ከብረታ ብረት ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት 723.3 ሚሊዮን ብር የውጭ ምንዛሬ ተገኘ

0
523

በጋዜጣው ሪፖርተር
ከብረታ ብረት ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት 723.3 ሚሊዮን ብር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች መገምገሙን አዲስ ማለዳ ከኢንስቲትዩቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ከዘርፉ የኢንዱስትሪዎች ምርት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በተደረገው እንቅስቃሴ 723.3 ሚሊዮን ብር ወይም 14.646 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1.52 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ተብሏል።

በግማሽ ዓመቱ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 20 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 17 በመቶ መከናወኑንና ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ2.2 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑም ተገልጿል። የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ስምንት ፕሮጀክቶች በቁጥር 100 ሺሕ እና በቶን 619 ሚሊዮን 565 ሺሕ አቅም ይዘው ዘርፉን የተቀላቀቀሉ ሲሆን፣ ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር በንፅፅር ሲታይ ከፍተኛ ዕድገት ያሳየ መሆኑንም ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው።

የኢንዱስትሪዎችን ችግር መሠረት ያደረጉ አራት የምርምር ሥራዎች በባለሙያዎች ተሠርተው መጠናቀቃቸው እና በግማሽ ዓመቱ ለአራት ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለሦስት ሺሕ 817 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉም ተመላክቷል።

በኢንስቲትዩቱ የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በቀጣይ ወራት በሚከናወኑ የ100 ቀናት ዕቅድ ላይ ጥር 12/2014 የተቋሙ ሠራተኞችና ማኔጅመንት ጋር ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ 100 ቀናት ትኩረት በማድረግ የሚያከናውናቸው ሥራዎች በተለይም የማምረት አቅም ማሳደግ፣ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ማጠናከር፣ ገቢ ምርትን መተካት፣ ኢንቨስትመንትን ማሳለጥ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ጥናትና ምርምር ሥራዎችና ሌሎች ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ ጋር የተሳሰሩ ሥራዎች ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራ አስታውቋል።

ኢንስቱትዩቱ በ2013 በጀት ዓመት በአካባቢ ጥበቃ፣ በምርት ጥራት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በግብአት አቅርቦትና ገበያ ትስስር ከዕቅድ አንፃር የተከናወኑ ዝርዝር ሥራዎች እና በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪዎችና በኢንስቲትዩቱ ጠንካራ ቅንጅት ገቢ ምርትን ለመተካት በተሠራው ሥራ 31.848 ቢሊዮን ብር ወይም 177.55 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና በወጪ ንግድ 28.368 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጾ ነበር።

ተቋሙ በ2013 በጀት ዓመት አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ 921 ሚሊዮን 884 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ያላቸው 19 ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውና፣ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ደግሞ 429 ሺሕ 314 ቶን እና በቁጥር 180 ሺሕ 144 አቅም በመያዝ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን በ2013 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ መግለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here