሚሆኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባሉ አገሮች አዲሱ ዝርያ ስለተገኘ፣ እንደአዲስ ኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ ኑሮ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ዕርምጃዎች በተናጥል መወሰዳቸው ውጤታማነቱ አጠራጣሪ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል፣ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከተለመዱትም ሆነ ዴልታ ከተባለውና ይበልጥ ተላላፊ እንደሆነ ይገመት ከነበረው ዝርያ የበለጠ ተስፋፊ መሆኑ በጊዜያዊ ጥናቶች መረጋገጡ ታውቋል። በምን ያህል ብሎ እርግጠኛ አኃዝን ለማስቀመጥ ከጊዜውና ከተወሰደው የጥናቱ ናሙና ውስንነት አኳያ ባይቻልም፣ ከዴልታ ዝርያ ይበልጥ ተስፋፊ ነው ተብሏል። የሥርጭት ፍጥነቱ ብቻ ሳይሆን፣ የጉዳት መጠኑም ከፍተኛ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በበሽታው የተያዘ ሰው የሚያሳየው ምልክት ግን አነስተኛ ነው የተባለ ሲሆን፣ የክትባትንም ውጤታማነት ይበልጥ የሚቀንስ መሆኑ እንደታወቀ ‹ሚንት› የተሰኘው ድረ-ገጽ የዓለም ጤና ድርጅትን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል።
የአዲሱ ዝርያ የሥርጭት ፍጥነት ከቀደሙት ዓይነቶች ይበልጥ ወይም ይነስ ገና አልታወቀም የተባለው አሁን ተቀይሯል የተባለ ሲሆን፣ በተለይ ከዴልታ ዝርያ አስጊነቱ አይበልጥም ተብሎ የነበረው መረጃ ተቀይሯል። የኦሚክሮን የሥርጭት መጠን ቢያንስ አንድ ነጥብ አምስት ጊዜ ከዴልታ ይበልጣል ተብሏል። ይህ ግኝት ግን ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ ሳይሆን አነስተኛ ቁጥር ያለው ናሙና በአጭር ጊዜ ተወስዶ የተሠራ በመሆኑ ያን ያህል አስተማማኝ አይደለም መባሉንም ‹ዳውን ቱ ኧርዝ› የዓለም ጤና ድርጅትን ጠቅሶ ዘግቧል።
በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ወራት ውስጥ ኦሚክሮን ዋናው የኮቪድ 19 ዝርያ በመሆን በተለይ አውሮፓን በመሳሰሉ አገራት ይበልጥ ሊስፋፋ እንደሚችል ተገምቷል። በአፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ቢያሻቅብም፣ የሚሞቱ ሰዎች አኃዝ ግን አሽቆልቁሏል ተብሏል። በደቡብ አፍሪካ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ በአዲሱ ዝርያ ተጠቅተው ሆስፒታል የሚገቡት ቁጥር በ82 በመቶ ጨምሮ እንደነበር ተመዝግቧል። የሚመረመመረው ቁጥር ያን ያህል ጭማሪ ባያሳይም፣ አዲሱ ዝርያ ከተገኘ በኋላ ባለውና አሁን ባለንበት የፈረንጆቹ ወር መጀመሪያ ሰሞን ቁጥሩ ይበልጥ ጨምሮ እንደነበር ተጠቅሷል። ይህ ቢሆንም ምን ያህሉ በአዲሱ ዝርያ ተጠቅተው ሆስፒታል እንደገቡ ስላልተለየ የበለጠ ጥናት የሚፈልግ እንደሆነ ተነግሯል። የሥርጭት መጠኑም ሆነ ጎጂነቱ ከ እስከ አሁኖቹ ዝርያዎች ሊከፋ እንደሚችል እስካሁን ያሉ ጠቋሚዎች ያመለክታሉ በመባሉ ብቻ ሕብረተሰቡ ሳይሸበር የሚጠበቅበትን ጥንቃቄ ከማድረግ መዘናጋት እንደሌለበት ተጠቁሟል።
ወረርሽኝና ድኅነት
በዓለማችን ከተከሰተ ኹለት ዓመትን ያስቆጠረው የኮሮና ቫይረስ ወረርስኝ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንዲሞቱ፣ በርካቶች ሕይወታቸው እንዲመሰቃቀል ከማድረጉ ባሻገር፣ አያሌዎችን ከሥራ ገበታቸው አፈናቅሎ ለድኅነትና ለተረጂነት እንዳጋለጠ ይታወቃል። የዓለም ጤና ድርጅት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ባወጡት መረጃ ከኮቪድ ጋር በተገናኘ ከ500 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፍተኛ ድኅነት ተጋልጠዋል።
ለኹለት አስርት ዓመታት የዓለማችንን ነዋሪ ጤና አጠባበቅ ለማሻሻል ሲሠራ የነበረውንም ወረርሽኙ ገደል ከቶታል ያሉት እነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አገራትም ሆኑ ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወሰዱት ዕርምጃ ከፍተኛ ወጪ በመውጣቱ ባለፉት ኹለት ዓመታት ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ሕዝቦች ከፍተኛ ለሆነ ድኅነት እንደተዳረጉ ታውቋል።
በተለይ በድኃ አገራት ያሉ የጤና ተቋማት ከአቅማቸው በላይ እንዲለጠጡና እንዲዳከሙ ወረርሽኙ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ተነግሯል። በዚህም ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይካሄዱ የነበሩ የተለመዱ ክትባቶች ሥርጭት ከባለፈው ዐሥር ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁጥሩ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሳንባ ነቀርሳና በወባ የሚሞተው ሰው ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲጨምር ወረርሽኙ ምክንያት መሆኑ ተመዝግቧል። የበርካታ አገራት የጤና ተቋማት በቫይረሱ ከተጠቁ በስተቀር የማያስተናግዱበት ወቅት ስለነበር በሌሎች በሽታዎች ተጠቅተው የሚሞቱት ቁጥር ለመጨመሩ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።
ላለፉት ኹለት ዓመታት እየተቀዛቀዘና እየጨመረ የቆየው ወረርሽኙ ከሁሉም በላይ በዓለማችን ላይ ያስከተለው የኢኮኖሚ ድቀት፣ በፈረንጆቹ 1930ዎቹ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተከስቶ ከነበረው የኢኮኖሚ መኮማተር ወዲህ ከፍተኛው እንደሆነ ተጠቁሟል። ይህ ሁኔታ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍል መድኃኒት ገዝቶ መጠቀምን እንደቅንጦት እንዲያየው አድርጓል። መታከምን ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ለጤና መድኅን የሚከፈለውን ወጪውንም ለመሸፈን አስቸጋሪ እንደሆነበት በጥናት መረጋገጡ ተጠቁሟል።
ከፍተኛ ለሆነ ድኅነት እየተጋለጠ ያለው ማኅበረሰብ እየበዛ እንዳይቀጥል መንግሥታት ከፍተኛ የሆነ በጄት በመመደብ ዘርፉን መታደግ እንደሚገባቸውና የሕረተሰቡም ተስፋ መልሶ እንዲለመልም ኹሉም መረባረብ እንደሚጠበቅበት ድርጅቶቹ ወረርሽኙን አስመልክቶ ያወጡትን ሪፖርት ተመርኩዞ ጥሪ ቀርቧል። አፍሪካን የመሳሰሉ አገራት ድኅነታቸው ይበልጥ እየጨመረ እንዲቀጥል ወረርሽኙ ያደረገውን አስተዋጽኦ በአኃዝ ማስቀመጥ ባይቻልም፣ ቀደም ተብሎ ተሠግቶ እንደነበረው ከፍተኛ ጉዳት አያስከትልም ብሎ የአሁኑን የአዲሱን ዝርያ ማዕበል በመዘናጋት መጠበቁ ተገቢ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።
የወረርሽኙ ክትባትና የምሥክር ወረቀቱ ውጤታማነት
ለበርካታ ወራት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ቀድሞ ለማግኘት በአገራት መካከል ፉክክር ፈጥሮ የነበረው የክትባቱ ሥርጭት አሁን መቀዛቀዝ እየታየበት እንደሆነ የሚያመላክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛል። ከአሉባልታም ሆነ ከዕምነት ጋር በተገናኘ አንከተብም የሚሉ እየበዙ በመምጣታቸው ክትባቱ ተገኝቶ የሚከተብ እንዳጡ የሚናገሩ አገራት እየበዙም መጥተዋል። አፍሪካን በተመለከተ፣ ፈላጊው በበቂ መጠን ባላገኘበትና ከ10 በመቶ በታች የሕብረተሰቡ ክፍል ብቻ ስለተከተበ፣ በግድ ተከተቡ የሚል ማስፈራሪያም ሆነ ቅጣት በአህጉሪቱ ስለመታወጁ የተሠማ ነገር የለም።
በምዕራባውያን፣ በተለይ በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ፣ ከክትባት ጋር በተገናኘ ውዝግቡ እየበረታ ለአመጽና ለረብሻም ምክንያት እየሆነ ነው። አንከተብም በሚሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችና መከተብ አለባችሁ በሚሉ መንግሥታት መካከል ልዩነቱ እየሠፋ መምጣቱ መነጋገሪያ ሆኗል። ሕፃናት ይከተቡ አይከተቡ ከሚለው ጀምሮ፣ ያልተከተቡ ሊታገዱ የሚችሉት ከምንና ምን መብቶችና አገልግሎቶች ነው በሚል ውዝግቡ እየተካረረ እንደመጣ እየተዘገበ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በርካታ አገራት ያልተከተበ እንዳይጓጓዝ፣ መስተንግዶ እንዳያገኝና የመሳሰሉ ዓይነት መመሪያዎችን በማውጣታቸው የሚከተበው ሰው ቁጥር መጨመሩን የሚያረጋግጥ ጥናት ይፋ ሁኗል። ‹ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ› በድረ-ገጹ ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ ስለመከተባችሁ የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት አሳዩ እየተባሉ ሰዎች ማስረጃ መጠየቃቸው የሚከተቡ ሰዎችን ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። ግኝቱ በ6 አገራት በተደረገ የናሙና ጥናት ላይ የተመረኮዘ ሲሆን፣ እንደአገራቱ የተከታቢ ቁጥርና ዕድሜ ይለያያል ተብሏል።
የምሥክር ወረቀት ማሳየትን አስገዳጅ የሚያደርጉ ሕጎች ከመውጣታቸው ከ20 ቀናት በፊት የነበረ ሒደትንና መመሪያዎቹ ከወጡ 40 ቀናት በኋላ ያለውን የተከታቢ ቁጥር በማነጻጸር ይበልጥ ወጣቶች ሊከተቡ እንደቻሉ ታውቋል። ይህ መንገድ ሕብረተሰቡ እንዲከተብ ሊያበረታታ ይችል ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ እንዲከተቡ ማድረግ ላያስችል ይችላል መባሉም ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል፣ ምሥክር ወረቀት እያሳያችሁ ካልሆነ የሙዚቃ ዝግጅቶችን (ኮንሰርት) መከታተልም ሆነ ምግብ ቤት መገልግል አትችሉም፣ እንዲሁም የሕዝብ አገልግሎት መስጫ የሆኑ መጓጓዣዎችንም አትጠቀሙም መባሉ የተጭበረበሩ ሠነዶች ሥርጭትን እንደጨምር ማድረጉን ከዚህ ቀደም በነበረ ዕትማችን በዝርዝር አቅርበንላችሁ ነበር። ይህን መሰል የሐሰት ምሥክር ወረቀትን ሥርጭት ለመገደብ አገራት የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰድ የጀመሩ ሲሆን፣ እንግሊዝም ሒደቱን ለመቆጣጠር ሲያጭበረብር የተገኘ ሰው 10 ሺሕ ፓውንድ ሊቀጣ እንደሚችል አሳውቃለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014



