በአማራ ክልል ከ1 ሚሊዮን በላይ አባወራዎች የጤና መድኅን ክፍያ የመክፈል አቅም የላቸውም ተባለ

0
902

በአማራ ክልል ህወሓት ጥቃት በፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባወራዎች እና ዕማወራዎች፣ በዚህ ዓመት ጥር ወር የሚከፈለውን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ክፍያ ለመፈጸም መቸገራቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
በዓመቱ ጥር ወር ላይ አዋጥተው ለአንድ ዓመት ሕክምና ሲያገኙ የነበሩ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚዎች፣ ሀብት ንብረታቸው ላይ ጉዳት በመድረሱ በዚህ ዓመት ይህን ማድረግ የተቸገሩ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በዚህም፣ ከዋግኽምራ በስምንቱም ወረዳዎች፣ በሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ እንዲሁም ከፊል በሰሜን ሸዋ የሚገኙ፣ በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን 58 ሺሕ 127 አባውራዎች/እማወራዎች ክፍያውን መፈጸም የማይችሉ መሆናቸውን ክልሉ አሳውቋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሀብት አሰባሰብ አስተዳደርና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጀኔራል አዲሱ አበባው፣ እነዚህን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባወራዎች/አማወራዎች ለማገዝ እና የጤና መድኅን አባልነታቸውን ለማስቀጠል፣ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ እና ጤና ቢሮ በጋራ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠሩ እና ለዚህም የባንክ አካውንት መከፈቱን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

በጤና መድኅን አገልግሎት ኹሉም ሰው ይታመማል ተብሎ ሳይሆን ገንዘብ የሚያዋጣው የማያመው የሚያመውን ለመርዳት ስለሆነ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በክልሉ በጦርነቱ ያልተጎዱ አካባቢዎች ለራሳቸውም ለወገኖቻቸውም ገንዘብ እንደሚያዋጡ አብራርተዋል።
ሌሎች ባለሀብቶች፣ የግል ተቋማት፣ እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞችም የሚችሉትን ያህል በመክፈልና ለማይችሉ ወገኖች ክፍያ በመፈጸም፣ ተጎጅዎቹ አባልነታቸው እንዲቀጥል ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም፣ በአካባቢዎቹ ያሉ የጤና ተቋማት የወደሙ ቢሆንም፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በነጻ እንዲታከሙ እና በባለፈው ዓመት የጀመሩት አገልግሎታቸው አንዳይቋረጥ መደረጉንም አንስተዋል።
ኃላፊው በክልሉ ስለሚተገበረው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አያይዘው ባደረጉት ገለጻ፣ አሁን ባለንበት የጥር ወር ውስጥ የአባላት ምዝገባ እና የአባልነት ክፍያ እየተካሄደ መሆኑን አንስተዋል።

የባለፈው ዓመት የጤና መድኅን ሽፋን የተጠናቀቀው ታኅሣሥ 30 መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ በዓመቱ 67 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ነበር ነው ያሉት።
በዚህም፣ 1 ቢሊዮን 29 ሚሊዮን ብር ተዋጥቶ ለአገልግሎት እንደዋለና፣ የጤና መድኅን አገልግሎት 52 በመቶ ለሚሆነው የክልሉ ሕዝብ ተደራሽ እንደነበረ ገልጸዋል።

ሆኖም፣ በክልሉ በበጀት ዕጥረት ምክንያት ዓመቱ ሳይሞላ አገልግሎት የሚያቋርጡ የተወሰኑ የጤና ተቋማት መኖራቸውን ተከትሎ፣ ይህን ለመቅረፍ በ2012 መመሪያ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

ለበጀት ዕጥረት መከሠት ዋናው ምክንያትም ታካሚዎች ከግል የጤና ተቋማት የሚያጠፉት የተጋነነ የሕክምና ወጪ በመሆኑ፣ በመመሪያው መሠረትም በቅድሚያ የመንግሠት የጤና ተቋማት በግብዓት እንዲሟሉ ተወስኗል ብለዋል። ይህ ሳይቻል ቀርቶ ተገልጋዮች ወደ ውጭ ቢወጡ እንኳን ከቀይ መስቀል፣ ከሕዝብ መድኃኒት ቤት እና ከከነማ መድኃኒት ቤቶች ጋር ውል በመፈጸም በነጻ አገልግሎት እንዲያገኙ መመሪያው ማዘዙን ነው የገለጹት።

ችግሩ ከዚህም ያለፈ ከሆነ፣ የግል ተቋማትን በጨረታ አወዳድሮ ታካሚዎች ነጻ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ከዚህም ብሶ የግል ጤና ተቋማት ሔደው ቢታከሙ በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ ልክ የከፈሉት ገንዘብ ይመለስላቸዋል ሲሉ ግልጽ አድርገዋል።
በሌላ በኩል፣ የፌዴራል ጤና መድኅን አጄንሲ በዚህ ዓመት 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በአገር አቀፍ ደረጃ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን አስመልክቶም በመንግሥት በኩል ድጎማ ለማድረግ ወይም ፈንድ አካውንት ለመክፈት የውሳኔ ሐሳብ መኖሩንም አመላክቷል። በአማራ ክልል ከተቸገሩ ተጠቃሚዎች ሌላ፣ በአፋር ክልል አንድ ወረዳ (ጭፍራ) ብቻ የጤና መድኅን ክፍያ ለመክፈል ችግር ያጋጠማቸው ነዋሪዎች መኖራቸውን ነው ያስረዳው።

ተመሳሳይ ርዕሶች 

በአማራ ክልል የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ መገንቢያ ዕቅድ ለማዘጋጀት ጥናት እየተደረገ ነው – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በአማራ ክልል የወደሙ የጤና ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር ጥናት እየተካሄደ ነው – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በአማራ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ ሆስፒታሎች የጤና መድኅን አገልግሎት ማቋረጣቸው ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በአማራ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ ሆስፒታሎች የጤና መድኅን አገልግሎት ማቋረጣቸው ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here