ኢትዮጵያ የአሸንዳ ሶለል ባሕላዊ ቅርስን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አቅርባው የነበረውን ጥያቄ አነሳች

0
870

ከጥቂት ዓመታት በፊት በትግራይና በአማራ ክልሎች ውስጥ ታዋቂ የሆነውን የአሸንዳ ሶለል ባሕላዊ ክንውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም፣ ዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን በማቅረብ የምዝገባ ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ነገር ግን ለምዝገባው የሚያስፈልገውን መስፈርት ለማሟላት በገምጋሚ አካላት ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ምላሽና ማብራሪያ ቢቀርብም፣ በዚህ ዓመት ለሚሰጠው ውሳኔ ሳይደርስ መቅረቱን በቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል መረጃው ይፋ ሆኗል።
ይህ በሰሜን ኢትዮጵያ በሴቶች የሚካሄድ ባህላዊ ክንውን በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥያቄ የቀረበው ከሦስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በቀረቡ ሰነዶች ላይ ከገምጋሚ ባለሙያዎች ጥያቄ ቀርቦ ማብራሪያ መሰጠቱ ተገልጿል።
ገምጋሚ ባለሙያዎቹ ይህን ባህላዊ ቅርስ ለመመዝገብ በቀረበው ሰንድ ላይ መሟላት ካለባቸው አምስት መስፈርቶች አራቱ አለመሟላታቸውን ቢገልጹም በኢትዮጵያ በኩል ግን አስፈላጊውን መረጃ አሟልታ ማቅረቧ ተገልጾ ነበር።
ኢትዮጵያ የአሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ አይኒዋሪ/ ማርያ/ ሶለል ባህላዊ ቅርስ ምዝገባ ያቀረበችውን ጥያቄ ለጊዜው በማንሳት ለግምገማው የሚያስፈልጉ ሰነዶችን መልሳ በማደረጃት ጥያቄውን በድጋሚ እንደምታቀርብ ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here