ማክሠኞ ታህሳስ 19/ 2014 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ክልል የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ለህብረተሰቡ ሲያቀርቡ በተገኙ 29 ሺህ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ጨምሮ 98 ኩንታል በርበሬ ከመርዛማ ነገር ጋር በመቀላቀል ሲሸጡ በተገኙ አካላት ላይም ክስ መመሰርቱን ገልጿል።
በክልሉ የገና በዓልን በማስመልከት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር እንደሚሰራም ተጠቁሟል።
የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ማሄ ቦዳ የበዓላት ወቅት ሸማቹም ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ነው ብለዋል።
በዚህም 98 ኩንታል በርበሬ ከመርዛማ ነገር ጋር በመቀላቀል ሲሸጡ በተገኙ አካላት ላይ ክስ ተመስርቶ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አክለውም በዓልን ተንተርሰው የግል ጥቅማቸውን ለማካበት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ኃላፊው አስጠንቅቀዋል።
ወደ ክልሉ የሚገቡ ዳያስፖራዎችን የኢትዮጵያውያንን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በመጠቀም እንዲሁም እስከ 30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ በክብካቤ ማስተናገድ እንደሚገባም ኃላፊው ማሳሰባቸውን ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።



