የመጠበቅ ኃላፊነት የአገሮችን ሉዓላዊነት መጣሻ ሰበብ

0
986

የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በተለይ በአፍሪካ አገራት ራሱን የቻለ ጉዳይ ሆኖ መነሳት የሚችል ሰፊ አርዕስተ ነገር ነው። ታድያ ብዙ ጊዜ ለዚህ ጣልቃ ገብነታቸው ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› የሚል ምክንያት ይጠቀሳል። ሽመላሽ ወንዳለ ይህን ነጥብ መነሻ በማድረግ በዚህ ጽሑፋቸው ስለ ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› እና ተግባራዊነት መሠረታዊ ጽንሰ-ሐሳብ ዳስሰዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን ከምዕራባውያን አገሮች ጋር ስላላት ፍጥጫና በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እንደ ሰበብ ሊጠቀሙባቸው ስለሚችሉ ምክንያቶች ያነሳሉ። አያይዘውም ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው መፍትሄዎችንም ጠቁመዋል።

በመርህ ደረጃ አገሮች በግዛታቸው ውስጥ ፍጹም ሉዓላዊ ሥልጣን አላቸው። ሆኖም ለዚህ ፍጹም ሉዓላዊነት ልዩ ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› (Responsibility to Protect) በመባል ይታወቃል።

በ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› መርህ መሠረት ሉዓላዊ አገራት በግዛታቸው ውስጥ ያሉ ሰዎችን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። በማናቸውም ምክንያት መንግሥታት ሕዝባቸውን መጠበቅ ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ሕዝቡን ለመከላከል ጣልቃ መግባት ይችላል። በሌላ አነጋገር አንድ አገር ሕዝቦቹን መጠበቅ ካልቻለ የመጠበቅ ኃላፊነቱ ወደ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ይሸጋገራል ማለት ነው።

እ.ኤ.አ. በ2005 ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› አስፈላጊነት ላይ ተስማምተዋል። በስምምነቱ መሠረትም የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲኖሩ በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት በአንድ አገር ውስጥ ጣልቃ ገብነት ሊኖር ወይም ሊደረግ ይችላል። ሁኔታዎቹም የዘር ማጥፋት፣ መጠነ ሰፊ ግድያ፣ የዘር ማጽዳት፣ የጦር ወንጀል እና በስብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው።

ይሁን እንጂ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በሙሉ ድምጽ ካልተወሰነ ጣልቃ ገብነት አይፈቀድም። የትኛውም የምክር ቤቱ አባል ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ከሆነ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አይቻልም። እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ነጥብ፤ ጣልቃ ገብነት ሁልጊዜ ወታደራዊ መሆን አያስፈልገውም። ይልቁንም በእገዳና ማእቀብ መልክም ሊሆን ይችላል። ወታደራዊ ጣልቃ-ገብነት አማራጮች ሁሉ ከተሟጠጡ በኋላ የሚገኝ የመጨረሻው መፍትሄ ነው።

ከላይ በተጠቀሰው ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› ማብራሪያ መሠረት ኹለት የመርሁን ድክመቶች ማየት እንችላለን። አንደኛ፤ የፀጥታው ምክር ቤት ጣልቃ-ገብነትን በሙሉ ድምፅ ካላፀደቀው ከላይ የተጠቀሱት ወንጀሎች እየተፈጸሙ ቢሆንም እንኳ ምንም ዓይነት እርምጃ አይወሰድም። ኹለተኛ፤ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በአንድ ድምፅ ውሳኔ አሳልፈው የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት የሚፃረር እርምጃ መውሰድ ይችላሉ።

‹የመጠበቅ ኃላፊነት› አተገባበሩን ለመመልከት ከመጽደቁ በፊት እና በኋላ የተከሰቱ አንዳንድ አጋጣሚዎችንና የተሰጡ ምላሾችን እንይ፡-
በአፍሪካ፤ በሩዋንዳ እ.ኤ.አ. በ1994 በአገሪቱ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሩዋንዳውያን (800,000 ቱትሲ እና 200,000 ለዘብተኛ ሁቱዎች) ላይ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል። ሆኖም ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አቅሙ የነበራቸው ሁሉም ምዕራባውያን አገራት ግድያውን ለማስቆም እርምጃ አልወሰዱም ነበር። በመጨረሻም ቱትሲዎች በፖል ካጋሜ መሪነት እራሳቸውን ከመጥፋት ታደጉ።

በአውሮፓ፤ በዩጎዝላቪያ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ግድያዎች ከተፈጸሙ በኋላ በኔቶ ጣልቃ ገብነት አብቅቷል። ጦርነቱ ሲያበቃም ዩጎዝላቪያ ፈርሳ በአሁኑ ጊዜ በምዕራባውያን ተጽእኖ ስር ወዳሉ ሰባት ጥቃቅን አገሮች ተቀይራለች።

በአፍሪካ፤ እ.ኤ.አ. በ2011 በሊብያ የነበረውን የውስጥ ግጭት ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ንጹሃንን ለመከላከል በሚል ሰበብ ጣልቃ ገብቶ በመጨረሻ አገሪቱን መንግሥት አልባ አድርጓታል። ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመናቸው ካለቀ በኋላ በሊቢያ የተደረገው ጣልቃ ገብነት ትልቅ ስህተት እንደነበር አምነዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ክስተቶች የሚከተሉትን ነጥቦች መረዳት እንችላለን፡-
አንደኛ ጣልቃ-ገብነት በጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን፤ ይህም ማለት የምዕራባውያን አገራት በሩዋንዳ ውስጥ ጣልቃ ያልገቡበት ምክንያት ምንም ጫይነት የሚከላከሉለት ጥቅም ስላልነበራቸው ነው። በሌላ አገላለጽ ጣልቃ በመግባት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ንጹሃንን ሕይወት ማዳን ለእነሱ ጥቅም ስላልነበረው ነው።

ሌላው ከሶቪየት ኅብረት መፍረስ በኋላ ዩጎዝላቪያ በምሥራቅ አውሮፓ ካሉት አገሮች ጠንካራ ስለነበረች ምእራባውያን በአካባቢው የበላይነታቸውን የሚፈታተን ጠንካራ መንግሥት ማየት ምቾት የሚሰጣቸው አልነበረም። በዚህ ምክንያትም በአገሪቱ የመንግሥት ለውጥ ማምጣት ይፈልጉ ስለነበር የመከላከል ኃላፊነትን ጣልቃ መግቢያ ሰበብ አድርገው ተጠቀሙበት።

እንዲሁም ምዕራባውያን በሊቢያ ጣልቃ የገቡት ሊብያዊያንን ከጋዳፊ ጥቃት ለመጠበቅ ሳይሆን መንግሥት ከነሱ ፍላጎት ውጪ ስለሆነ፤ በዚህ ምክንያትም ከሊቢያ ዘይት ተጠቃሚ መሆን ባለመቻላቸው ነው። በመሆኑም፤ በአገሪቱ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ይፈልጉ ስለነበር የውስጥ ግጭቱ ሲነሳ የመከላከል ኃላፊነትን እንደ ሰበብ ተጠቅመው የጋዳፊን አገዛዝ በመገልበጥ አገሪቱን መንግሥት አልባና እስካሁንም ያልተረጋጋች እንድትሆን አደረጓት።

አሜሪካ እና አጋሮቿ ያለጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔም ቢሆን ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ። ከላይ ባየናቸው ክስተቶች ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላቸው ሩስያ እና ቻይና በዩጎዝላቪያ እና በሊብያ ጣልቃ-ገብነት ላይ ባይስማሙም አሜሪካና አጋሮቿ በማን-አለብኝነት ጣልቃ ገብተው አገር አፍርሰዋል።

ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎችን ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስናመጣ፤ አገሪቱ ከሕወሓት አሸባሪ ቡድን ጋር እየተደረገ ያለውን የውስጥ ጦርነት ለማስወገድ የተቻላትን ጥረት እያደረገች ነው። የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ሲሆን መንግሥት ወታደራዊ ኃይልን ወደ የትኛውም የአገሪቱ ክልል ሊያሰማራ ይችላል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ ኢትዮጵያ በነሱ ሉዓላዊ አስተዳደር ስር ያለች ይመስል መንግሥት ወታደሮቹን ከትግራይ ክልል እንዲያወጣ ትእዛዝ ሲሰጡ ቆይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ዜጎቿንና ጥቅሞቿን ለመጠበቅ በቀጥታ በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ እንደምትገባ አስጠንቅቃለች። ተያይዞም አሜሪካ እና አጋሮቿ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሕይወት ለመጠበቅ ጣልቃ ልንገባም እንችላለን እያሉ ነው። ለዚህ እንዲያመቻቸውም በትግራይ ክልል በኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ብለው ያለ ምንም ማስረጃ መንግሥትን ሲከሱ ቆይተዋል።

ዛቻውና ውንጀላው እንዳለ ሆኖ አሜሪካ ኢትዮጵያ ትእዛዜን አላከበረችም ስትል በቅርቡ ከ‹የአፍሪካ የእድገት እና እድል መርኃግብር፤ አጎዋ› ዝርዝር ውስጥ ሰርዛታለች። ይህም አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን ለማሳየት ጠንካራ ማረጋገጫ ነው። እዚህ ላይ ዋናው ነገር አሜሪካ እና አጋሮቿ ገለልተኛ አለመሆናቸው ነው።

ይህ ማለት በኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት በሕወሓት የተፈፀመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የዘር ማጥፋት እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አውግዘው አያውቁም። በተጨማሪም በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ ባለፉት 6 ወራት በሕወሓት የተፈፀመውን የዘር ማጥፋትና በስብእና ላይ ስለተፈጸሙ ወንጀሎች ምንም አላሉም። ይልቁንም ቡድኑ የፈፀመውን ወንጀል ሕጋዊ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። በተቃራኒው ግን የኢትዮጵያ መንግሥትን ይወቅሳሉ።

እዚህ ላይ ጥያቄ መሆን ያለበት አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ምን ፍላጎት አላቸው? የሚለው ነው። ኢትዮጵያ የምትገኘው ከቀይ ባህር ስትራቴጂካዊ ቦታ አጠገብ ነው። በተጨማሪም አገሪቱ ከጎረቤቶቿ የበለጠ አስፈላጊ የሚያደርጉ ነገሮች አሏት። እነዚህም፤ ታሪካዊ ጠቀሜታ (ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዢዎች ነፃነቷን ያረጋገጠች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ነች)፣ የሕዝብ ብዛት (በአፍሪካ ኹለተኛ ደረጃ የሕዝብ ቁጥር አላት)፣ የቆዳ ስፋት (በአፍሪካ ቀንድ ካሉት ትልልቅ አገራት አንዷ ነች)፣ የተፈጥሮ ሀብት ስጦታ (ውሃ፣ ማዕድናት…ወዘተ) በመሳሰሉት ምክንያቶች ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት ጠንካራ ወታደራዊ ኃይሎች አንዷ ነች። በመሆኑም፤ አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደ ፍቃዳቸው በመዘወር በአካባቢው ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ አገሪቱን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የመቆጣጠር ፍላጎት አላቸው።
ሕወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን መስዋዕት በማድረግ ፍላጎታቸውን እያሟላላቸው ስለነበር ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፍላጎት አስጠብቀው ነበር። ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ጥቅማቸውን በሚፈልጉት ልክ ማስጠበቅ አልቻሉም። በዚህ ምክንያትም በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ እና አጋራቸውን ሕወሓትን ወደ ሥልጣን ለመመለስ እየጣሩ ነው።

ለዚህም ነው ቡድኑ ምንም ቢያደርግ ሲደግፉት የነበሩትና አሁንም በመደገፍ ላይ የሚገኙት። ዓላማቸውን ለማሳካት አሁንም ቡድኑን በተለያዩ መንገዶች እየደገፉ ይገኛሉ። ይህም የሚያመለክተው ምዕራባውያን በሌሎች አገሮች ያደረጉትን ነገር ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› በሚል ሽፋን በኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም እየሞከሩ መሆኑን ነው።

ከላይ ከተገለጹት ማብራሪያዎች መረዳት የምንችለው ምዕራባውያን የመጠበቅ ኃላፊነትን ወጥ በሆነ መልኩ እንደማይተገብሩት ነው። ለዚህ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም፣ ከላይ ከተጠቀሱት ምሳሌዎች እና ማብራሪያዎች ቀላል መደምደሚያዎችን ማግኘት እንችላለን።

እናም ዋናው ጉዳያቸው ሰብአዊ መብት ሳይሆን ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ነው። ‹የመጠበቅ ኃላፊነት›ን ከነሱ ጥቅም በተቃራኒ በሆነ አገር ውስጥ የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ይጠቀሙበታል። እንዲሁም ‹የመጠበቅ ኃላፊነት› እንደ ጠላት የሚቆጥሯቸው አገሮችን ለመበታተን ወይም ለማዳከም ጥቅም ላይ ይውላል።

ስለሆነም፤ ጦርነት እስከቀጠለ ድረስ ኢትዮጵያ የምዕራባውያንን ተጽእኖ ለመጋፈጥ ራሷን በሚገባ ማዘጋጀት አለባት። ምክንያቱም የምዕራቡ ዓለም ወታደራዊ ጣልቃ-ገብነት የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ከላይ ያሉት ታሪኮች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። ምዕራባውያን በእርግጥም ጥቅማቸው አደጋ ላይ እንደሆነ ካመኑ በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን ዲያቢሎሳዊ ተልዕኮ ለማሳካት አንዳንድ እርምጃዎችን ከመውሰድ ወደኋላ አይሉም ይሆናል።

ይህን ስጋት ለማስወገድም ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር ያላትን ውጥረት ከማባባስ ይልቅ ያሏትን ጠቃሚ ማስረጃዎችን ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በመግለጽና በማጋራት ለስላሳ የዲፕሎማሲ ሥራ እየሠራች መቆየት ይኖርባታል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከምሥራቃዊ አጋሮቿ እንደ ሩሲያ እና ቻይና ካሉት ጋር በመሆን የምዕራባውያንን የተስፋፊነት እንቅስቃሴ ለማስቆም መሥራት ይኖርባታል።

ሽመላሽ ወንዳለ፤ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በዓለምአቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ኹለተኛ ዲግሪ አላቸው። በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here