ዳሰሰ ዘ ማለዳ የካቲት (2/2012)

Views: 512

በጋምቤላ ክልል ለሶስት ወራት የሚቆይ የስራ ሰዓት ለውጥ ተደረገ

በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ መደረጉን የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ገለጸ። በክልሉ የሙቀቱ መጨመር ለስራ ምቹ ባለመሆኑ ከየካቲት 1/2012 ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የስራ ሰዓት ለውጥ ተደርጓል። በዚህም መሠረት የመደበኛው የስራ ሰዓት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል የነበረው ከአንድ ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ተኩል መሆኑም ተነግሯል። ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ 11 ተኩል የነበረው ከአስር ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል  እንዲሆን መወሰኑን ምክር ቤቱ በመግለጫ አመላክቷል። በአሁኑ ወቅት የክልሉ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ39 እስክ 40 ነጥብ 4 ድግሪ ሴሊሺየስ መሆኑን  በብሄራዊ ሜቲዎሎጂ ኤጀንሲ የጋምቤላ ክልል አገልግሎት ማዕከል ዳሬክተር  ሙሴ ትዛዙ  ገልጸዋል። የለሊቱ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ደግሞ ከ21 እስከ 23 ድግሪ ሴሊሺየስ መሆኑንም ጠቅሰዋል።(ኢዜአ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የምፅዋና የአሰብ ወደቦች የሚሰጡትን አገልግሎት የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የኤርትራው  ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ተናገሩ። በአገሪቷ ውስጣዊ ጉዳዮች በተያያዘ ከመንግስት መገናኛ ብዙኃን  ጋር  ቆይታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ከሆነም የነዚህን ወደቦችን አገልግሎት ውጤታማነት ለመጨመር የማደስ፣ የማስፋትና የማሳደግ ስራዎች ለማከናወን እቅድ መያዙን ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።(ቢቢሲ አማርኛ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም በመጪው ሐሙስ የካቲት 5/2012 በተለያየ የፖለቲካ አቋማቸው በሚታወቁ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች መካከል በዲሞክራሲያዊ ሽግግር ፣በሠላም እና መረጋጋት ዙሪያ ውይይት ሊካሄድ ነው፡፡ በውይይቱም ልደቱ አያሌው ከኢዴፓ፣ጃዋር መሀመድ ከኦፌኮ፣አንዱዓለም አራጌ ከኢዜማ፣ጌታቸው ረዳ ከኅውሃት እና ደሳለኛ ጫኔ (ዶ/ር) ከዐብን ናቸው፡፡ አንድ ተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በዝርዝሩ ሊካተቱ እንደሚችሉም ተጠቅሷል፡፡(አዲሰ ማለዳ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ኢትዮጵያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የነፃ ቪዛ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ስምምነቱን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ  ሂሩት ዘመነ እና የኢኳቶሪያል ጊኒው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሞን ኦዮኖ እንደተፈራረሙ ተነግሯል። ከስምምነቱ በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ የአገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮችና ከዚህ በፊት የተፈረሙ ስምምነቶች አፈጻጸም በተመለከተ መምከራቸው ታውቋል። (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትንስፖርት አገልግሎት ከ96 ሺህ  ብር በላይ  የሚገመት አደጋ ከሀምሌ እስከ ታህሳስ ባሉት ስድስት ወራት አደጋ  እንደገጠመው ተገለጸ፡፡ በአምስት ባቡር ላይ በደረሰ የመኪና ግጭት እና በአጥር ላይ በደረሰ 36 አደጋ 96 ሺህ 250 ብር፤ እንዲሁም በኬብል ስርቆት ስልሳ ሺህ ብር የሚገመት ጉዳት እንዳጋጠመው ተገልጿል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ እና የሰዎችን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማሳደግ ከሞያሌ በተጨማሪ በማርሳቢት አካባቢ ተጨማሪ የመገበያያ ስፍራ ለመክፈት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡በማርሳቢት ግዛት አስተዳደር ጥያቄ እና ድጋፍ የሚቋቋመው የመገበያያ ስፍራ በሽታዎችን እና በአካባቢው ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሏል። በድንበር ከሚዋሰኑ አገራት ጋር 26 የመገበያያ ስፍራዎችን ለመክፈት እቅድ መኖሩን እና  ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኗቸው የድንበር አካባቢዎች እንደሚከፈቱ የኬንያ ድንበር አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኬንደይ ንያዮ ገልፀዋል።( ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የገቢዎች ሚኒስቴር ከየካቲት 01/2012 ጀምሮ የስራ ሰዓት መግበያና መውጫ ያሻሻለ ሲሆን ከሰኞ እስካ አርብ  ከጠዋቱ 2፡00 እስከ 6፡00 መደበኛ የሥራ ሰዓት ሲሆን ከ6፡00 እስከ 7፡00 የምሳ እረፍት መሆኑን አስታውቋል፡፡ዘወትር አርብ ደግሞ ከጠዋቱ 2፡00 እስከ 5፡00  የሥራ ሰዓት ሲሆን ከ5፡00 እስከ 7፡00 የምሳ ሰዓት ነው፡፡ ከሰዓት በኃላ  ከ7፡00 እስከ  11፡00 መደበኛ የሥራ ሰዓት መሆኑንም ይፋ አደርጓል፡፡ ቅዳሜ ጠዋት ከ2፡00 እስከ  6፡00 ሰዓት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መደበኛ የሥራ ሰዓት መግቢያና መውጫ መሆኑን አመላክቷል (የገቢዎች ሚኒስቴር)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ በያዝነው የካቲት  ወር ዕረፍት ላይ እንሚሆን ተገለጸ፡፡ በዚሁ መሠረት አምስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሰራ ዘመኑ ከየካቲት 1/2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 30/2012 ዓ.ም ድረስ በዕረፍት ላይ እንደሚሆን ታውቋል፡፡(የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com