የምንተማመንበትን እንወቅ!

0
783

“ሠውን ውደደው እንጂ አትመነው” እየተባልን ያደግን ትውልዶች፤ በቡድንና በብዛት፣ በጉልበትም መተማመን ከጀመርን ከራርመናል። ሠው በሠውነቱ ሊከበርና ሊወደድ ይችላል። ከዛ በላይ ግን ልንተማመንበትና ልናምነው እንደማይገባን በቅዱሳን መጻሕፍት ጭምር የተጠቀሰ ነው። ማመን ኹሉን የፈጠረ አምላክን ብቻ እንደሆነ በሚሰበክበት አገር፣ አሁን አሁን ዘመናዊነት ይመስል በፍጡርና በቁስ መተማመን ተጀምሯል።

በወላጆቹ ሀብትም ሆነ ጉልበት እየተመካ ያደገ ልጅ በኋላ ላይ ከወላጆቹ የሚበልጥ እንዳለ ሲረዳ ይበልጣቸዋል ብሎ በሚያምነው ሰውም ሆነ ግዑዝ ነገር ቢተማመን ላይገርም ይችላል። አንድ ሰው ባዕዳንን ተማምኖ ቤተሰቦቹንም ሆነ ያደገበትን ማኅበረሰብ የሚከዳውና ለሌላ አሳልፎ የሚሰጠው ከአስተዳደጉ በጀመረ የተዛባ አመለካከት ነው። ዕውቀትና እምነት ላይ መሠረት ያላደረገ መተማመን እንደማያዋጣ እስከቅርብ ጊዜ በነበሩና በደረሱ መከራዎች መገንዘብ ይገባናል። ለሠው መድኀኒቱ ሠው ነው ቢባልም፣ ለመድኀኒትም ገደብና መጠን እንዳለው አዲስ ማለዳ ታምናለች።

“ሩቅ ካለ ዘመድ ይሻላል ጎረቤት” የሚሉ ለሰው ልጅ ያልተገባና የተጋነነ እምነት እንዲኖረን የሚያደርጉ፣ እንዲሁም “ገንዘብ ካለ በሠማይ መንገድ አለ” የሚሉ በሚገባው ላይ ሳይሆን በመገበያያ ቁስ ላይ ፈፅሞ እንድናመልክ የሚያደርጉ ሳናውቃቸው የለመዱብን አባባሎች እስከዛሬም አሉ። የሠው ልጅ ተረዳድቶ ተጋግዞ እርስ በርሱ እየተደጋገፈ መኖሩ የሚበረታታ ቢሆንም፣ አንዱ በአንዱ ተማምኖ ወይም የተወሰነ ቡድን ከሌላው በብዛትም ሆነ በአቅም መብለጡን ተማምኖ ሌላውን ያንሳል የሚለውን ለመበደል መነሳቱ ግን መቼም ቢሆን በማንም ቢፈፀም ሊኮነንና ሊወገዝ ይገባል።

ለጉልበተኛም ጉልበተኛ አለው እንደሚባለው ጉልበቱን የተማመነ መድከሙ እንደማይቀር እድሜ በራሱ አስተማሪ ነው። ሰዎች የሚመኩበት ነገር እንደግንዛቤያቸው የተለያየ ቢሆንም የሚያመሳስላቸው ባሕሪ አለ። በሥራቸው ወይም በፈጣሪያቸው ከመተማመን ይልቅ በአንድ ጀንበር ሊጠፋና ሊቀር የሚችልን ነገር ትልቅ ቦታ በመስጠት አለኝታቸው ሲያደርጉት ይስተዋላል። በሀብት፣ በሥልጣን፣ በመልክ፣ በቡድን፣ በጉልበት፣ በዘመድ፣ በችሎታና በእውቀታቸው የሚተማመኑ፣ እንዲሁም በሰውና በአገር የሚተማመኑ ግለሰቦችንም ሆነ መንግሥታትን መመልከት የተለመደ ነው።

ያለእነሱ መኖር አልችልም ከሚል የተሳሳተ አረዳድ በመነሳት፣ እንዲሁም ለራስ ያለ አመለካከትን በማሳነስ እንዲህ ራስን ችሎ ለመቆም የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንደሚደረስ የሥነልቦና ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል። አንዳንዶች መመካትን ከፍርሃት ሲያገናኙት ሌሎች ደግሞ ተስፋ ከመቁረጥና ከአቅመ-ቢስነት ስሜት እንደሚመነጭ ይናገራሉ።

በራስ መተማመን እንዳይኖር የሚያደርገው ያልተገባ መተማመን ነው በሚለው ብዙዎች ይስማማሉ። ይህን የመሰለውን የሥነልቦናም ሆነ የአመለካከት ቀውስ ለመቀነስና በጊዜ ሂደት ለማጥፋት ቀዳሚው፣ የችግሩን መንስዔ አውቆ ለመቀየር ቁርጠኛ አቋም መያዝ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሥልጣን መመካት የሚባለው ፅንሰ ሐሳብ በሕግ የተከለከለ፣ ለሕገወጥ ተግባር መሠረት የሆነና ታችኛው ከሚባለው የሹመት እርከን ጀምሮ እንደ ሥልጣኑ ግዝፈትና እልቅና እየጨመረ የሚሄድ ነው። ሠው በሥልጣኑ፣ በሀብቱና በጠባቂዎቹ እንዲሁም በታጠቀውና አይዞሁ በሚለው እንዲተማመን የሚያደርገው በርካታ ምክንያት መኖሩ ይታመናል።

ድህነት አንዱና ግለሰቦችንም ሆነ መንግሥታትን ተለጣፊ ሆነው በሌላ እኩያቸው እንዲተማመኑ የሚያደርግ ዋናው መንስዔ እንደሆነ ይነገራል። እንዲህ አይነት መተማመኖች በአገራት መካከል የጦር ቃልኪዳን በቡድን ሆኖ በመፈራረምም ሆነ የተናጥል የኹለትዮሽ ስምምነቶችን በማድረግ የሚገለፅ ነው። እነዚህ ጊዜያዊ መተማመንን የሚፈጥሩ የመንግሥታት ድርጊቶች በአብዛኛው ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም።

ነገሩን በኢትዮጵያ ታሪክ መሠረት ከቃኘነውም ከጠቀመን የጎዳን ይበልጣል። ጣሊያን ኹለት ጊዜ ቅኝ ለመግዛት ከመውረሯ አስቀድሞም ሆነ በኋላ ከየመንግሥታቱ ጋር ስምምነት ተፈራርማ ነበር። ኢትዮጵያም ብወረር አጋዥ ያስገኘኛል በሚል እሳቤ የዓለም ጎራ ውስጥ ገብታ የሚቀርባትን እየፈለገች ወዳጅ ለማበጀት መጣር ከጀመረች 500 ዓመታት አልፈዋል። በ15ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መንግሥት እስከዛ ጊዜ ድረስ በአምላክ ይተማመን የነበረውን ብቸኛ መተማመኛውን በመዘንጋት ከፖርቱጋል ጋር ወዳጅ ለመሆን በደብዳቤ ልውውጥ እንቅስቃሴ በይፋ የጀመረ ሲሆን፣ ጠላቴ የሚለው ቡድን ደግሞ የፖርቱጋል ጠላት ሆና ዘመኑን ከዘለቀችው ቱርክ ጋር በማበር የዓለሙን የጥንት ጦርነት ደጃፋችን አምጥተናል።

በወቅቱም ሆነ እስካሁን በየትኛውም ጎራ ተሰልፈው ሕዝባቸውን ያጋደሉ፣ የተማመኑበትና ቃል የተገባላቸው ድጋፍ እንደጠበቁት ሳይሆንላቸው ቀርቷል። የአንዱ ወገን መተማመኛ የነበረ ኃይል ዘግይቶ ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ሲያግዝ፣ የሌላው ደግሞ በተፈለገበት ወቅት ሳይገኝለት ጥሎ እንደሄደ በታሪክ መዛግብት ሠፍሯል። እንግሊዝ የ‹ሒወት ውል›ን አሽቀንጥራ የተሳለቀችብን ወይም የቅርቡ የሊግ ኦፍ ኔሽን ክሕደት፤ በሌላ ተማምኖ እጅን አጣጥፎ የመቀመጥን እሳቤ መጥፎ ውጤት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ክስተት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማመላከት ትፈልጋለች።

በዘመናችን ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ጎራ ተሰልፎ ኢትዮጵያን ለማዳን መሞከር እንደማያዋጣ ሶሪያንም ሆነ ሊቢያንና የመንን በምሳሌነት በማንሳት ችግሩን በማስረጃ ማሳየት ይቻላል። ሱማሌ ደጋግማ የተከዳችበትን ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ባይሆንም ወዳጆቿን እንድትቀያይር የተደረገበትን ሂደት በማጤን ከስህተቱ መማር ይገባል።

በየትኛውም የዓለም ጦርነት ገለልተኛ አቋም ወስደው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከጥፋትና እልቂት መታደግ ከቻሉ መንግሥታት ለመማር አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደርኩ ነው የሚለው መንግሥት ተግቶ መጣር ይኖርበታል። በፍላጎትና በስሜት ብቻ የሚለወጥ ባለመኖሩ ለእንዲህ ዓይነት ክብርን የሚያዋርድ ሁኔታ የሚዳርጉትን ድህነትን የመሳሰሉ መንስዔዎችን ለማጥፋት ወይም ይዞ የሚመጣውን ቆርጦ ለመቀበል መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ዝግጁ እንዲሆኑ ከቅስቀሳ ሥራ ጀምሮ የሚጠበቀው ነገር ሁሉ ጊዜ ሳይሰጠው መጀመር ይኖርበታል። የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ከመግባታችን በፊትም ሆነ ጥደን ከማልቀስ ይልቅ በእጃችን ያለውን ሳንለቅ ባለን መጀመር ይኖርብናል።

እንደ አዲስ ማለዳ እምነት፤ አገርም ሆነ ሕዝብ የሚተማመንበትን ለይቶ ማወቅ አለበት። ከሞትም ሆነ ከጥፋት ራሱን መስዋእት አድርጎ የሚታደግ ፍጡር እንደማይኖር ሁላችንም በጊዜ ልንረዳ ይገባናል። ሀብትም ሆነ ዝና ጠፊ እንደሆነ የማናውቅ ባንኖርም፣ ያለን ለምን እንደኖረንና ለምን ልንገለገልበት እንደሚገባ መረዳት ይገባናል። ነገሮች የሉንም ብለን የምናስብም፣ ሌላው በገንዘብ የማይተመነውን ክብራችንንም ሆነ ሉዓላዊነታችንን ስለሌለን ብቻ ሊያሳጣን አይገባም።

በሌላ በኩል፣ ሠው በድሎ የሚሸሽ ካልሆነ በቀር ምንም ሳያጠፋ ሊፈራና ሊደበቅ እንደማይገባው ግልፅ ነው። መሪዎችም ሆኑ ግለሰቦች ሁሉንም ማስደሰት ባይችሉም ማንንም ሳያስከፉ ዘና ብለው በየአውራ ጎዳናዎቹ መንሸራሸር እንዲችሉ መሠራት ያለበት ከአሁኑ መሆኑን አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች። ለወደፊት መሪዎቻችን በተግባር የሕዝብ አገልጋይ ሆነው ራሳቸው ሕዝብ ሆነው እንደኅብረተሰቡ መኖር እንዲችሉ ከዜጋው የሚለያቸው የሚተማመኑበት ፍጡራዊ ምክንያት መበጣጠስ ይኖርበታል።

በኹሉም ፈጣሪና በሕዝባቸው መተማመን እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ተለይቶ ጥናት መደረግ ይኖርበታል። ተገቢ ካልሆነ መተማመኛ ለመራቅ ምን ቢደረግ ጥሩ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ በተቻለ ሐሳብ ማንሸራሸር የሚቻልበት መንገድ መመቻቸት አለበት።

አሁን አሁን ‹ጌታዋን የተማመነች በግ…› ውጭ የምታሳድረው ላቷን ብቻ ሳይሆን ጭንቅላቷንም የሆነ ይመስላል። አሁን እየሄድንበት ባለው አቅጣጫ በያዝነው ፍጥነት መንገዱን ሳናሻሽል ከቀጠልንበት፣ ያለአግባብ የተማመንበት ቀድሞን እየጠፋ መውጫ የሌለው ጭንቅ ውስጥ መውደቃችን እንደማቀር በጊዜ መረዳት ይገባናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here