ፓርቲው ወደ አገራዊ ፓርቲ እንደሚያድግ አስታውቋል
በቅርቡ ክሳቸው ተቋርጦ ከዕሥር የተፈቱ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች የመንግሥት ዳግም ዕሥር ማስፈራሪያን እንደማይቀበሉት እና ሠላማዊ ትግል እንደሚቀጥሉ ገለጹ።
መንግሥት ታኅሣሥ 29/2014 ክሳቸውን ተቋርጦ ከዕሥር በፈታቸው ዕሥረኞች ጉዳይ ላይ ጥር 1/2014 በተካሄደው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት የምረቃ መድረክ ወቅት ባደረጉት ንግግር ማብራሪያ የሠጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ሰዎች የተሠጣቸውን ዕድል በአግባቡ ካልተጠቀሙ የክስ መዝገባቸውን መምዘዝ እንደሚቻል መግለጻቸውን ተከትሎ፣ ከዕሥር የተፈቱት የባልደራስ አመራሮች ጥር 5/2014 በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስፈራሪያ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
የባልደራስ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝደንት እስክንድር ነጋ በጉዳዩ ላይ በሠጡት ማብራሪያ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዳግም ዕሥር ማስፈራሪያ መልዕክት ቢያስተላልፉም፣ “አርፈን አንቀመጥም፤ ሕግ አንጥስም፤ ሠላማዊ ትግል እንቀጥላለን” ብለዋል። እስክንድር አክለውም፣ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ ለማውጣት በተሰጠን ሠላማዊ መንገድ ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ዳግም ክስ መቀስቀስ የሰጡት ሐሳብ ተቀባይነት የለውም ያሉት የባልደራስ አመራሮች፣ ትግላቸውን በሠላማዊ መንገድ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። ምናልባትም መንግሥት ክስ ቀስቅሶ ቢያሥረን የፓርቲው ዴሞክራሲያዊ ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ የሚለወጥ ነገር አይኖርም ብለዋል።
“መንግሥት አርፈው ይቀመጡ፤ ክሱ ተቋርጧል ማለት በፈለግንበት ስዓት እናንቀሳቅሰዋለን ማለቱ ሥንኩል ሐሳብ ነው፤ የማያራምድ ሐሳብ ነው” ያሉት ከዕሥር የተፈቱት የፓርቲው አመራር አስካለ ደምሌ፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንደምትገኝ ጠቁመዋል። አክለውም፣ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ኹኔታ ላይ እያለች አርፈን ልንቀመጥ አይገባም ያሉ ሲሆን፣ ሥጋት ሊኖርብን አይገባም ብለዋል።
መንግሥት የአገርን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ መወሠን እንደሌለበት ፓርቲው በመግለጫው አሳስቧል። በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሠላም ሊገኝ የሚችለው መንግሥት ተጠያቂነትን እና ፍትሕ ሲያሰፍን ብቻ ነው ያለው ፓርቲው፣ ከዚህ መርህ በተቃራኒ መልኩ የሚደረግ ማንኛውም ቁማር አገርንን እና ሕዝብን መልሶ ወደ ችግር እንደሚከት አያጠያይቅም ብሏል።
መንግሥት ምዕራፍ አንድ ያለዉን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ “ትልቅ አደጋ ያዘለ” መሆኑን በመግለጽም፣ “ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሬ መታገሌን እቀጥላለሁ” ሲል ባልደራስ ገልጿል። ይደረጋል የተባለው የምክክር ሒደትን በተመለከተ ባለቤቱ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሲቪክ ተቋማት መሆናቸውን በማስታወስም፣ ሒደቱን ኹሉም ባለድርሻዎች በባለቤትነት እንዲመሩት ጠይቋል።
የምክክሩ ቅድመ ኹኔታ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መሆን አለበት ያለው ባልደራስ፣ በሠላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ያለ ቅድመ ኹኔታ መቀበል ይገባል ሲልም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል፣ ፓርቲው ከክልላዊ ፓርቲ ወደ አገራዊ ፓርቲ እንደሚያድግ የፓርቲው መሪ እስክንድር ገልጸዋል። የፓርቲው ከክልላዊ ወደ አገራዊ ፓርቲነት የሚያደርገው ዕድገት በቀጣይ በሚየካሂደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደሚወሠን ተገልጿል። ባልደራስ እስካሁን በነበረው የፖለቲካ እና የምርጫ ተሳትፎ አዲስ አበባ ላይ መሠረት አድርጎ ሲሠራ የነበረ ፓርቲ ነው።
ተመሳሳይ ርዕሶች
“መንግስት ከህወሃት ጋር ተደራደር ቢባል እንኳን ‘ህዝቤ አይፈቅድልኝም’ ማለት አለበት”፦ባልደራስ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
ባልደራስ ህወሓትን ከመቃብር ለማንሳት የሚደረገውን የዓለም ዐቀፉ ሴራ መመከት እንደሚገባ ገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
የአዲስ አበባን ምርጫ ውጤት ያልተቀበለው ባልደራስ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014



