ቀጠሮ የሚበዛበት የሕሙማን ሕክምና

0
717

ሹመት እሸቴ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል መቅደላ ወረዳ፣ ከደሴ በስተምዕራብ 128 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምተገኘው ተንታ ከተማ ነው። ሹመት የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ የሚተዳደሩት በግብረና ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ። ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ በማሠማራታቸው የግብርናውን ሥራ ብቻቸውን ነው የሚከውኑት።

ሹመት ማልደው በመነሳት የግብርና ሥራቸውን ቀኑን ሙሉ ሲያከናውኑ ውለው፣ አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው ማቅናት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ከሆነ ሰንበትበት ብሏል።
ደከመኝ ሰለቸኝን ማለትን ወደ ጎን ትተው እርሻቸውን ጉምብስ ቀና ብለው አለስልሰው፣ ዘርተው፣ አርመውና አጭደው ምርቱን ከገለባው እየለዩ ቤተሰብን የሚያስተዳድሩት ሹመት እሸቴ፣ ሆዳቸው አካባቢ የሕመም ስሜት ከተሰማቸው ሰንበትበት ብሏል። ቢሆንም ግን ወደ ሥራቸው በማተኮር የሚሰማቸውን ሕመም በወቅቱ እንዳልተከታተሉት ይናገራሉ።

ቀንን ቀን እየወለደው ሕመሙ እየተባባሰባቸው ሲመጣ፣ በአካባቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያ መመላለሱን ተያይዘውታል። ቢሆንም ግን አጥጋቢ መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም። በመሆኑም ሕመሙ በሥራ ከመሳተፍ ጣሪያ ዕየቆጠሩ አልጋ ላይ ውሎ ወደማደር ሕይወት እንዲያመሩ አስገደዳቸው።

አንድ ቀን ከተለመደው በተለየ መልኩ በጠና ታመው ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል አቅንተው ነበር። በጤና ምርመራ ውጤታቸው መሠረትም ቀዶ ሕክመና እንደሚያስፈልጋቸው ቢታወቅም፣ ያለባቸውን ሕመም ለማዳን አቅሙ ያልፈቀደው የደሴ ሆሰፒታል፣ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር እንዳላቸው ያወሳሉ።

ሹመት እሸቴ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሕክምና እንዲደረግላቸው የተፃፈላቸውን ደብዳቤ ይዘው ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።

ሆስፒታሉን ካሁን በፊት በአካል የማየት ዕድል ባይገጥማቸውም፣ የብዙዎችን ሕይወት ከሞት አፋፍ መዞ ያወጣ አንጋፋ ተቋም መሆኑን በመስማታቸው የመዳን ተስፋ በውስጣቸው እየተሠማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሆስፒታሉ ጎራ አሉ።
ካደረባቸው ሕመም በፍጥነት ተፈውሰው ወደ ተለመደው ሥራቸው ለመመለስ ውስጣቸው ተስፋ አድርጓ። ነገር ግን ከሹመት ገጠመኝና ንግግር መረዳት የተቻለው ነገሮች ባላጠበቁት መንገድ መሆናቸውን ነው። ነገሩ እንዲህ ነው የሆነባቸው፣
ደብዳቤያቸውን እንዳቀረቡ በሆስፒታሉ በኩል ሙሉ ምርመራ እንደተደረገላቸው፣ ከውስጥ የአካል ክፍላቸው ምግብን ከአንዱ ወደ ሌላኛው ውስጥጣዊ ክፍል የሚያስተላልፈው ቱቦ ችግር እንደገጠመውና ጉበታቸው ላይ ችግር በመፈጠሩ ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላቸው ተነገራቸው።

ሆኖም ግን ‹‹አልጋ ስለሌለ ይደወልላችኋል አሁን ወደ ቤታችሁ ሒዱ›› የሚል ያልጠበቁት መርዶ ነበር ከዶክተሮች የደረሳቸው።
የቀዶ ጥገና ሕክመናው የመጀመሪያቸው በመሆኑ ቢያደናግጣቸውም “ሁል ጊዜ ከመሰቃየት ለትንሽ ጊዜ መስዋዕት መክፈል እንዳለባቸው” ራሳቸውን አሳምነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሆስፒታሉ ሠራተኞች ዘንድ “አልጋ ስለሌለ ወደ ቤታችሁ ሒዳችሁ ወራፋችሁን ልትጠብቁ ይገባል” የሚል ያልጠበቁት ጉዳይ ገጠማቸው። ሹመት እንዳመማቸውና ምግብ ለመመገብ እንኳን እንደሚቸገሩ ለማብራራት ቢሞከሩም ተቀባይነትን ማግኘት አልቻሉም።

ሹመት እንደሚሉት ከሆነ የማስታገሻ መድኃኒት እንኳን እንዳመማቸው በመግለጽ ማስታገሻ ስጡኝ ብለው ከለመኑ በኋላ ነው ማግኘት የቻሉት።
አገር አቋዋጠው የመጡት የተሻለና ወቅታዊ ሕክምና አግኝተው ከሕመማቸው ማገገም ይችሉ ዘንድ ተስፋ የሰነቁት ሹመት፣ ከሕመማቸው በተጨማሪ ወደ መበሳጨት ደረጃ ሳይደርሱ አልቀሩም። ለብስጭታቸው ዋናኛ ምክንያትም ከኋላቸው የሚመጡት ሕሙማን ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ማየታቸው ነበር።

“ይህ የቸልተኝነት እንጅ የሥራ ጫና አይደለም፤ አልጋ እንኳን ባይኖር ሲሆን ያለሁበት ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ በወቅቱ እታከም ነበር፤ እኔ ከገጠር ስለመጣሁ ማንም ሊረዳኝ አይችልም” የሚል የመከፋት ስሜት እንደተሠማቸው ይገልጻሉ።
“ይደወልላችኋል” በሚል ስንብት ብቻ ቀኑም ሳይነገራቸው ከሆስፒታሉ ለመውጣት “የተገደዱት” ሹመት፣ በመዲናዋ ውስጥ ወደሚገኝ ቤተሰባቸው ዘንድ ለመሔድ ወሰኑ።

መብላትና መጠጣት እያማራቸው እንደፈለጉ ለመመገብ ሕመማቸው ስለገደባቸው አፋጣኝ መፍትሔ ለማግኘት በግል የሕክምና ተቋማት ለመታከም ቢሞክሩም፣ የሚተዳደሩበት የግብርና ሥራ ግን “ከእጅ ወደ አፍ” አልፎ ይህን ወጭ ለመሸፈን እንዳላስቻላቸው ያወሳሉ።
ከዛሬ ነገ ይደወልልኛል በሚል የመታከሚያቸወን ቀን ሲናፍቁ ድፍን ስድስት ወር ተቆጠረ። በሂደቱም ሕመማቸው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ።

ለግል ሕክምና አቅማቸው እንዳልፈቀደ ማመናቸውና በተስፋ የሚጠባባቋዋቸው የጥቁር አንበሳ ዶክተሮች አለመደወላቸው ያጋባባቸው ጭንቀት ለሕመሜ መባባስ ሌላ መንስኤ ሆነብኝ ይላሉ።
እስካሁን ስልክ አልተደወለልኝም፤ በግሌ እንደልታከም አቅም የለኝም የሚሉት ሹመት “ሕመሙ ጊዜው ሲራዘም ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስብኝ” ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው። የሚመለከተው አካልም ችግራቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት አልጋ እንዲያሲዛቸውና ሕክምናውን እንዲሰጣቸው ነው ከአዲስ ማለዳ በነበራቸው ቆይታ የገለጹት።

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከተለያዩ ጤና ጣቢያዎች፣ የግል ክሊኒኮችና ጀማሪ ሆስፒታሎች አቅም በላይ የሆኑ ሕሙማን የሚታከሙበትና ለችግራቸው መፍትሔ የሚቸሩበት አንጋፋ ሆስፒታል እንደሆነ ይነገራል።
ለዚህም በየቀኑ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚርመሰመሱ ታካሚዎች ምስክር ናቸው። ይህ በእንዲህ እንደለ ሆኖ ከተለያዩ የጤና ተቋማት የድንገተኛ ደብዳቤ ተጽፎላቸው ቢመጡም በወቅቱ ሕክማና ባለማግኘታችን በቀጠሮ ብዛት እየተጉላላን ነው የሚሉ ሕሙማንም አልጠፉም።
ከተለያዩ ቦታዎች ‹ሪፈር› የሚጻፍላቸው ታካሚዎች በየዕለቱ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማቅናታቸውን ተከትሎ ወረፋ የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው። ብዙዎቹ “ይደወልላቸኋል ከቤታችሁ ሆናችሁ ጠብቁ” ተብለው ቢቆዩም፣ በወቅቱ ተጠርተው ሕክምና ባለማግኘታቸው ለሞት የተዳረጉ ሕሙማን እንዳሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ግለሰቦች ጠቁመዋል።

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ይዘው ለሚመጡ ታካሚዎች ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታ የለም የሚሉት ሀብታሙ ሲሳይ ናቸው። እንደውልላቸኋለን ተብለው እየጠበቁ እያለ ሕመሙ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉ ሰዎች አውቃለሁ በማለት የተናገረው ሀብታሙ፣ ዶክተሮች ከሰባት ወር በኋላ ሲደዉሉ ስልኩን ቤተሰብ አነስቶ እንዳዋራቸው ሰምቻለሁ በማለት ነው የዓይን ዕማኘነታቸውን የገለጹት።
አክለውም ጥቁር አንበሳ ብዙዎች የሚተሙበት ታላቅ ሆስፒታል ነው፤ ግን እንደ ስሙ አይደለም። ምክንያቱም ለድንገኛ ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታ የተዳከመ ነው ይላሉ።

አያያዘውም “ታመህ በአቅራቢያህ ወዳለ የጤና ተቋም ስትሄድ ከአቅማችን በላይ ነው ተብለህ ወደ ሌላ ሆስፒታል ብትሄድም በቶሎ መፍትሔ ማግኘት አይቻለም” ነው ያሉት። “ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደብዳቤ ቢጻፍልህ እንኳ፣ ትመረመራለህ፤ ሌላ ቀን ይደወልልሃል ትባላለህ፤ ነገር ግን ቶሎ የሚደወልበት አጋጣሚ አናሳ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ሀብታሙ በመጨረሻም “እኔ እንዳየሁት ከሆነ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአልጋ ዕጥረት አለ፤ ይህን ተከትሎም ይደወልልላችኋል በማለት በአጉል ተስፋ ከመሙላት አንችልም ብሎ መመለስ ወይም ድንገተኛ የሚጻፍላቸውን በወቅቱ ማስተናገድ ይገባል” በማለት ነው አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።

መጀመሪያ ለሕክምና ከሄዱበት የግል ክሊኒክ አቅማችን አይፈቅድም ተብለው ወደ ጥቁር አንበሳ ድንገተኛ የሕክምና ደብዳቤ ቢጻፍላቸውም፣ ሕክምና ማግኘት ያልቻሉ እስካሁን በተስፋ የሚጠብቁ ግለሰቦች እንዳሉም ነው አዲስ ማለዳ መረዳት የቻለችው።
ሌላኛው ሽመልስ መንገሻ ወንድሙ በጠና ታሞበት በጥቁር አንበሳ ቀጠሮ ቢሰጠውም ስልክ ስላልተደወለለት ዶክተሮችን ሊያማክር ወደ ሆስታሉ መምጣቱን የሚናገረው ወጣት “ምን የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብለህ ነው”? በሚል አነጋገር ነው ለገጠመው ችግር መፍተሔ ለማግኘት አለመቻሉን ተስፋ የቁረጠ በሚመስል ስሜት የገለጸው።

“ምን የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብለህ ነው? የሚያስተካክሉት ነገር ይኖራል ብለህ ነው? እንዳው ካላችሁ ዘግቡት እንጂ የሚመጣ ለውጥ የለም” ሲል ይናገራል።
ሽመልሽ አያይዞም፣ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ሙከራ እንዳደረገ ገልጾ፣ “አስቸጋሪ ነው እኔ የማውቃቸው ስፔሻሊስቶች አሉ ሳናግራቸው በቃ ከቀጠሮ ውጭ ምንም አይነት የሚሰጥህ ነገር የለም” ብለውኛል በማለት ነው ያብራራው።
ግለሰቡ አክሎም ከባለሙያዎቹ አነጋገር የተረዳሁት ቀጠሮ የሚቀጥሩት ሕሙማኑ ቁርጣቸውን አውቀው በግል ለመታከም እንዲነሳሱ መልዕከት ለማስተላለፍ ነው በማለት የግል አስተያቱን ሰጥቷል።
ሰፔሻሊስት ዶክተሮቹ ለሽመልሽ ያስረዱት ይደወልልናል እያሉ ስልክ ከመጠበቅ ይልቅ ታማሚው ወደ ሌላ የሕክምና ተቋም ሔደው እንዲታከሙ ማመቻቸቱ የተሸለ መሆኑን ነው።

የመጉላላትና “ሲደወልላችሁ ትመጣላችሁ” ብሎ ቀጠሮ መስጠትና በቀጠሮው ሰዓት ሕሙማኑን አለመጥራት የሚስተዋለው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ በሚገኙ ሌሎች ሆስፒታሎችም ጭምር ነው።
ለአብነትም ከተለያዩ የሕክምና ተቋማት ሪፈር ተጽፎላቸው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል የሚያቀኑ በርካታ ሕሙማን ተመሳሳይ ችግር ገጠመን ሲሉ ይደመጣሉ።

ቅሬታ አቅራቢ ሕሙማኑ እንደሚሉት ከሆነ፣ ቅሬታቸው ለምን ቀጠሮ ተሰጠን ሳይሆን በተሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ሕክምና ያለማግኘታቸው መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው።
ሌላኛው ከታካሚዎች ጋር በተያያዘ የሚነሳው ቅሬታ ሕሙማኑ ወደ ሆስፒታሉ በሚያቀኑበት ወቅት ‹‹ሲደወልላችሁ ትመጣላችሁ፤ ለጊዜው አልጋ ስለሌለ ወደ ቤታችሁ ሒዱ›› ይባላሉ እንጅ ለሕክምና የሚጠሩበት የቀጠሮ ቀንና ወር ተለይቶ አለመሰጠቱ ነው።
በዚህም ሆስፒታሉ ቀጠሮ ቢሰጣቸውም ሕመሙ ግን ቀጠሮ እንደማይሰጣቸው በአጽንኦት የሚናገሩት በርካታ ታካሚዎች ናቸው።

ይህን በተመለከተም አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ሲሆን፣ የየሆስፒታሉ ኃላፊዎች ምላሽም በተለይም ለቀዶ ሕክምና የሚያገለግል የአልጋ አቅርቦት ዕጥረት መኖር ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።
በጉዳዩ ከአዲስ ማለዳ በተጨማሪ ሌሌች በርካታ የሚዲያ ተቋማትም በተደጋጋሚ ሲዘግቡ ይስተዋላሉ። የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ምላሽ ግን “የአልጋ ዕጥረት መኖር፤ የሕሙማን መብዛት” እንደሆነ ነው የተመላከተው።
በመሆኑም ኹሉንም ታማሚ በተመሳሳይ ጊዜ ማስተናገድ ስለማይቻል የከፋ ችግር ያለበትን እስቀደምን፣ ጊዜ የሚሰጥ ሕመም ላላቸው ቀጠሮ መስጠታችን የማይቀር ነው ሲሉ ነው የሆስፒታሎቹ ሠራተኞች የሚናገሩት።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here