በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸው የሚታወቅ ነው። ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ምክንያት በጦርነት ቀጠናው ውስጥ ያሉ ኹሉም ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል። ተማሪዎች ትምህርት ከማቋረጣቸውም በላይ፣ በጦርነት ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉ በተለያዩ ግንባሮች ከሚማረኩ የህወሓት ታጣቂዎች መረዳት ይቻላል።
በአማራ እና አፋር ክልል እንዲሁ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው እንደሚገኙ ተነግሯል። ከሰባት ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች መወደማቸውም የተማሪዎችን ሕይወት የባሰ ከባድ እንደሚያደርገው በርካቶች ይገልጻሉ። በተለይ በአማራ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባትና ትምህርት ለማስጀመር መንግሥት ከ11 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ያስፈልገኛል ማለቱ ተማሪዎች ለበርካታ ወራት ከትምህርት ገበታቸው ዕርቀው እንዲቆዩ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ግምት አለ።
ሆኖም ተማሪዎች ለረዥም ጊዜ ከትምህርት ቤት በራቁ ቁጥር የሚፈጠርባቸው የሥነ-ልቦና ቀውስ ከመኖሩ ባለፈ፣ ዳግም ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ እንደ በፊቱ ቀለም ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይችላሉ ወይ የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ይነሳል።
በዚህም ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት እና መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ የተማሪዎችን ሥነ-ልቦና መጠገንና ያዩትን እንዲረሱ ማድረግ እንደሚገባም የብዙዎች ጥቆማ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ከቆቦ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር የተወሰነ ቆይታ አድርጋለች። ተማሪዎቹ ከአካባቢያቸው ግጭቱን ሸሽተው አዲስ አበባ ውስጥ ዘመድ ቤት ተጠልለው እንደሚኖሩ ገልጸው፣ ከተቋረጠው ትምህርት ይልቅ አሁን ላይ የሚያሳስባቸው ሌላ መሆኑን ተናግረዋል።
ሮቤል አለሙ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን ባለፈው ዓመት አጠናቋል። ሮቤል አሁን ላይ የ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን መቀጠል ሲገባው፣ በተፈጠረው ችግር ምክንያት አዲስ አበባ መጥቶ ከአክስቱ ጋር እየኖረ ነው። ሮቤል ኹሌ የሚያስበውና የሚጨነቀው ትቷቸው ስለመጣ ቤተሰቦቹ እንደሆነ ያስረዳል። ሮቤል፣ “በዚህ ሰዓት ስለትምህርት አልጨነቅም፣ ሠላም ቢኖርና ትምህርታችን ባይቋረጥ መልካም ነበር። ነገር ግን አሁን ስለትምህርት የምናስብበት ጊዜ ላይ አይደለንም” ነው ያለው። ቀድሞ በኮሮና ምክንያት ብዙ ጫና እንዳሳለፉ የሚገልጸው ሮቤል፣ አሁንም ብዙ የምናውቃቸውን አጥተናል፤ ይህም ስለትምህርት ተስፋ እንዳይኖረን ያደረገ ነገር ነው ሲል አብራርቷል።
ጓደኛው ሻምበል ተሰፋዬም እንዲሁ፣ አሁን ላይ ቤቱ ቁጭ ብሎ በሚውልበት ጊዜ ስለ ቤተሰቦቹና ስለጦርነቱ መረጃ ለማግኘት ከመጣር ይልቅ ስለትምህርት አስቦ እንደማያውቅ ነው የሚገልጸው። ትምህርት ቢጀመርና ወደ ትምህርት ቤት ብንመለስ እኛ በቦታው ተገኝተን የደረሰውን ግፍ ስላላየን ላይከብደን ይችላል፣ በቦታው ሆነው ጥቃት የደረሰባቸው፣ የተደፈሩና ሲደፈሩ የተመለከቱ እና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ተማሪዎች ከዚህ በኋላ እንደበፊቱ ተረጋግተው ትምህርታቸውን እስከመጨረሻው ይከታተላሉ ብሎ ማሰብ በጭራሽ ይከብዳል ባይ ነው።
ወይንሸት አባተም እንዲሁ በ2013 የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን ጨርሳለች። “ጦርነት ከመከሠቱ በፊት ትምህርቴን ጨርሸ ስለሚኖረኝ ሕልም አስብ ነበር፣ አሁን ግን ስለማውቃቸው የሞቱ ተማሪዎችና ስለሁኔታው ከማሰብ ውጭ ስለትምህርት የማስበው ነገር የለኝም” ብላለች።
ጓደኛዋ ሜላት ፈንታሁንም ለአዲስ ማለዳ በሰጠችው ሐሳብ፣ በጣም የላቀ ዕውቀትና የትምህርት አቀባበል የነበራቸው ተማሪዎች ሳይቀር ሥለትምህርት ተስፋ ቆርጠው መመልከቷን አንስታለች። የተማሩ የሚባሉ አካላት በፈጠሩት ቀውስ አገር እንዲህ ስትበጠበጥ ያዩ ተማሪዎች፣ ለትምህርት ያላቸው ዋጋ ደብዛዛ እንደሚሆንም ነው የጠቆመችው። እንዲሁም ከሌሎች ተማሪዎች ወደ ኋላ መቅረታችን የሚፈጥረው ስሜት በጣም የሚጎዳ ነው። ለተማሪ አንድ ዓመት ወደኋላ መቅረት ቀላል ነገር አይደለም፤ ይህም ያሳስበኛል ብላለች። ሥጋዊ ፍላጎትን ለማሳካት ግዴታ መማር አለብን፤ በሰዎች ኑሮ መካከል ልዩነት የሚፈጥረውም ትምህርት ነው። የነገ አገር ተረካቢ ታዳጊዎች በመሆናችን ይህ አይገባንም ነበር፤ የደረሰብን ጉዳት በቀላሉ የማይረሳ በመሆኑ ያሳዝናል ስትል ተናግራለች።
የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት አምባቸው ይሁን በጦርነት ወቅት ከፍተኛ ጫና የሚደርስባቸው ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን አንስተው፣ በዚህም ታዳጊዎች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ የአዕምሮ መታወክ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ተስፋ ማጣት እና ያላሳዳጊ መቅረት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸዋል። በዚህም ለማይቃና የዕድሜ ልክ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገው እንደሚኖሩ ነው ያብራሩት። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ጦርነትና የአዕምሮ ጤና መታወክ የተቆራኙ ናቸው። ጦርነት ለአዕምሮ መቃወስ ደወል ነው ይላሉ። እናቱና እህቱ ስትደፈር ያዬ ተማሪ እንዴት ብሎ በቀላሉ ወደ ትምህርት ገበታው ተመልሶ ውጤታማ ይሆናል ያሉት ባለሙያው፣ የሰው አስከሬን በየመንገዱ ሲያዩ የሚውሉ፣ የጥይት ድምጽ በአዕምሯቸው የታተመባቸው፣ ለረሀብና ለበሽታ የተጋለጡ ተማሪዎች ለመኖር ተስፋ የመቁረጥ ዕድላቸው የሠፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ምናልባት የአካባቢያቸው ሠላም ተረጋግጦ ወደ ትምህርት ገበታቸው ቢመለሱ እንኳን፣ ያለማቋረጥ የባለሙያ ዕገዛ ይሻሉ ነው ያሉት። የቤተሰብ ፍቅር ማጣት ለታዳጊዎች ትልቅ ጉዳት ነው፤ በዚህ ጦርነት ወላጆቻቸውን ያጡ ወይም ከወላጅ የተነጠሉ ተማሪዎች ይኖራሉ። ስለዚህም እንደ አገር ወይም እንደ አንድ አካባቢ ማኅበረሰብ የሚፈጠረውን የትውልድ ክፍተት ለመሙላት በርካታ ጥረቶች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።
መምህሩ ሲገደል፣ ወይም ያስተማረችው መምህር ስትደፈር ያዬ ተማሪ ሊኖር ይችላል፤ ይህ ጦርነት በየትኛውም አገር ላይ ባለ ትውልድ ያልተፈጠረ አሳዛኝ የሥነ-ልቦና ቀውስ የፈጠረ ነው ብለውታል።
የአሁኑ ትውልድ ስለ ጦርነት እየሰማ እንዲያድግ እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ በታዳጊ አገሮች ተማራማሪ እና ችግር ፈች ትውልድ በማፍራት የሠለጠነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ማነቆ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ትምህርት ቤቶች፣ በተለይ በገጠር ያሉት፣ የሥነ-ልቦና ባለሙያ አልባ መሆናቸው በራሱ ችግሩን በቀላሉ ለመወጣት እንደሚያዳግትም ነው ያመላከቱት።
በሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አድነው አበራ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ሐሳብ፣ በሽብርተኛው ህወሓት ምክንያት የብዙ ሕፃናት እና ተማሪዎች ሕይዎት አደጋ ውስጥ ወድቋል። ከደረሰባቸው አካላዊ ጥቃት በበለጠ፣ ያጋጠማቸው የሥነ-ልቦና እና አዕምሯዊ ሥብራት ክፉኛ ጎድቷቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። በሰሜን ጎንደር ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን ያላነሱ ሕፃናት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መራቃቸውን አውስተው፣ ትምህርት ቤታቸው ወድሟል። የትምህርት ቤታቸው በመውደሙም የሚያደርስባቸው ዘላቂ የሥነ-ልቦና ጫና ከፍተኛ ነው በማለት ነው ያብራሩት።
ሕፃናት ተማሪዎች በዚህ መልኩ እንዳይማሩ መደረጉም መብታቸውን መጣስ መሆኑን አመላክተዋል። ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች (በተለይ ሴቶችና ሕፃናትን) ሥነ-ልቦና ለማጠንከር የተለያዩ ንቅናቄዎችን ተቋማቸው በየጊዜው የሚያዘጋጅ መሆኑን ጠቁመዋል። እስካሁንም የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ እያቀረቡ እንደሚገኙም ነው የገለጹት። ለደረሰው ችግር በሕግ የሚጠየቁ አካላት እንደሚኖሩም ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ የታዳጊዎችን የወደመ ትምህርት ቤት እና የተሰበረ ሥነ- ልቦና ለመገንባት ዕቅድ (Recovery Plan) መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
አዲስ ማለዳ ከትምህርት ሚኒስቴር ጠይቃ ያገኘችው መልስ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ ግጭት በተከሰተባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በነበሩ ትምህርት ቤቶች ይማሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጥናት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አማካይነት እየተካሄደ ነው። የጥናቱ ውጤትም ወደፊት ይፋ ይደረጋል የሚል ዕምነት አለ።
በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው የራቁት እና በርካታ ትምህርት ቤቶች የወደሙት በአማራ ክልል መሆኑ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወቃል። ይሁን እንጅ በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካላት ቀርቷል።
የዓለም ጤና ድርጀት በአንድ ወቅት ይፋ ያደረገው ጥናት፣ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች፣ ለአሰቃቂ ጦርነት ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት ለአዕምሮ መቃወስ ይጋለጣሉ ይላል። 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አቅማቸውን ተጠቅመው መደበኛ ሕይወታቸውን መምራት እንደሚያቅታቸው ጥናቱ አያይዞ አስቀምጧል። ከጦርነት ጋር በተያያዘ በስፋት ይከሰታሉ ካላቸው ነገሮች ውስጥም፣ ድብርት፣ ሥጋት፣ በጭንቀት የሚመጣ የአዕምሮ በሽታ እና እንቅልፍ ማጣት ይጠቀሳሉ።
በዚህም ጦርነት ባለባቸው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ በርካታ ታዳጊዎች፣ ከትምህርት ገበታቸው ከመራቃቸው ባሻገር በደረሰባቸው ሠቆቃ እና በተመለከቱት ጭካኔ ለበርካታ ማኅበራዊና አካላዊ፣ እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶች ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይነገራል።
ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014



