“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰናበቷና ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፊርማቸው አጽድቀው መዝገቡን ዘግተዋል። በብዙ ጫናዎች ውስጥ በምትገኝ አገር ጫንቃ ላይ ተጨማሪ ፈተናዎችን ለመጫን የማይራሩት ‹ባለጸጋ› አገራት፣ ባገኙት አጋጣሚ ይህን ዱላ በኢትዮጵያ ላይ እያሳረፉት ይገኛሉ።
ይህን ከምንም በላይ በሴቶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም በሚገባ እያወቁ ያደረጉት ነው። ‹ሴቶችና ሕጻናትን ለመርዳት ድንበርና ሁኔታ አይገድበንም› እያሉ በሴቶችና ሕጻናት ስም የአፍሪካን በሮች በ‹ትህትና› አስከፍተው የሚገቡት የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት፣ ሲያሻቸው ‹መንግሥታችሁን መቅጣት ስለፈለግን ነው› ብለው ሴቶችና ሕጻናትን አናውቅላችሁም ሊሉ እንደሚችሉም አሳይተዋል።
የአጎዋ ስምምነት በመጀመሪያ ሰነድ ሆኖ ፊርማ ያረፈበት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2000 ነበር። ያኔ ታድያ ለስምንት ዓመታት ብቻ የሚዘልቅ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ 39 የአፍሪካ አገራት ብቃትና ጥራት ያላቸውን ምርቶች ያለቀረጥ ወደ አሜሪካ የሚልኩበት እድል ነበር። ነገሩ ትልቅ ውለታ መሆኑ እሙን ነው። ይህ የሚሆነው አፍሪካ ካለችበት ድህነት አንጻር እንጂ ‹ምርጥ ምርጡን ለአሜሪካ፣ ደንበኛ ንጉሥ ነው› እየተባለ የተጣራው ሁሉ ሲላክ ነው የኖረው።
ይህ ስምምነት ይጠናቀቃል በተባለበት ዓመት ታድሶ ተራዘመ፣ መጀመሪያ እስከ 2015 ከዛ እስከ 2025 እንዲዘልቅ ተወሰነ። ኢትዮጵያም በዚህ ቀላል ተጠቃሚ አልነበረችም። ብዙ የሰው ኃይልም በዚህ ምክንያት የሥራ እድልን አግኝቷል። ቀላል የማይባል በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርም ገቢ ሆኗል።
ከምንም በላይ ለሴቶች የፈጠረው የሥራ እድል ዋጋ ነበረው። ይህን የተረዱም ‹ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ብትሆንም፣ የጓዳ ችግሯን በራሷ ትፍታ እንጂ የአጎዋ ስምምነት አይነካ› ብለው ጠይቀዋል። ነገር ግን ድምጻቸው አልተሰማም። ለሴቶች እንታገላለን ያሉ ድርጅቶች ‹ምን አገናኘው?› ብለው አልጠየቁም። እንደውም ‹ኢትዮጵያ እንኳን ከአጎዋ ታገደች!› ብለው ጮቤ የረገጡና ለወትሮ የሴቶች ጉዳይ ተሟጋች ነን ያሉ ግለሰቦችን መታዘቤን ሳልጠቅስ ለማለፍ አልወድም። ያሳዝናሉ!
ይህ አጋጣሚ አዳዲስ በሮችን ይከፈታል። አንዳንዴ መገፋት የሚያበረታቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ይህ ከአጎዋ መገፋት ኢትዮጵያ አዲስ መላ እንድትቀይስ ሊረዳት ይችላል።
አዎን! ኢትዮጵያ ከአጎዋ ባትሰረዝ ጥሩ ነበር። አዎን! የግብይት ስርዓቱ ራሳቸውን ለመቻልና ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚታትሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊት ሴቶችን ያግዝ ነበር። አዎን! አሁን መልፋት፣ መድከም፣ ብዙ መውደቅና መነሳት ከፊታችን አለ። አዎን! ያለፋል። ግን ማለፉ አይቀርም። ኢትዮጵያ ከታሪክ መዝገብ ትቆይ እንጂ ከአጎዋ መዝገብ መነሳቷ የዓለም ፈጻሜ ሊሆን አይችልም። ሴቶች በርቱ!
ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014


