የሠራዊቱ ወደ ትግራይ አለመግባት

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ከኹለት ወራት ገደማ ሁኗል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን አካል ሕግ ፊት ለማቅረብና ከአስጊነት ደረጃ ለማውረድ በርካታ ሰዎች መሰዋዕት የሁኑባቸው ውጊያዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። መከላከያ ትግራይ ክልልን ትቶ ከወጣ ጀምሮ ሠራዊቱ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳይከፍል መደረጉ ተገቢ እንደሆነ ይነገራል። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጁሃር ሳዲቅ ከሠሞኑ መከላከያ ወደትግራይ እንዳይገባ መደረጉን በተመለከተ ሐሳባቸውን እንዲህ አስፍረዋል።

ህወሓት “በሰሜን የመከላከያ ዕዝ ላይ መብረቃዊ ጥቃት አድርገናል” በማለት ጦርነቱን በይፋ በመጀመር፣ ኢትዮጵያን እንደሚያፈርሱ እና ከአማራ ሕዝብ ጋር ሒሣብ እንደሚያወራርዱ በመዛት ኢትዮጵያን ወደጦርነት ከቷታል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ በህወሓት የተከፈተበትን ጦርነት ለማስቆም የሕግ ማስከበር( Law Enforcement) እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወቅ ነዉ ። በነዚህ የሕግ ማስከበር ሒደቶች፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ በጦርነቱ ሊደርስ የሚችለው መከራ፣ እንዲሁም ራሳቸዉን በሽብር ከተፈረጀው ባንዳ ቡድን ነፃ ማድረግ ለሚፈልጉ ሲባል የእጅ ስጡ ጥሪ ለተከታታይ 72 ሰዓታት ቢታወጅም፣ በዕብሪት ልቡ ያበጠዉ ሰዉ በላ ድርጅት ህወሓት ግን ጥሪውን ወደ ጎን በማለት፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት ለመሣብ በርካታ ዉሸቶችን እየደረደረ የትግራይ ወጣትን ለጦርነት በማሠለፍ ኢትዮጵያን ለመዉጋት መሣሪያዉን ደገነ ። የኢትዮጵያ ሠራዊትም የተከፈተበትን የክህደት ጦርነት ለመቀልበስ፣ ብሎም አይደፈሬ ክንዱን ለማሣየት ተንቀሳቅሶ ትግራይን የተቆጣጠረዉ ከኹለት ሳምንት ባልዘለለ ጊዜ ዉስጥ ነበር። ታዲያ የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይን ሲቆጣጠር፣ ህወሓት የተባለዉ የሽብር ቁንጮ ግን በቀበሮ ጉድጓዱ ዉስጥ ገብቶ ነበር የቆየዉ።

አንድ የማይካድ ሐቅ የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ላይ መከላከያ እንኳ ሲገባ ቀድሞ በፌደራል ፖሊስ ነበር ሕዝቡ እንዲረጋጋ የተደረገው ። ከዚህ በኋላ የትግራይ ሕዝብ እንደ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ መዉጣት አለበት፤ ከህወሓት መዥገራዊ አስተዳደር መላቀቅ አለበት፤ ብሎ እንደወገኑ ቆጥሮ ለስምንት ወር ትግራይ የነበረው መከላከያ ሠራዊት ላይ ምን ዓይነት ግፍ እንደተፈፀመበት ከኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እስከ ወታደራዊ አመራሮች ድረስ ሲገለጽ የነበር ነበር። ሠራዊቱ በመርዝና ለተለያዩ ዕርዳታዎች በሚል ጥሪ በነዋሪዎቹ እንደተወጋ መገለጹ ይታወሳል። ከዚህም አልፎ ከህወሓት ጋር በማበር ሕዝቡን የሚያሠቃዩትን፣ በወንጀል የሚፈለጉትን አሳልፋችሁ ስጡ ሲባልም ከማጋለጥ ይልቅ፣ በጊዜያዊ አስተዳደርነት የተሾሙትን ጭምር ማስፈራራትና ግድያ መፈጸሙ የሕዝቡ ተባባሪነትን ጥያቄ ዉስጥ የከተተ ሆኖ አልፏል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደጀን ይሆነኛል ብሎ በቀረበዉ ሕዝብ ሲቀጣ ለመጀመሪያ ጊዜ አለመሆኑ ደግሞ እኔን ጨምሮ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያሳዘነ ተግባር ነበር። ህወሓት ከማዕከላዊ መንግሥቱ እንደቀድሞዉ ጊዜ ካልተደመጥኩ አልታዘዝም በማለት ትግራይ ከከተመበት ወቅት አንስቶ፣ ለበርካታ ዓመታት ሲዘጋጅበት ለነበረው ጦርነት የክልሉን በጄት ጭምር ለልዩ ኃይል ማሠልጠኛነት መጠቀሙ የሚታወስ ነው። በዚህ መልኩ የጦርነት ጉሠማዉን የተመለከቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ቀድሞም ሠራዊቱ ትግራይ የተቀመጠው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል በነበረው ጦርነት መነሻነት የሰሜኑን ክፍል ከጥቃት ለመከላከል የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ዕርቅ በመውረዱ ምንም የሚያሠጋ ነገር ስለሌለ እንዉጣ ሲሉ፣ የአካባቢው ሕፃናትና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አጎንብሰዉ እባካችሁ አትሂዱብን በማለትና የሰሜን መከላከያ ዕዝን በማዘናጋት በዉድቅት ሌሊት በህወሓት ጥቃት እንዲፈጸምበት ማድረጋቸው ትዉልድ ይቅር የማይለው ስህተት ነዉ ።

በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሰሜን ዕዝ ላይ ከተገደሉ በኋላ የህወሓት ታጣቂዎች ዙሪያ ከበው እየጠጡ ሲጨፍሩ እግዚያብሔርም አላህም የሚወደዉ አይደለም የሚል አንድም ሰው መጥፋቱ የጭካኔያቸዉን ጥግ ይገልጸዋል። ከገደሉ በኋላ መጨፈሩስ ይቅርና፣ አብሮ የበላ የጠጣን፣ ሲጠብቀዉና ሰብሉን ሲንከባከብለት የነበረውን፣ መሠረተልማት ሲሠራለት የቆየውን ሠራዊት ሬሳ ቀባሪ አጥቶ የአሞራና የጅብ ቀለብ የሆነበት የቅርብ ጊዜ ግፍ ከኢትዮጵያዊያን አእምሮ አይጠፋም።

ይህን ሁሉ ግፍ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ካስተናገደ በኋላ የተከፈተበት የሥም ማጥፋት ዘመቻ ሠፊ ነበር። በጦርነቱ እየተሣተፉና ህወሓት ያዘጋጃቸውን አምስት ዓይነት የሚሊታሪ ዩኒፎርሞች እየለበሱ ሴቶችን የደፈሩ የህወሓት አባላትን ተግባር በመከላከያ ያላከኩ፣ ህወሓት የገደለውን ጭምር በሠራዊቱ እያሳበቡ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል የሚሉ የሥም ማጥፋት ፕሮፓጋንዳዎች ስንሠማ ነበር። ህወሓትና ደጋፊዎቹ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ሲለጥፋት የነበረዉ ነገር በሙሉ በተለያየ ጊዜ በነ UNHCR፣AMNESTY INTERNATIONAL፣ HUMAN RIGHT WATCH፣ ETHIOPIAN HUMAN RIGHT COMMISSION በተደረጉ የምርመራ ዉጤቶች ውድቅ መደረጋቸው ይታወሳል። ይህ የምለው ሠራዊቱ በደል ደርሶበት ጭምር መሆኑ ነዉ። ህወሓቶች የዉጭዉን ዓለም ትኩረት ለመሣብ ሠራዊቱን ቢከሱም፣ የነሱ ተላላኪ በሆኑ ድርጅቶች ጭምር ክሳቸው ፉርሽ ሆኖባቸዋል ። የሚገርመዉ አንድም የዓለም ሚዲያ ሆነ ዛሬ ህወሓትን ደግፈዉ ከሚላላኩ አገራት ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ስላደረሰዉ ግፍ ምንም ለማለት አለመፈለጋቸው ነዉ ። ነገር ግን፣ የአንድ አገር መከላከያ ሲነካ የትኛውም አገር ቢሆን አጸፋዊ ምላሽ መስጠት ምክንያታዊ ስለሚሆን በአዘጋገባቸው የጦርነቱን መንስኤ ከመግለጽ የጸቆጠቡ መሆናቸው ነዉ ።

መከላከያ ሠራዊት ደጀን ብሎ የቀረበዉ ማኅበረሰብ ከለላ ሳይሆንለት ሲቀር፣ ለጥሞና ብሎ ትግራይን ለቆ የወጣ ጊዜ ዕብሪተኛዉ ቡድን ሠላም ካለእኔ የለም በሚል በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራና ጥቃት ማካሄድ ጀመረ። በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ ሠርጎ ገብ በማደራጀትና በገንዘብ በመደለል፣ ማኅበረሰቡ ዘንድ የዉሸት መዕክተኛ በመላክ የሽብር ሥራ በመሥራት ሕዝቡ ከቀየዉ እንዲፈናቀል አድርጓል። መከላከያ ሠራዊቱንም ከዉስጥና ከውጭ በማጥቃት እንዲያፈገፍግ አስገድዷል። የቂሙን ያህል ዘርፏል፤ አዉድሟል፤ አቃጥሏል፤ ገሏል ። በአፋር በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ፣ በአማራ ክልል ሸዋሮቢት ፣ አጣዬ ፣ ከሚሴ ፣ደሴ ፣ ኮምቦልቻ ፣ ሰሜን ሸዋ ፣ ባቲ ፣ቆቦ ፣ወልዲያ ፣ ላሊበላ ፣ ዋግኸምራ ፣ ሰቆጣ፣ ወዘተ. ያደረሰውን ውድመት እና በሕዝብ ላይ የፈጸመውን ወንጀል ስናይ፣ ምንም ትርጉም የማይሰጥ፣ ከወታደራዊ ትግል ይልቅ ንጹኃን ዜጎችን እየመረጡ መግደልን መሠረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ተግባር ነዉ አሸባሪዉ ህወሓት የፈፀመው። የአማራ ክልል መንግሥት ስለዉድመቱ ባወጣዉ መረጃ የደረሰበት የጉዳት መጠን በገንዘብ ሲለካ ከ 297ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ነው ያሳወቀው። ይሄ በሕዝቡ ጉዳት ጋር ሲደማመር በአማራ ክልል የወደሙ ከተሞችን ለመመለስ 50 ዓመት ሊጠይቅ እንደሚችል ነው የከተማ መሠረተ ልማት ግንባታ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የገለጹት። አፋርም ዉድመቱ ብዙ ነዉ። ክልሉቹ ከደረሰባቸው አደጋ ለመውጣት ካላቸው የአቅም ዉሱንነት አንጻር ነገሮች ቀላል ሊሆኑ እንደማይችል ይገመታል። ነገር ግን አሁን እያየነዉ ያለነዉ የዳያስፖራው መነቃቃትና ኢትዮጵያን ባይነት፣ የሕዝቡ አንድነት ፣በአገር ቤት ያለዉ በጋራ ችግር የመጋፈጥና የመተጋገዙ መንፈስ ከቀጠለ ሁሉም ነገር በአጭር ጊዜ ሊስተካከል እንደሚችል አምናለሁ። ህወሓት የተባለ አጥፊ ወንበዴ ቡድን ከመቀሌ ተነስቶ፣ “ሚሌን ልቆጣጠር ነዉ፤ አዲስ አበባን ተዋት በቃ ገብተናል ማለት ይቻላል” በሚል፣ ከውጪ ሆነዉ የሚመሯቸውን የአሜሪካ ነጭ ጁንታዎችና ሚዲያዎች ለምሳሌ እንደ ብሊንከን፣ ጀፍሪ ፌልትማን፣ ሲ.ኤን.ኤን. የመሣሠሉትን ጮቤ አስረገጡ።
የአሜሪካ ኤምባሲም “ህወሓት ደርሷል፣ የጸጥታ ችግር አለ፤ ዜጎቼ ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ ዉጡ” ሲሉ፣ በተደጋጋሚ የህወሓት ልሳን ከሆኑት ትግራይ ሚዲያ ሓውስና ድምፂ ወያነ ትግራይ ባልተናነሰ ሕዝብን የማዋከብ ሥራ ተያይዛዉ ነበር ። ነገር ግን ከፈረንሳይ እና ከተወሰኑ

የአውሮፓ አገራት ውጭ አንድም የአሜሪካን ጥሪ የሠማ አልነበረም። የሚገርመው እንዲህ እያሉ ከመቃብር ወደቤተ መንግሥት ባንቀልባ አዝለው ለማስገባት ሽር ጉድ ሲሉለት የነበረው ህወሓት፣ በአፋርና በአማራ ክልል ስለፈጸማቸው የጦርነትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ምንም አለማለታቸው ነዉ።

በዚህ መልኩ ህወሓት አዲስ አበባ ልገባ ነዉ ቀናት ብቻ ነዉ የቀረኝ ሲል፣ የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛዉ የደስታ መግለጫቸዉን እንዲህ ነበር ያበሰሯቸው፣ ‹‹ህወሓቶች አዲስ አበባ እንዳትገቡ፤ ዛሬ እንደበፊቱ የሚቀበላችሁ የለም። የበለጠ እልቂት ይፈጠራል። ስለዚህ ባላችሁበት እርጉ›› አለ። በሚቀጥለውም አዲስ አበባ የመጣው ጄፍሪ ፊልትማን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አገኘ። ያነጋገራቸዉም ስለድርድር ነበር። ህወሓት በር እያንኳኳ ስለሆነና ስለተቃረበ ፈጥናችሁ ለድርድር ተቀመጡ ብለዉ ወደ አሻጥረኛዋ አገራቸዉ ተመለሱ። ሰውየው አሜሪካ ሲደርሱ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር ማምራታቸዉን ሰሙ። ሚሌን ልቆጣጠር ነው ያለዉ የፕሮፓጋንዳ ማሽኑ ህወሓት በሳምንት ዉስጥ ከካሣ ጊታ አንስቶ ሙሉ አፋርን የለቀቀበት እግሬ አዉጭኝ ሩጫ አጀብ ሳያሠኝ አልቀረም። በቀጣይም ምናልባት ከኹለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ለዉንብድና ከገባባቸዉ የአማራ ክልል ከተሞች ተጠራርጎ ተሸኜ።

ይህ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ የተገኘው ወታደራዊ ድል ጠቅላላ ኢትዮጵያዉያንንና የኢትዮጵያ ደጋፊዎችን በትልቁ ያነቃቃ ነበር። በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ በተቀናጀና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመራ ጥምረት የተገኘው ዉጤት በርካቶችን አስደምሟል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለሌሎች አርአያ ሁነዋል። ህወሓት ይዞት የመጣውን ያሠለፈዉን ተዋጊ ካራገፈ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች፣ ‹ማሬ፣ልክነሽ ወይም በላይነሽ አመዴ› የሚል ቅፅል ሥም በወጣላት ‹ድሮን› አማካይነት ጭዳ ጭዳ ሁኖ ያሰበውን ማሳካት አልቻለም። በዚህ መልኩ በዕብሪት ተወጥሮ ከ500ኪ.ሜ. በላይ ለስድስት ወር የተመኘው ሥልጣን ቀዠት ሆኖ ወደትግራይ ተመልሷል። ክብር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ለልዩ ኃይል አባላት። ያዉ ፈፅሞ አውነት የማያውቀውና ሽንፈት የማያምነው ህወሓት በለመደው የቅጥፈት ከያዝኳቸው አካባቢዎች ያፈገፈኩት ለስትራቴጂ ነው ብሏል። ያዉ የፈረደበትና ሳያላምጥ የሚሠለቅጥ የህወሓት መንጋ ደጋፊ ስላለ ይህንን አምኖ ተቀብሏል። ህወሓት እግሩ መቀሌ ሲረግጥ ልጄስ/ልጆቻችንስ የሚል የለም። አሁን ላይ ዐቢይ እየመጣ ነዉ፤ ትግራይን መጠበቅ አለብን በሚል ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡ ማሰብ እንዳይችል ሆኗል። አሁን ህወሓት እየሠራ ያለዉ አዲስ ኃይል መመልመል ነዉ፤ ይሄ ደግሞ አንድም በድጋሚ ለመተንኮስ ዝግጅት ሲሆን፣ ሌላኛዉ የግብጹ ጋዜጠኛ እንዳለዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ትግራይ እንዳይገባ ለማድረግ ነው። ይሁን እንጂ በትግራይ ‹ጂኖሳይድ› እያሉ ሬሳቸዉን ለቃቅመው ዓለም አቀፍ በቀቀኖቻቸዉን ለመሣብ ያደረጉት ጥረት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ጁንታዉን ተከትሎ ባለመግባቱ ሬሳቸውን ታቅፈዉ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል ።

የመከላከያ ሠራዊት ተከትሎ ትግራይ ባለመግባቱ ጩኸታችን ተቀማን በሚል ካልገባችሁ የሚል ጉትጎታ ዉስጥም ነበሩ። ህወሓት ከዚህ በኋላ ከቻለ ለዳግም ትንኮሳ ነዉ እየተዘጋጀ ያለዉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ክልል ዉስጥ በነበረባቸው ወራት የደረሰበት ግፍና በደል የሚታወቅ ነዉ። ይህ በደል እያለ የኢትዮጵያ መከላከያ ትግራይ ክልል ገብቶ እንዲማገድ አለመደረጉ ብልህ ዉሳኔ ነዉ ባይ ነኝ። በተገኘዉ ወታደራዊ ድል ኮርቻለሁ። የትግራይ ልኂቃን ቆም ብለዉ ካባለፈው ዓንድ አመት ከግማሽ ተምረዉ ህወሓትን ኢትዮጵያን ማፍረስ አትችልም በቃህ ሊሉት ይገባል። ሕዝባቸዉን ማስተባበር አለባቸው። በአገር ዉስጥ ያለዉ ትግራዋይ ህወሓትን በገዛ ፈቃዱ በቃህ በማለት የትግራይ ሕዝብን በተለይም ወጣቱን ቢታደጉት መልካም ነዉ እላለሁ።

ድል ለኢትዮጵያ !
ኢትዮጵያ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !
ጁሃር ሳዲቅን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ያገኙዋቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here