“የፋይናንስም ሆኑ የንግድ ሕጎች ከወቅቱ ጦርነት ጋር በሚሔድ መልኩ መሻሻል አለባቸው”

0
930

አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) ይባላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በወጣትነታቸው ሕንድ አገር በባህር መሐንዲስነት (ማሪን ኢንጅነርነት) ሠልጥነው ለተወሰኑ ዓመታት አገራቸውን በመርከበኛነት ያገለገሉት እኚህ ምሁር፣ በምጣኔ ሐብት ዘርፍ ተምረው ከ1998 ጀምሮ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሦስቱንም ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ያገኙት እኚህ የዩኒቨርስቲ መምህር፣ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀትና በማማከር፣ እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ዕውቀታቸውን በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ ስለወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ እንዲሁም ጦርነቱ እያስከተለ ስላለው የምጣኔ ሐብት ጉዳት ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ኹኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ኹኔታ እንደአንድ ዜጋ ሳየው በጣም ኃይለኛ ነውጥ የነበረበት፣ ያለበትና ወደመረጋጋት የሚኬድበት ወቅት ላይ ያለን ይመስላል። አሁን ኃይለኛ የውስጥ ነውጥና የውጭ አፈና የሚካሄድበት ጊዜ ነው። በዚህ ምክንያትና ያለው የፖለቲካ ኹኔታ ኢኮኖሚው ላይ ብዙ ጉዳት በማድረሱ ኢኮኖሚው ችግር ላይ ይገኛል። ቀደም ብሎም ችግር ላይ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በጦርነቱ የተነሳ ብዙ ጉዳት ደርሶበታል። ኹኔታውን ለማስተካከል ብዙ ጥረትና ልፋት ከጥሩ አመራር ጋር ይፈልጋል። የፖለቲካውን ኹኔታ በሚገባ ማሻሻል ይፈልጋል። ጥሩ ፖለቲካ ከሌለ ጥሩ ኢኮኖሚ ሊኖር አይችልም። ጥሩ ፖለቲካ ከሌለ እንዳየነው የተገኘችዋን ትንሽ ዕድገት እንኳን ይቀለብሰዋል። ስለዚህ የፖለቲካ መስተካከል ዋናው ነገር ነው። መንግሥት ማሰብ ያለበት ትልቁ ነገር ረዘም ላለ ጊዜ ካለው የአገሪቱ ጥቅም አንጻር ቅድሚያ ማስተካከል ያለበት ፖለቲካውን ነው።

አሁን ያለው ፖለቲካ በጣም የተበላሸ ነው። አብራችሁ አትኑሩ የሚል ፖለቲካ፤ በአገር አንድነት ላይ የማያምን ፖለቲካ በጣም በብዛት አገሪቱ ላይ አለ። ይህ ዓይነት ፖለቲካ በብዙ ፓርቲዎች የሚቀነቀን ነው። ኹላችንንም የሚያገናኘን አንድ ነገር ቢኖር ግለኞች መሆናችን ነው እንጂ፣ በብዙ ነገር እንለያያለን። በተፈጥሮም ሆነ በአስተሳሰብ እንለያያለን። ይህ ቢሆንም አስተሳስሮ የሚይዘን ዋናው ነገር የአንድ አገር ዜጎች ኢትዮጵያዊ መሆናችን ነው። ይህን አንድነታችንን የሚያጠናክርልንን በማጉላት ፈንታ፣ ከሕገ-መንግሥት አንስቶ ፖለተከኞቹ የሚለያየን ላይ ያተኩራሉ። በተለይ ቀደም ብለው በሥልጣን ላይ የነበሩት ፖለቲከኞቻችን የሚያስቡ የነበረው እንደአገር በማይጠቅመን ላይ ነበር። ሕገ-መንግሥቱን ጨምሮ አተገባበሩ የተለያዩ ዜጎች እርስበርስ ተፋጠው እንዲኖሩ የሚያደርግ በመሆኑ መስተካከል ያለበት ነው። እንደእውነቱ ወደ ጥሩና የተሻለ የኢኮኖሚ ኹኔታ እንምጣ ካሉ መጀመሪያ ማስተካከል ያለባቸው የአንድ አገር ዜግነትን በትክክል የማይቀበል ሕገ-መንግሥት ነው። የተለያዩ ዜጎች መጥተው አገሪቷን እንደሠሯት የሚያስመስለው ይህ ሕገ-መንግሥትና አስተሳሰቡ መወገድ ይኖርበታል። ፖለቲካው ሲስተካከል ኢኮኖሚውም እንደልብ ተንቀሳቅሶ ይስተካከላል። ለምሳሌ፣ ሰዎች አሁን እንደልብ መሥራት አይችሉም። ጥሩ ፖለቲካ ቢኖር እንደልብ የትም ሔደው መሥራት ይችላሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የሠሩትም አይበላሽም፤ አይደመሰስም፤ አይቃጠልም፤ አይዘረፍም። ኢኮኖሚውን በዋናነት ያበላሸው ጥሩ የፖለቲካ ኹኔታ አለመኖሩ ነው። የሰው ጉልበትም ሆነ ዕውቀት፣ እንዲሁም ካፒታል እንደልብ ተንቀሳቅሶ እንዳይሠራ ፖለቲካው አድርጓል። አሁን ፖለቲካው በተበላሸ ኹኔታ ላይ እንዳለ ነው መታሠብ ያለበት።

አሁን ያለንበት የጦርነት ኢኮኖሚ ነው ሲባል ምን ለማለት ነው?
የጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ ነው ያለነው የሚለው የሚገልጸው ኹለት ዓይነት ነገሮችን ነው። በጦርነት ውስጥ ያለ ኢኮኖሚ ከሚያስተናግዳቸው የመጀመሪያው፣ ኢኮኖሚው ጦርነቱን መደገፍ ይኖርበታል። ይህ ማለት ሥንቅና ትጥቅ፣ ጥይትና መሣሪያ ማቅረብ፣ የሰው ኃይልንም ማጠንከር ይጠበቃል። ጦርነት ሲባል ሀብትና ንብረት እንዲሁም ጉልበት ወደ ጦርሜዳው የሚሄድበት ነው። ከተለመደውና መደበኛ ከሆነው የኢኮኖሚ ኹኔታ ተላቆ መደበኛ ያልሆነ አስቸጋሪ የአደጋ ጊዜ ኹኔታ ነው የሚሆነው። ሀብት መኖር ስላለበት መሠራትም ስላለበት ኢኮኖሚ ከሌለ ጦርነቱን ማካሄድ አይቻልም። ጦርነቱን በድል ለመወጣት ብዙ ሀብትና ኢኮኖሚውን ወስዶ መጠቀም ይጠይቃል፣ ያወድማልም። ከትጥቅና ሥንቅ ዝግጅት ጀምሮ፣ በሰው ኃይልም ተዘጋጅቶ ለመቅረብ ትኩረትን ኹሉ ከመደበኛው ወስዶ ወደ ጦርነቱ ያደርጋል። ጦርነት አገርን ወደ አስቸኳይ ኹኔታ ከመውሰዱ ባሻገር ተንቀሳቅሶ መሥራትም ሆነ መነገድን ይገድባል። በአስፈሪነትም የተነሳ ለጥንቃቄም ሆነ በጦርነቱ ምክንያት ተገደው ሰዎች መደበኛ እንቅስቃሴያቸውን ይገድባሉ።

በውጭ በኩል ደግሞ ከባድ ተጽዕኖ አለ። የውስጥ ተፋላሚዎችን የሚደግፉ አሉ። በአገር ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጁ ኹለት አሸባሪ ቡድኖች አሉ። ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ቢሆኑም፣ ብዙውን ጊዜ ኦነግ ሸኔ እንደሚያጠፋው ብዙ ጥፋት ትኩረት እየተሰጠው አይደለም። ኹለቱ ቡድኖች ከፍተኛ የሆነ የውጭ ድጋፍ እንዳላቸው ይታወቃል። ኢኮኖሚው የውጭ ድጋፍ እንዳይኖርና መከላከል እንዳቻል አስተዋጽዖ አድርጓል። ደጋፊዎቻቸው ከውጭ ኢኮኖሚው ላይ የተለያየ ተጽዕኖ ስለሚያደርሱበት፣ ብድር ማግኘትንም ሆነ መነገድን ስለሚገድቡ በኢኮኖሚው ላይ ጫና ያሳድራል ማለት ነው። የጦርነት ጊዜ ኢኮኖሚ በውስጥም በውጭም አስቸጋሪ ኹኔታዎች ተወጥሮ ያለበት ነው።

የውጭ በተለይም የምዕራባውያን ተጽዕኖ ለወደፊትም የሚቀጥል ይመስሎታል?
ይህ በእኛ ሁኔታ የሚወሰን ነው የሚሆነው። ብዙ ጊዜ እኛ ኢትዮጵያውያን ጋር ያለው ድክመትና ለውጭ ጥቃት የሚያጋልጠን የውስጥ ድክመታችን መሆኑን አለመረዳት ነው። ተባብረን ሳንገኝና የውስጥ ክፍፍል ሲኖር ነው ለእነሱ ጣልቃገብነት የምንጋለጠው። አሁን የውጭ ጠላቶቻችን የውስጦቹን ተመርኩዘው ነው የመጡት። ለምሳሌ፣ ግብጽ ለብዙ ጊዜ በዓባይ የተነሳ ስትራቴጂክ ጠላታችን ሆና ቆይታለች። አሜሪካኖች ደግሞ ኹልጊዜ ጥቅማቸውን ዓይተው የሚለዋወጡ ናቸው። የአገሪቱን ውስጣዊ ኹኔታ ዓይተው የሚደግፉና የሚቃወሙ ናቸው። እነሱ ታዛዥ መንግሥት ይፈልጋሉ። ሕብረተሰቡም ቀና የማይል የእነሱን ጥቅም ብቻ እየጠበቀ የሚኖር እንዲሆን ይፈልጋሉ። ነባር የነበረውን ዘመናዊ ቅኝ ግዛት በመከተል የማስፋፋት ዝንባሌ አላቸው። በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች ላይ ከባድ በደል ሲያደርሱ የኖሩ ናቸው። የእነሱ ማጥቃት አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ኹልጊዜ የሚሞክሩት ውስጣችን መከፋፈል ሲኖር ነው። በአገር ውስጥ ያለው ክፍፍል በቅጡ ስላልተያዘ ነው ለእነሱ ጫና ያጋለጠን። የውስጥ ቅራኔ የሚያዝበት ሁኔታ ትክክል ሣይሆን ሲቀርና መንግሥት የሕዝቡን አንድነት መጠበቅ ሲሳነው ነው ችግር የሚፈጠረው።

አሁንም ቢሆን ከሰሜኑ ጦርነት ውጭ በሌላ በኩል ያለው ችግር ከመንግሥት አቅም ማነስ ወይም ፍላጎት ማጣት የመነጨ ነው። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ችግሮች የአቅም ሳይሆን የፍላጎት ማጣት ነው መስለው የሚታዩት። ለምን ቢባል፣ ያን ያህል ጦርነት ሰሜን እየተካሄደ ትንሽ አቅም አለው የሚባለው ቡድን ትልቅ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ይህ ዓይነት ኹኔታ ውስጥን ይከፋፍላል፤ በአስተሳሰብም ይለያያል። መንግሥት የውስጡን ሁኔታ በደንብ ካልያዘ የውጭ ጣልቃ ገብነትም ይህን አስታኮ የመጨመር ዝንባሌ ይኖረዋል።

ለዜጎች አጥጋቢ ያልሆኑ ዕስራቶችም ሆኑ ክልከላዎች ሰውን ቅር የሚያሰኙ እስከሆኑና አላግባብና ጊዜያቸውን ያልጠበቁ እስከሆኑ ድረስ በዚህ ቀዳዳ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ያስነሳል። ለምሳሌ በጋዜጠኞች ላይና በሌሎች ዜጎች ላይ የሚነሱ የሰብዓዊ መብትን የተመለከቱ ጥያቄዎች በሚፈጥሩት ክፍተት ሰበብ አግኝተው ነው ምዕራባውያን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡት። ጣልቃ ገብነቱ መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች እልባት ለመስጠት ብቃት ሳይኖረው ሲቀር ወይም ሳይፈልግ ከቀረ ነው የሚጨምረው ። የውስጥ አንድነታችን ለመጠበቅ መንግሥት መፍትሄ በቶሎ እየሠጠ ከሔደ አሸናፊ ስለሚሆን አውሮፓውያኑም ሆኑ ሌሎቹ ያሸነፈው ጋር መሔዳቸው አይቀርም። የእነሱ ኹኔታ የሚወሰነው እኛ በጦርሜዳ ላይ ባለን ብርታት ነው።

አንዳንዴ መሃል አገርም አንድነትን የሚበጠብጥ ውሳኔ ሲደረግ እናያለን። ከመሃል ሆኖ የሚበጠብጠውንና የሕዝቡን አንድነት የሚከፋፍለውን መንግሥት መከላከል አለበት። ጦርነቱ ግንባር ላይ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ሆኖ የሚዋጋላቸው መኖሩን መረዳት ያስፈልጋል። አገሬውን በማስቀየም ነገሮችን ለማበላሸት የሚጥሩትን መለየት ያስፈልጋል። በጦር ሜዳም በውስጥም ያለውን መከፋፈል ማስወገድ ከተቻለ ጦርነቱ ረጅም ጊዜ አይወስድም የሚል ዕምነት አለኝ።

ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ካልተቻለ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ያህል ከአሁኑም ይብሳል?
የጦርነቱ መራዘም በጣም ብዙ ነገርን ነው የሚነካው። አንደኛ፣ ጦርነቱን በመሣሪያም ሆነ በትጥቅና ሥንቅ የመደገፉ ኹኔታ ቀላል አይሆንም። ጦርነት ሀብት አውዳሚ ነው። አንድ ጊዜ የሚተኮሰው ጥይትና የሚጣለው ቦንብ በጣም ብዙ ዋጋ ያለው ነው። በአየርም ሆነ በምድር የምንጠቀማቸው ኹሉም የጦር መሣሪያዎች ወጪያቸው ከፍተኛ ነው። በዚህ ምክንያት የሚጎዳው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀላል አይደለም። መራዘሙ ከሚያስከትለው የኢኮኖሚ ጉዳት ባሻገር፣ ጠላት እያገገመ እንዲጠናከር ዕድል ይሰጠዋል። ይህም የራሱ መዘዝ ይኖረዋል። ይህ ሀብትን ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰውንም ወደጦርነቱ ስለሚወስድ ከመደበኛው ወታደር በተጨማሪ የሚዘምተው አምራች የነበረው የሕብረተሰብ ክፍል ማምረቱን ስለሚያቆም ኢኮኖሚው ላይ ጫና ያሳድራል።

በሌላ በኩል፣ የጦርነቱ መራዘም ከሚያስከትለው ቀጥታ ጉዳት በተጨማሪም መሰላቸትን ይፈጥራል። ይህ በተዋጊው ላይ ብቻ ሳይሆን ከኋላ ደጀን ሆኖ ድጋፍ የሚደርገውንም ነው። ስለዚህ ውጤታማ በሆነ መንገድ ጦርነቱን በቶሎ መጨረስ አስፈላጊ መሆኑ ለማንም ግልጽ ይመስለኛል።

በጦርነቱ የወደመውንና የተዘረፈውን ንብረት ወደነበረበት ለመመለስ ምን ያህል ጊዜና አቅም ይፈልጋል ይላሉ?
አንደኛ አውዳሚውንና ዘራፊውን መያዝ ለሀብቱ መመለስ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው። ሌላው ዘራፊው ሲሸሽ ተከትሎ ንብረትን ማስቀረት ነው። ማስጣል የማይቻል ካልሆነ መልሶ እንዳይጠቀምበትና ለአገር ጥፋት እንዳያውለው ማውደም ነው። ከዚህ በተረፈ ይህንን ጥፋት ያስከተለውን በኃላፊነት እንዲመልስ በጉልበት ጭምር መሥራት አለበት። ታጣቂ ቡድኑ የዘረፈው በርካታ ሀብት ሳያንስ ያወደመው ንብረት ብዙ ነው። በጣም የሚያሳፍረው ደግሞ ንብረትን ያበላሹበት አጸያፊ መንገድ ነው። በጣም እርኩስ መሆናቸውን የሚያሳይ አስቀያሚ ድርጊታቸው በጦርነት ውስጥ የትም ሲፈጸም አልሰማሁም። የምግብ ሌማትና መኝታ ላይ የሚጸዳዱ ናቸው። እንደዚህ የፈጸሙና እንዳይመለሱ ተደርገው የወደሙትን ምንም ማድረግ ባይቻልም፣ መመለስ የሚቻለውን ግን ማስመለስ የሚቻለው ጦርነቱ ሲያበቃና እነሱን መያዝ ሲቻል ነው። የብዙ ድኃ ሀብት ስለሆነ የወደመው ንብረት፣ አውድመውታል ተብሎ ዝም ተብሎ መታለፍ የለበትም።

ከጦርነቱ በፊት ወደነበርንበት የኢኮኖሚ ኹኔታ ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ የሚወስድ ይመስሎታል?
ይህ እንደመተባበራችን መጠን የሚወሰን ነው የሚሆነው። ይህን ያህል ዓመት ይፈጃል ብሎ ለማስቀመጥ አይቻልም። ሀብት (ሪሶርስ) ካለ አጭር ጊዜ ነው የሚፈጀው። ዋናው ጥያቄ ሀብቱ ከየት ይመጣል የሚለው ነው። ከአገር ውስጥና ከውጭ ድጋፍ መገንባት ይቻል ይሆናል። ምግብን ራስ ለማምረት ቢያንስ አንድ የአዝመራ ወቅትን ይፈልጋል፤ ይህም ቢሆን አቅም ይጠይቃል። መኖሪያ ቤቱ የፈረሠበት፣ የተቃጠለበትም መልሶ ለመገንባት ጊዜው የሚወሰነው እንዳለው አቅም ነው። እነዚህ ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ብድርን የመሳሰለ ድጋፍ ይፈልጋሉ። የፋይናንስ ድርጅቶችም የሕዝቡን ፍላጎት ለሟሟላት ምን ያህል አቅም አላቸው የሚለው ራሱ አጠያያቂ ነው። የአቅም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡ አመለካከትም የጊዜውን ሁኔታ ይወስነዋል። የሥራ ባህላችን ተቀይሮ ተስፋ ሳይቆረጥ የሚሞከር ከሆነ ቆይታውን ማሳጠር ይቻላል። ትብብሩ ብቻ ሳይሆን ሠላሙም መጠበቅ አለበት። በኹሉም ወገን ያሉ ፖለቲከኞች የሚፈጥሩት የማበጣበጥ ድርጊት ከቀጠለ ኢኮኖሚውን ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆናል። ሠላም ካለ በቀላሉ ይመለሳል የሚል ዕምነት አለኝ።

ብድር ካሉት ጋር በተገናኘ አነስተኛና ጥቃቅን አበዳሪዎች ወደባንክነት እያደጉ በመምጣታቸው፣ እንዲሁም አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በተደጋጋሚ ዕርዱ እየተባሉ አቅማቸው ተዳክሟል መባሉ ምን ያስከትላል?
እኛ አገር ሕግ መሬት ላይ ያለ ዕውነታን ማየት ይሳነዋል። ለሁኔታዎች ተለዋዋጭ የሆኑ ስላልሆኑ ችግርን ማቃለል ይሳናቸዋል። እንዲህ አይነት ነገርን ማስተካከል ያለበት መንግሥት ነው። የፋይናንስ ተቋማት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የብድር አቅርቦት ማመቻቸት አለባቸው። አሰሠራራቸውን ከመደበኛው ሒደት ማሻሻል አለባቸው። አገር ሠላም በነበረ ጊዜ በነበረው አሠራርና ሕግ በጦርነት ወቅት መቀጠል አይቻልም። የፋይናንስም ሆኑ የንግድ ሕጎች ከወቅቱ ጦርነት ጋር በሚሔድ መልኩ መሻሻል አለባቸው። እንቅፋቶች ካሉ ተስተካክለው ለሕብረተሰቡ ፍላጎት ምላሽ መስጠት መቻል አለባቸው። የመንግሥትም ሆኑ የግል ባንኮች ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ አስተዋጽዖ ማድረግ አለባቸው።

በጀትን በተመለከተ የተጎዱ የጦር ቀጠና አካባቢዎች ለጦርነት ያዋሉትን ለማካካስ ሌሎች በልግስና መልክ እየቆነጠሩ መስጠታቸው ያዛልቃል ይላሉ?
በጀትን በተመለከተ፣ አንደኛ ወያኔና ኦነግ ሸኔ ተዋግተው ሰሜን ሸዋ ሲደርሱ የአገር ሀብትን እያበላሹ ነው። ወረራውን አማራና አፋር ክልል ሲዋጉ ጉዳዩ የእነሱ ብቻ አይደለም። ወያኔ መሀል ከተማ ቢመጣ ኑሮ የሚጎዳው ኹሉም የኢትዮጵያ ክፍል ነው። ኦነግ ሸኔም ቢሆን የሚጎዳው ኹሉንም ነው። እንዳጋጣሚ ሆኖ ጦርነቱ የመጣው በሰሜን በኩል ነው። እንደህወሓት ትርክት ዋና ጠላቴ የሚለው አማራውን እንደመሆኑ ለይቶ ሊያጠቃ ይችላል። ነገር ግን፣ ለኦሮሞውም፣ ለጋንቤላውም፣ ለቤኒሻንጉሉም፣ ለሱማሌም የሚቀርለት አልነበረም። ስለዚህ ኹለቱ ክልሎች የአገሪቱን ሸክም ነው የተሸከሙት። ስለዚህ ውድመቱ የእነሱ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ እንደማይታይ ተስፋ አድርጋለሁ።

ሌሎች ክልሎች በጀታቸውን ለልማት እየተጠቀሙና አዳዲስ በጄቶችን እየጠበቁ ሲሄዱ፣ ኹለቱ ክልሎች ደግሞ ያላቸውን ሙሉለሙሉ ለጦርነቱ ማዋላቸው ፍትሐዊ አይሆንም። አንደኛ እንደአንድ አገር ዜግነትም ቢሆን የጠፋው የአገር ሀብት እንደመሆኑ ኹሉም ማካካስ ያለበት ይመስለኛል። ሀብት የወደመባቸው አካባቢዎች በጄታቸውን ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ያጡት፣ ለዓመታት በበጄታቸው ገንብተው ያስቀመጡትንና ያለሙትን ጭምር ነው። ክልሎች በሥርዓት የጠፋውን ለማካካስ ዝግጁ መሆን የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ጉዳዩ የእነሱ ብቻ ተደርጎ ከታየ ሁኔታው ከአጥፊዎቹ ካላቸው የማድህየት ሀሳብ ተለይቶ የሚታይ አይሆንም።

የጦርነቱ ዓላማ ለማደህየት ነው የሚሉ አካላት እንደመኖራቸው አሁን የተከሰተው የኑሮ ውድነት እንደተሳካላቸው የሚያሳይ ነው? በቀጣይስ ምን ያስከትላል?
በጦርነት ሀብት ነው የሚጠፋው። ሠላም ሲጠፋ አቅርቦት ይጠፋል። ፍላጎት እንደነበረ ስለሚቆይ የዋጋ ንረት ማስከተሉ አይቀርም። በጦርነት ጊዜም ሰዎች ግዴታ መብላት መልበስ ይኖርባቸዋል። መደበኛ አቅርቦቶች ለጦርነት ሲውሉ ዕጥረት ይገጥማል። ጦርነቱ መሠረተ ልማቶችንም ከማጥፋቱ ባሻገር የሚወስዳቸው አቅርቦቶች መኖራቸው የራሱን አስተዋጽዖ ያደርጋል። ዕጥረት ሲኖር ደግሞ የዋጋ መወደድ የተለመደ ነው። ይህ ጉዳት እንደሚኖረው ይታወቃል። ነገር ግን፣ የኹላችንንም አመለካከት መቀየር ከተቻለ ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል።
ጦርነቱን ተጠቅመን የሕዝቡን ችግር እንጠቀምበት የሚሉ ስግብግብ ነጋዴዎች እንደሚኖሩ ይታወቃል። አብዛኛው ዋጋ ስለሚጨምርብት የሚጨምር ቢሆንም፣ በዚህ ጊዜ ኹሉም በመተሳሰብ ሊያሳልፈው ይገባል። ኹሉም በየበኩሉ የሞራል ግዴታውን መወጣት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ መስጠቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኹሉ፣ በተጎዳ ሕዝብና አገር ላይ አትርፈን አላግባብ እንበልጽግበት የሚል አስተሳሰብ ሊኖር አይገባም። ከተሳሰብን ችግሩን እያለዘብነው ጥሩ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ተቻችለን መቆየት ይቻላል።

አሁን ያለውን ኢኮኖሚ ከበለጠ ጉዳት ለመታደግ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የማሻሻያ ሥራ መሥራት ያለበት ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ነው ወይስ ማይክሮው ላይ ነው ማተኮር ያለበት?
እንደእውነቱ ከሆነ እስከአሁን ድረስ የእኛ አገር የአፈጻጸም ችግር በጣም ከፍተኛ ነው። ምንአልባት አሁን የተፈጠረው ኹኔታ ነግሮን የአፈጻጸም ችግራችንን የማሻሻል ዝንባሌ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ። በነበረው ልምድ ግን እንኳን ለጊዜው የሚመጥኑ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ማቅረብ ይቅርና፣ የነበሩትንም በትክክል የመፈጸም ችግር አለብን። ማይክሮም ሆነ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በትክክል በጊዜያቸው ሲተገበሩ አናይም። አሁን በተፈጠረው ንዝረት መንግሥት ጥሩ አፈጻጸም ወደ መስጠት ከሔደ ጥሩ ይሆናል። ከመንግሥት የሚጠበቀው ነገር ሜዳውን ማስተካከል ነው። ደንቡ፣ አሠራሩና ሕጉ ጥሩ ከሆነ ሰዎች መሠራት ያለበትን ራሳቸው ይሠሩታል። በመንግሥት በኩል መሥራትና መለወጥ የሚችሉ ሰዎችን መመደቡ ላይ ያለ ችግር ተቀርፎ እንደሚስተካከል ተስፋ አድርጋለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here