መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ዘጠኝ ንጹሀን...

ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ዘጠኝ ንጹሀን ሰዎችን መግደሉ ተገለጸ

ከ17 በላይ ሰዎች ታግተዋል

የኦነግ ሸኔ ታጣቂ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ዘጠኝ ንጹሀን ሰዎች መግደሉን ጉዳዩን በቅርብ ርቀት ሲከታተሉ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ታጣቂ ቡድኑ በተለይም በሀሮ ሊሙ እና ጊዳ አያና ወረዳ ከዓመታት በላይ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን፤ የነዋሪዎቹን ንብረት መዝረፉና ማቃጠሉ እንዲሁም ሰላም ወደ ሰፈነበት አካባቢ ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎችን እያገተ እንደሚገኝ ሲመላከት መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ የድረሱልን ጥሪ ቢያስተላልፉም እስከ አሁን መፍትሄ እንዳላገኙና ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ወቅት ድረስ ጥቃቱ እንዳልቆመ ነው የተናገሩት።

ባሳለፍነው ጥር 8 እና 9/2014 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአንገር ጉትን ከተማ መንደር አራት አካባቢ የበቆሎ ምርት ሲሰበስቡ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎችን መግደላቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ግለሰብ ‹‹ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል። የስድስቱ አስከሬን ቢገኝም የሦስቱ ሰዎች ግን የት እንደሆነ አይታወቅም።›› ብለዋል።

የስድስቱ ሰዎች አስከሬን ጥቃቱ ከተፈጸመበት መንደር አራትና አምስት ድንበር አካባቢ በጋሪ ተጭኖ ወደ ጉተን ከተማ እንደሄደና በዛው በጉትን ከተማ በሚገኘው መስጊድና ቤተክርስቲያን ጥር 9/2014 የቀብር ስርዓት መፈጸሙን ግለሰቡ አክለው አብራርተዋል።

ሌላኛዋ ‹‹ተፈናቅዬ አንድ ሽኩቻ ቦታ ነው ያለሁት። የቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ ሄጄ ነበር።›› ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፤ ‹‹ብዙ ሰዎች እየተገደሉ ነው። ንብረት እየተዘረፈ፤ ቤትም እየተቃጠለ ነው።›› በማለት ነው የተመለከቱትን የገለጹት።

ሰሞኑን ኦነግ ሸኔ በሰነዘረው ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል የሚሉት ግለሰቧ፤ በተያያዘ ‹‹ይሙቱ ይዳኑ ያልታወቁ ከ17 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ገና አድራሻቸው አልታወቀም።›› ነው ያሉት።

ሰሞኑን በተፈጸው ጥቃት ሰለባ የሆኑት አብዛኛዎቹ በቆሎ ለመሰብሰብ የወጡ ሰዎች መሆናቸው ነው የተጠቀሰው። ይህን በተመለከተም ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ፤ ‹‹እኔ የማውቃቸው ስምንት ሙስሊም ጓደኞቼ ታግተዋል።›› ሲሉ ገልጸው፤ ‹‹ከሟቾቹ መካከል አንዱ በቀን ሥራ የሚተዳደር የአምስት ልጆች አባት ነው።›› በማለት ነው ያስረዱት።

ግለሰቡ አያይዘውም መንገድ ዝግ መሆኑን፤ የእሳት ቃጠሎ አደጋ መኖሩን እንዲሁም የግድያ ጥቃቱ አለማቆሙን አብራርተዋል። ‹‹ዙሪያውን በጥቃት ታጥረን እንዴት እንሁን? መንግሥት ግን የወለጋን ጉዳይ የማይመለከተው እስከመቼ ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል።

ሌላኛው ወደ አዲስ ማለዳ ስልክ ደውለው ጥቆማ የሰጡት ግለሰብ በበኩላቸው፤ ጥቃቱ እንደቀጠለ መሆኑንና የደረሰላቸው አካል እንደሌለ ተናግረዋል። ‹‹ከቶ መንግሥት ዝም ያለን! እውነት ወለጋን አይዳኘውምን? እኛ የመንግሥት ልጆች አይደለንምን? ይህ ሁሉ ሕዝብ እያለቀ ዝም የተባለው ምን ችግር ተገኝቶብን ነው? እንዲያው ለማን እንጩኽ?›› ሲሉ ነው የጠየቁት።

ከነዋሪዎቹ ገለጻ መረዳት የተቻለው ጥቃቱ ሊያቆም ስላልቻለ መንግሥት ቢያንስ እንኳ የተዘጉ መንገዶችን አስከፍቶላቸው ሰላም ወዳለበት ቦታ መውጣቱን የመጨረሻው አማራጭ ሊሆናቸው እንደሚችል ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች