ዕሮብ ታህሳስ 27/2014 (አዲስ ማለዳ) በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ ዜጎችን ለሞት እየዳረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ረሺድ በድርቁ ምክንያት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ለአሐዱ አረጋግጠዋል፡፡
በጥቅምት መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ በክልሉ የሚገኙ 9 ዞኖች ለድርቅ ተጋልጠው የነበረ ሲሆን አሁን ድርቁ ወደ 10ኛው ዞን መሸጋገሩንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም በተለይም በክልሉ 4 ዞኖች በዳዋ ፣ አፍዴራ፣ ሸበሌ እና ቆራሔ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 1 መቶ 46 ሺሕ 8 መቶ 6 እንስሳት መሞታቸውን ገልፀዋል፡፡
በድርቁ የሚሞቱ እንስሳት ቁጥር በቅርብ ቀናት ሊጨምር እንደሚችል ስጋት መኖሩንም ጠቅሰው ፤ በድርቁ የተነሳም በክልሉ የሚገኙ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሕዝብ ለችግር መጋለጡን አስረድተዋል፡፡
በሚያዚያ የሚጠበቅ ዝናብ እንዳለ የገለፁ ሲሆን ዝናብ ካልዘነበ ድርቁ ከዚህም በላይ የከፋ እንደሚሆንና በርካታ ዜጎችን ሊያሳጣ እንደሚችል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




