ከፍታ ከንባብ ጋር

በየሳምንቱ እለተ አርብ ማምሻ ላይ ሰብሰብ ይላሉ። መሰባሰቢያ ስፍራቸው በአዲስ አበባ ሃያ ኹለት አካባቢ፣ ጎልጉል አጠገብ ከሚገኘው ታውን ስኩዌር ሞል ላይ ነው። በዚህ ሕንጻ ላይ ከፍታ የሥልጠና እና ማማከር አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቢሮ ይገኛል። ታድያ አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ሰብሰብ የሚሉት ሰዎች በተመረጡ መጻሕፍት ዙሪያ ውይይት ለማድረግ በየሳምንቱ አርብ የተቃጠሩ አንባብያንና አንባብያት ናቸው።

አዶስ ማለዳ እንዲህ ካለው መርሃ ግብር በአንዱ የመሳተፍ እድል አግኝታ ነበር። የአባላቱን ቆይታና የመጽሐፍ ላይ ውይይት ድባብም ታዝባለች። በዚህ እለት በተመረጠው መጽሐፍ ላይ ውይይት ለማድረግ የተገኙት ስምንት የመጽሐፉ ክበብ አባላት ሲሆኑ የተመረጠው ደግሞ 92 ገጾች ያሉት፣ በናትናኤል ብራንደን የተጻፈውና በ1992 ለህትመት የበቃው ‹ዘ ፓወር ኦፍ ሰልፍ እስቲም› የተሰኘው መጽሐፍ ነው።

በቆይታቸው መግቢያ ላይ የእለቱ አንባቢና አቅራቢ ሠላሳ ደቂቃዎችን ወስደው ስለመጽሐፉ አጠር ያለ ትንታኔ ሰጡ። ቀጥሎም ተሳታፊዎች በየተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የየራሳቸውን ዕይታ፣ የተገነዘቡትን እና የተረዱበትን አንጻር አካፈሉ። በነጻነት በሚያንሸራሽሩት ሐሳብ መካከል ሻይ ቡና እየተቋደሱ ሰዓቱ ገፍቶ ምሽት ኹለት ሰዓት ሆነ። ለቀጣይ አርብ ተመሳሳይ ኹናቴ ግን በተለየ መጽሐፍ ላይ ውይይት ለማድረግ ተቃጥረው ተለያዩ።

ይህን መሰናዶ የሚያዘጋጀው ከፍታ የሥልጠና እና የማማከር አገልገሎት ነው። ድርጅቱ ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ተቋማትን ያማክራል፤ የጋዜጠኝነትን ጨምሮ የተለያዩ የሥነ ልቦና ሥልጠናዎችን ይሰጣል። ይህ የመጽሐፍ ላይ ውይይትም ከድርጅቱ ሥራዎች መካከል አንደኛው እንደሆነ ነው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ታጠቅ ጌታቸው የነገሩን።

የንባብ ክበብ
ዛሬ ላይ በብዙ የምናከብራቸው፣ የመጻሕፍት ሥራዎቻቸውን አድንቀን የማንጠግባቸው ደራሲያንና ደራሲያት የንባብ ክበብ ውጤቶች መሆናቸውን በተለያየ ጊዜ እንሰማለን። አንድ ብለው ማንበብ የጀመሩ ሰዎች እንዲበረቱ፣ ያነበቡትን በተለያየ አንጻር ተረድተው በሕይወት እንዲጠቀሙበት አልያም ለእውቀት ግብዓት እንዲያውሉት የንባብ ክበባት ትልቅ ሚና አላቸው። ከዚህ ሲሻገርና ከፍ ሲል ደግሞ ጸሐፊና ደራሲን በንባብ ክበባት ይፈጠራሉ።

አሁን ላይም በርካታ የንባብ ክበባት አሉ። አንድም ኹለትም ሆነው፣ ከፍ ሲል አዳራሽ ሞልተው የሚካሄዱ የመጻሕፍት ላይ ውይይትም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እስኪደነቃቀፉ ድረስ በአዲስ አበባ በብዛት ይስተዋሉ ነበር። አሁንም ይገኛሉ። ከነዛ መካከል ነው፤ ይህ ዛሬ ያሳነው በከፍታ ሥልጠና እና ማማከር አገልግሎት ስር የሚገኘው የንባብ ክበባት እንቅስቃሴ ጉዳይ።

ከፍታ የሥልጠና እና ማማከር አገልግሎት በንባብ የሚገኝን ልምድና ከፍታ ባለርዕይ ከመሆን ጋር እንደሚያዛምደው ነው ታጠቅ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት። ድርጅቱም ‹‹ማንም ሰው በርዕዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ካስፈለገ መጽሐፍ ማንበብ አለበት።›› የሚል መነሻ ነጥብ ይዞ እንደተነሳ ነው የነገሩን።

ሰዎች አስተሳሰባቸው ካለተቀየረ ኑሯቸውን መቀየር ይከብዳቸዋል ወይም አይችሉም። በዚህም የተነሳ የሰዎች አስተሳሰብ ላይ መሥራት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ። ‹‹በዓመት ውስጥ ኹለት ወይም ሦስት ጊዜ በሚሰጥ ሥልጠና የሰዎችን ሕይወት መለወጥ ስለማይቻል፣ በቋሚነት ለመሥራት እንዲሁም በርካታ አንባቢዎችን ለማፍራት እንዲያስችል ይህንን ክበብ ማቋቋም መፈትሔ ሆኖ አግኝተውታል።›› ሲሉ ታጠቅ ተናግረዋል።

ገና በጅማሬ ላይ የሚገኘው ክበቡ አሁን ላይ በሳምንት ለሦስት ቀናት ማለትም ረቡዕ፣ ሐሙስ እና አርብ ላይ የተለያ አንባብያንን ያሰባስባል፤ ያገናኛል። በዚህ መሠረት ተሰባስበው የንባብ ክበብ የፈጠሩት አንባቢዎችም በተመረጡ መጻሕፍት ዙሪያ ውይይት ይደርገሉ። ምን ተረዳችሁ? ምን ገባችሁ? መጽሐፉ ባነሳው ጉዳይ ላይ ዕይታችሁ ምን ይስላል? ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች ያወያያሉ። እያንዳንዳቸው የንባብ ክበባት ስምንት አባላትን ይይዛሉ።

ከፍታ የሥልጠናና የማማከር አገልግሎት ይህንን ልምድ ከአዲስ አበባ ባሻገር ወደ ክልል ከተሞችም የማስፋፋትና የማሻገር እቅድ አለው። ይህንን ሲያደርግ ታድያ አሁን ላይ ለተመሠረቱት ክበባት የሚያደርገውን የተለያየ ዓይነት እገዛ አጠናክሮ በመቀጠል ነው።
አሁን ላይ ከፍታ የአንባቢዎቹን ኅብረት በተለያዩ መንገድ ያግዛል። ለምሳሌ በየሳምንቱ የሚወያዩባቸውን መጽሐፎች ይመርጥላቸዋል። ለዚህም እንዲያግዝ ከዐስራ ኹለት እስከ ዐስራ አራት የሚደርሱ ምድቦች አዘጋጅቷል። እነዚህም ምድቦች በመጽሐፍት ጭብጦች ላይ መሠረት ያደረጉ ሲሆን፤ የቢዝነስ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የማኅበራዊ ሕይወት፣ መንፈሳዊ፣ የመሪነት ወዘተ ይገኙበታል።

የመወያያ ቦታውንም ድርጅቱ ሲሆን የሚያዘጋጀው፣ አባላት የሚቋደሱት፣ ቤት ያፈራው ቆሎም ሆነ ውሃና ሻይም ያቀርብላቸዋል። እንግዳ ለሚሆኑ አዳዲስ አባላትም፣ ዘልቀው ከመግባታቸው በፊት የመጽሐፍ ንባብን በተመለከተ ተያያዥ የሆኑ ሳይንሳዊ መንገዶች ዙሪያ ገለጻ ይደረግላቸዋል። ማንኛውም የንባብ ፍቅር ያለው ግለሰብ ታድያ ይህን ተከትሎ በወር ሦስት መቶ ሃምሳ ብር በመክፈል የክበቡ አባል መሆን ይችላል።

ታጠቅ እንደነገሩን አባላቱ ለንባብ እንዲረዳቸው ምቹ ሁኔታን ከመፍጠርና ለንባብ እንዲበረቱ ከመግፋት ባለፈ፣ በትምህርት እንዲሁም በተለያየ ሥልጠና የሚያገኙት መረጃ ራሳቸውን ያለማቋረጥ እንዲያስተምሩ ያግዛቸዋል፤ የማንበብ ልማዳቸውንም እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ከዛም ባሻገር ያገኙትን መረጃም ሆነ እውቀት፣ የተረዱትን አዲስ ሐሳብ፣ የተመለከቱትን አዲስ አንጻር ለሌላ ሰው የማጋራት ክህሎት እንዲያዳብሩም ይኽ ልምድ ያግዛቸዋል ሲሉ ነው ታጠቅ ያብራሩት።

‹‹አባላት ድንገት እጃቸው የሚገባ መጽሐፍን ሁሉ ከሚያነቡ ይልቅ፣ ካላቸው የሕይወት ጉዞ አኳያ መርጠው እንዲያነቡ ለማገዝም ይጠቅማቸዋል። በአጠቃላይ የማንበብ ክህሎታቸው እንዲዳብር ክበቡ ያገዛቸዋል።›› ሲሉም አክለዋል።

የከፍታ ዓላማ
ከፍታ የሥልጠና እና ማማከር አገልግሎት እንደሥሙ ለድርጅቶች የማማከር አገልግሎትን እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሥልጠናዎችም በተለያየ መልክና አኳኋን ይሰጣል። ከፍታ የንባብ ክበባትን መመሥራት በንባብ ከፍታን ማምጣት ላይ የመሥራት ጉዞውን የጀመረው ከሦስት ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ ነው።

ይህን በሚመለከት የድርጅቱ ዋና ዓላማ ትውልድ ላይ፣ ሰው አስተሳሰብ ላይ መሥራት የሚል ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በድርጅቱ እምነትና አካሄድ ላይ አንድ አገር ልትቀየር የምትችለው ሰው ላይ ስትሠራ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለ። ሌላው ጉዳይም ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣ ይሆናል ተብሎም ይታሰባል።

ታጠቅ ይህን በሚመለከት ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ፣ ሰዎች ውስጥ ያለውን ትልቅ ሀብት ተጠቅመው የተለወጡ ትልልቅ አገራትን በምሳሌነት ያነሳሉ። እናም ታድያ ማኅበረሰቡ ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የሚገኙትን እምቅ ችሎታዎች አውጥቶ በመጠቀም ያምናሉ። በዚህም የተነሳ ነው በንባብ አስተሳሰብና ዕይታን በማሳል አገር እንቀይራለን ብለው ነገሩን እንደ ተልዕኮ ይዘውትም እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ነው ያነሱት።

ይህን ግብ ለማሳካትም እንደ ርዕይ ትውልድ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ የጥበብ መንደሮችን መገንባትን ቅድሚያ ሰጥተዉታል። ማኅበረሰቡ ውስጥ ያዩዋቸውን ችግሮች የሚቀርፉባቸውን ዘዴዎችም ቀይሰው ነው ሥራቸውን የጀመሩት።
‹‹ስንነሳ አምስት እሴቶችን ይዘን ነበር።›› አሉ ታጠቅ። ከእሴቶቻቸው መካከል የመጀመሪያው ልኅቀት ወይም ‹ኤክሰለንስ› የሚለው ነው። በዚህም ለሁሉ ነገር የተሻለ መንገድ ይገኛል ተብሎ የታመነበት ነው። ኹለተኛው አገልግሎት (ሰርቪስ) ሲሆን፣ ይህም የሕይወት ዘይቤ እንጂ የሥራ ድርሻ ተደርጎ መቆጠር እንደማይኖርበት ጠቅሰዋል።

ሦስተኛው ጥልቅ ፍላጎት /ፓሽን/ ነው። ይህም ሰዎች በፍላጎታቸው እና በችሎታቸው ከሠሩ፣ ሥራ መዝናኛ እንጂ ግዴታ አይሆንም የሚል መነሻ ያለው ነው። ይህ ከሆነ ውጤታማ መሆን ሩቅ አይደለም። አራተኛው የቡድን ሥራ /ሲነርጂ/ ነው። በድርጅቱ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ይህ ነው፤ አብሮ በመሥራት ያምናሉ። አምስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ መሪነት /ሊደርሺፕ/ የሚለው እሴት ነው። በከፍታ የማማከርና ሥልጠና አገልግሎት ውስጥ፣ መውደቅም መነሳትም የሚያያዘው ከመሪነት ጋር ነው የሚል እምነት ይገኛል።

እነዚህም ግዙፍና ጥልቅ ሐሳብ የያዙ አምስት እሴቶችን የሰነቀው ድርጅቱ፣ በተመሳሳይ አምስት ዋና ዋና የሚላቸው አገልግሎቶች አሉት። እነዚህም ከላይ እንዳነሳነው የሥልጠና እና የማማከር የሚሉ ኹለቱ ናቸው። ከዛ በተጨማሪ በልጆች እና በወጣቶች ጉዳይ መሥራት፤ ኹነቶችን ማስተባበር እንዲሁምየተለያዩ የባለ ርዕይ ክበቦችን በማቋቋም የመጽሐፍ አንባቢዎች ክበብን ጨምሮ ትላልቅ ሥራዎችን መሥራት የሚሉ ይገኙበታል።

አዲስ ማለዳ በድርጅቱ ቢሮ በሚካሄደው የአርብ እለት የመጽሐፍት ላይ ውይይት በተገኘችበት አጋጣሚ የተወሰኑ የመጽሐፍ ላይ ውይይት ተሳታፊ አባላት ጋር ኢ-መደበኛ የሆነ አጠር ያለ ቆይታን አድርጋለች። ይሄኔ ታድያ በርካቶቹ እንዲህ ላለው ልምድ እንግዳ እንደሆኑ፣ ከዛም በተጓዳኝ ግን እጅግ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። በጥቂት ጊዜም ለንባብ የነበራቸው አመለካከት እየዳበረ እንደሄደ እና በዛ ያሉ ተጨማሪ መጽሐፍትን ለማንበብ ብረታት እንደሆናቸው አንስተዋል። በተጨማሪም የንግግር ችሎታቸውን ለማዳበር ሊረዳቸው እንደሚችል ያላቸውን ተስፋና እምነትም አክለውበታል።

ንባብ፣ ከሰዎች ጋር መወያየትና መመካከር የሰዎችን አመለካከትና አስተሳሰብ በመቅረጽ በኩል ቁልፍ ተግባራት ናቸው። የትኛውም የዛሬ ላይ የዓለም ሥልጣኔ በምኞት የሚጸነስ ቢሆንም የሚወለደው በንባብ ነው። ለዚህም ይመስላል ከፍታ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት ይህን በሚገባ በመረዳት የኢትዮጵያውያንን ከፍታ አንድም በንባብ ለማምጣት እየተጋ ያለው። ዛሬ ጥቂት የሚመስለው እርምጃም ነገ ፍሬው አብቦ እንደሚታይ ተስፋ እናደርጋለን።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here