ፍጠኚ!

0
1289

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ጊዜው ወደ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል መስመር እየወሰደን ዛሬ የምናውቃቸውን ሁሉ ‹ኋላቀር› ሊያሰኛቸው እየተጣደፈ ይገኛል። በርካታ አገራት አሁን ይህ ጉዳይ ቤተኛቸው ከመሆን አልፎ የቴክኖሎጂ እኩል ተደራሽነት አጀንዳቸው ሆኗል። የሴቶችና የወንዶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ጉዳይ ላይም በርካታ ጥናቶች እየወጡ ይገኛሉ።

የሕጻናትና የሴቶች እኩል መብት ይመለከተኛል ብሎ ላለፉት 80 ዓመታት ሲሠራ የቆየው ‹ፕላን ኢንተርናሽናል› የተሰኘው ድርጅት በድረ ገጹ ባስነበበው ዘገባ መሠረት፣ ሴቶች ከወንዶች አንጻር ቴክኖሎጂ እና ኢንተርኔት የማግኘት እድላቸው አናሳ ነው። ይህም በአዳጊ አገራት የባሰ እንደሆነ ይጠቅሳል።

የትምህርት ተደራሽነት ገና በቅጡ ያልተዳረሰባትና ጊዜዋን በጦርነትና በግጭት እየበላች በምትገኝ አገራችን ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ ቅንጦት ይመስል ይሆናል። ነገር ግን አንዳንድ የቁጥር መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ቅንጦት እንዳልሆነ መረዳታችን የሚቀር አይደለም።

ለዚህ ማሳያ ፕላን ኢንተርናሽናል ያወጣውን የጥናት ውጤት ስንመለከት፣ በዓለማችን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሥራዎች ከቴክኖሎጂ እና ዲጂታሉ ዓለም ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ስለዚህም ጉዳዩ ላይ ሳንወድ በግድ እንድናተኩር እንሆናለን።

በቅርበት እንኳ የባንኮች አሠራር ላይ የሚታዩ የቴክኖሎጂ ጥቅሞችን እንመልከት። በረዳት የሚጻፍላቸውና በአሻራ የሚፈርሙ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ይልቁንም ሴቶች አሁንም አሉ። በዚህ መካከል አሠራሩ ሁሉ ወደ ቴክኖሎጂ ከተቀየረ ወይ ያንን መከተል አልያም እንደባይተዋር መገለል አይቀርም። ስለዚህ ነው በፍጥነት ዜጎችን በተለይም ሴቶችን ለቴክኖሎጂ ዝግጁና ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው። ተቋማትና ድርጅቶችም ይህን ልብ ሳይሉ እንደማይቀሩ ተስፋ እናደርጋለን!

በነገራችን ላይ በማኅበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ረገድ፣ ጥናቶች እንዳሳዩት ከአምስት ሴቶች መካከል አንዲት ሴት በሚደርስባት ትንኮሳ የተነሳ ከማኅበራዊ ሚድያ ራሷን ታገላለች። ከዛም በበሳ ሴቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሥራዬ ብለው የመሳተፍ እድላቸው ከወንዶች አምስት እጥፍ ያነሰ ነው። ይህም ገና ከአሁኑ ወደፊት ‹የሴቶች የዲጂታል እኩልነት፣ መብትና ደኅንነት ይጠበቅ!› የሚል እንቅስቃሴ ሊያስነሳ እንደሚችል አመላካች ሳይሆን አይቀርም።

እናም ፍጠኚ! በፊት በሆነው ሳይሆን ወደፊት ለሚሆነው ለመሥራትና ከወዲሁ የተስተካከለ እንዲሆን ጣሪ! ‹እናቶቻችን እንዲህ ማድረግ ነበረባቸው!› የምትይው ካለ፣ ከዛም በላይ ዛሬ አንቺ ለነገ የምታቆይውና ልታደርጊው የምትችይው ብዙ ነው። ዓለም መንገዷና አካሄዷ ሁሉ ቴክኖሎጂን መሠረት እያደረገ ነውና ፍጠኚ! ተከተይ! ተመራመሪ! እኩልነትና መብትሽን ከመጠየቅ በተጓዳኝ ሊያመልጥሽ የማይገባው እድል ይኸውልሽ!
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here