በሱማሌ ክልል በተከሠተው ድርቅ የዱር እንስሳት ለአደጋ መጋለጣቸው ተገለጸ

0
1481

በምስራቅ አፍሪካ ብቻ የሚገኘው ዲባታግ ብርቅዬ እንሰሳ ያለበት ሁኔታ አይታወቅም

በሱማሌ ክልል በተከሠተው ድርቅ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የዱር እንስሳት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ።
የክልሉ ማኅበረሰብ በብዛት አርብቶ አደር በመሆኑ ግጦሽ ፍለጋ የዱር እንስሳቱ ወደሚኖሩበት ቦታ ከብቶችን ይዞ በመግባቱ፣ እንስሳቱ እየተረበሹ መሆኑን የገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መልካሙ አይቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት በተለይ በገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚኖሩ የዱር እንስሳት ቦታቸውን ጥለው ከመሰደድም ባሻገር፣ ከፍተኛ መረበሽ እንደሚያጋጥማቸው ነው ኃላፊው የጠቆሙት።
ኃላፊው አክለውም፣ ድርቁ በዚህ ወር ያበቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ ያ የማይሆን ከሆነ በፓርኩ ውስጥ ለሚገኙ የዱር እንስሳት ውኃ በቦቴ ለማቅረብ መታሠቡን ጠቁመዋል።

በክልሉ የዱር እንስሳት የሚገኙባቸው የተለያዩ ቦታዎች ቢኖሩም፣ ቦታዎቹ ተከልለው ጥበቃ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ፣ በድርቁ ምክንያትም ይሁን በሌላ እንስሳቱ የሚደርስባቸውን አደጋ በቀላሉ መቆጣጠር አለመቻሉን አክለው ገልጸዋል።
ለአብነትም ኦጋዴን አካባቢ ዲባታግ የሚባል በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ ሳር በል እንስሳ ቢኖርም፣ ይህ ብርቅዬ እንስሳን ጨምሮ ሌሎችም በምን ኹኔታ ላይ አንዳሉ አይታወቅም ነው ያሉት።

ወደ ባሌ አቅራቢያ ጨረቲ በሚባል ሥፍራም እንዲሁ ቀጭኔዎች፣ ጀረሩክ እና የሜዳ ፍየሎች የሚኖሩበት ቦታ ቢኖርም፣ አሁን ላይ እንስሳቱ በምን ዓይነት ኹኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ያዳግታል ሲሉ ገልጸዋል።
የዱር እንስሳት መገኛ ቦታዎች ተከልለው ጥበቃ ካለመደረጉ በተጨማሪ፣ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ኹኔታም እንስሳቱ ለገጠማቸው አደጋ ምክንያት መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ከሞያሌ በስተሰሜን ምስራቅ የሚገኘው ገራሌ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ ብቸኛ ሲሆን፣ 1734 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ሥፋት አለው ተብሏል።

በውስጡም ቀጭኔ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አቦ ሸማኔ፣ የሜዳ ፍየል፣ ጀረኑክ እና የተለያዩ ሥጋ በል እና ሳር በል እንስሳት፣ ብሎም የአዕዋፋት ዝርያዎችን የያዘ መሆኑ ተጠቁሟል። ከፓርኩ በተወሰነ ርቀት ላይም ዝሆን እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሠተው ድርቅ ምክንያት በቦረና ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ የዱር እንስሳት በቅርቡ የሞቱ መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

የክልሉ የዱር እንስሳት ፓርኮች እና ኢኮቱሪዝም ዳይሬክተር መሐመድ ኑር ጀመል ለአዲስ ማለዳ ከሠጡት አስተያየት መረዳት የተቻለው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዱር እንስሳት ላይ በጣም የከፋ የሚባል ጉዳት አለመድረሱ ሲሆን፣ ነገር ግን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እስከ ሞት የደርስ ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ መሆኑን ነው።

በቅርብ ቀን አራት የሜዳ አህያዎች መሞታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የሜዳ አህያዎቹ በቁጥር ትንሽ በመሆናቸው የሞቱትን ማወቅ ተቻለ እንጂ፣ ለመከታተል የማያመቹ ቁጥራቸው በዛ ያሉ እንስሳትም እየሞቱ መሆኑን አመላክተዋል።
አክለውም፣ አሁን ላይ በሕይወት ካሉት እንስሳት ብዙዎቹ የመክሳት እና የክብደት መቀነስ ይታይባቸዋል፤ ድርቁ በዚህ ከቀጠለ እንደሚሞቱ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፣ ከዝንጀሮዎች በተጨማሪ በተለየ ሁኔታ ውኃ የሚያስፈልጋቸው እንደ ከርከሮ ያሉ የዱር እንስሳትም ከፍተኛ ጉዳት እንዳጋጠማቸው አመላክተዋል።

በርከት ያሉ የዱር እንስሳትም ውኃ እና ግጦሽ ፍለጋ ከፓርኩ ክልል ውጭ እየተሠደዱ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በዚህም በአካባቢው ያለውን አርሶ አደር ሰብል በመብላትም ሌላ ችግር መፍጠራቸው ተገልጿል።
ከፓርኩ ውጭ የሚሰደዱት የዱር እንስሳት ሊሄዱ የሚችሉት ወደ ኬንያ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ሆኖም በሰሜን ኬንያ ያለው ድርቅ በቦረና ካለው በጣም የከፋ በመሆኑ ወደዚያ ይሰደዳሉ ብለው እንደማይገምቱ ተናግረዋል።

ድርቁ አሁን ካለው በበለጠ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩ ከእኛ አቅም በላይ በመሆኑ አገራዊ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀናል ነው ያሉት። በዚህም ለዱር እንስሳቱ በምን መንገድ ውኃ እና ምግብ መቅረብ እንዳለበት የሚያጠና ኮሚቴ በፌዴራል ደረጃ መቋቋሙን ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here