በሳይንስና በሒሳብ የሚሻለው ማነው?

0
639

በ2005 የአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ነው። በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አንድ መድረክ ላይ ምሁራን ተሰብስበው በሳይንስ እና በምህንድስና ዘርፍ ሴቶች ለምን በብዛት አይገኙም የሚል ጉዳይ ላይ እየተነጋገሩ ነው። ንግግሩ ሳይቆይ ነው ወደ ሙግት የተሻገረው። ለምን?
አንዱ ምሁር በንግግራቸው ሴቶች በሒሳብ፣ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ እና በባዮሎጂ እንዲሁም በመሳሰሉት ዘርፎች እንዳይሳተፉ የሚያደርጓቸውን ምክንያቶች በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን አሉ። በዚህ መሠረት አንደኛ ላይ ያስቀመጡት ሴቶች በእነዚህ ዘርፎች ላይ እንዳይሳተፉ ይገለላሉ የሚል ነው። ኹለተኛ ደግሞ ሴቶች ቤተሰብ ከመሠረቱ በኋላ በትምህርቱ ከመግፋት ይልቅ ልጆችን ማሳደግና ቤተሰብን መንከባከብ ላይ ስለሚያተኩሩ ነው የሚል ነው።

ሦስተኛ ላይ ያስቀመጡት ነጥብ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ሴቶች በዝርያቸው ወይም በጄኔቲክስ የሳይንስና የሒሳብ ጉዳይ ላይ የመሳተፍ አቅም የላቸውም፤ ከወንዶች አንጻርም ሲታይ ያላቸው አቅም ዝቅተኛ ነው ይላል። ለሙግትና ክርክር መነሻ የሆነውና፣ በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ አንዳንድ ሰዎችም ‹እርስዎን የሚያክል ምሁር እንዲህ ካሰበማ ከሌሎች ምን እንጠብቃለን!› ብለው አዳራሹን ጥለው እንዲወጡ ያደረጋቸው ይህ ነጥብ ነው።

ተናጋሪው ይህን ነጥብ ያነሱት በድምዳሜ ሳይሆን እንደ መላምት እንደሆነ ደጋግመው አስረዱ። ነጥቡን እንደመላምት እንዲያነሱ ያደረጋቸውም የሰዎች ጄኔቲክስ ከማኅበራዊ ሥሪት ጎን ለጎን በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ነው አሉ። የሰማቸው ግን የለም።
ይህ ጉዳይ በመድረኩ ላይ ከተሰበሰቡ ሰዎች አልፎ በውጪ ተሰማ፣ ብዙዎችም ተቃውሞአቸውን አሰሙ። ይህ ተቃውሞ ከማየሉ የተነሳ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኒቨርሲቲው አባለት ቅሬታቸውን በፊርማ አሰባስበው፣ ‹‹እኚህ ሰው ከሥራ ገበታቸው ይነሱልን! በእርሳቸው ላይ መታመመን የለንም›› የሚል ቅሬታ ለተቋሙ አስገቡ። እና በ2006 ግለሰቡ ከሥራ ገበታቸው እንዲነሱ ተደረገ።

ይህን ክስተት ተከትሎ በካናዳ ያሉ አጥኚዎች ሥራዬ ብለው ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት፣ በመላው ካናዳ 32 ሺሕ በላይ ከሚሆኑ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ በሳይንስ የትምህርት ዓይነት ሴቶቹ ብልጫ ሲያሳዩ፣ በሒሳብ ደግሞ በኹለቱም ጾታዎች መካከል ልዩነት አልታየም ነበር።
ሌላ ጥናት በሌላ ዩኒቨርሲቲ ተደገመ። በዚህም ላይ በሦስት ትውልዶች መካከል የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምህንድስና እንዲሁም የሒሳብ ጉዳዮች ላይ ያለውን የሴቶችና የወንዶች ተሳትፎ የተመለከተ ትንታኔ ተሠራ። እናም አጥኚዎቹ አሉ፤ ‹እንደውም ሴቶች በዚህ ትምህርት ዓይነት፣ ወንዶች በዚያ ዘርፍ ሰነፍና ጎበዝ ናቸው ብሎ መናገሩ ራሱ አሉታዊ ተጽእኖ አለው። በኹለቱም ወገን መርጦ ሰነፍ ለመሆን እድል ይሰጣል›› አንባቢዎች ሆይ! እናንተስ ምን ታስባላችሁ?


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here