አውራአምባን እንደ መልካም አርዓያ

0
747

አራጋው አሌ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ ወጆ ቀበሌ ውስጥ በምትገኘውና አውራአምባ ተብላ በምትጠራው ቦታ ነው።

አራጋው የአውራአምባን ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ፣ በተለይም አሁን በአገራችን ካለው ጦርነት ጋር በማያያዝ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አጫውተውናል።

አራጋው በአውራምባ ማኅበረሰብ አንድ የተገነዘቡት ነገር ቢኖር፣ ወደ መጣላት ደረጃ የሚያደርሰው በሐሳብ አለመመግባባትና የፍላጎት መለያየት አለመሆኑን ነው።

አንደ አራጋው ገለጻ ከሆነ፣ እንኳን በርከት ብለው ተሰባስበው በሚኖሩ ማኅበረሰቦች፣ ሰው ከራሱ ጋርም ወደ ክርክር የሚገባበት ወቅት እንዳለ አስተዋይ አዕምሮ ያለው ሰው ልብ ሳይለው አያልፍም ባይ ናቸው። ክርክርና ውዝግብ እንኳን በሕብረተሰቦች ዘንድ፣ በአንድ ግለሰብም መከሠቱ አይቀሬ መሆኑን አጽንዖት ይገልጻሉ።

ወደ መጣላትና አለመግባባት የሚያደርሰን በሠሳብ መለያየታችንና የፍላጎቶቻችን ለየቅል መሆን ሳይሆን፣ ‹‹የእኔው ይቀድማል፤ የእኔው ይበልጣል›› በሚል ራስ ወዳድነት ምርኮ ሥር መውደቃችን ነው ሲሉ የተገነዘቡትን ያብራራሉ።

አያይዘውም፣ ኹሉንም ነገር ተቀብለን ወደ መልካሙ ከቀየርነው የሐሳብና የፍላጎት መለያየት አንድ ሊያደርግ እንጅ ሊያጣላ የሚችል አይደለም ይላሉ። የሰውን ተፈጥሮ ጠለቅ ብለን ብንመለከት፣ ነፍስና ሥጋው በፍላጎታቸው ኹሌም ተቃርነው፣ ግን ደግሞ አብረው የሚኖሩ ናቸው፤ ሲሉ አራጋው በምሳሌ አስደግፈው ያስረዳሉ።

እንደ ገለጻቸው ከሆነ፣ የሥጋ ፍላጎት የሥጋ ነው፤ የነፍስ ፍላጎትም የነፍስ ነው። ይህም ፍጹም ተቃራኒ ነው። ቢሆንም ግን ኹለቱም ተለያይተው መኖር አይችሉም። ሥጋ ነፍስ ከተለያት በድን ናት። ነፍስም በእርጥብ ሥጋ ውስጥ እስትንፋሷን ዘርግታ ነው የምትኖረው። እናም ኹለቱ ከተለያዩ ሞት የተባለው ክስተት ይከሰታል።

የሰው ልጅም እንዲሁ ነው ይላሉ አራጋው። የሰው ልጅ በሐሳብና በፍላጎት ልዩነት ቢኖረውም፣ ተቻችሎ ካልኖረ ያኔ መጣላት፣ መካሰስ፣ መሰዳደብ፣ መነቋቆር፣ ከዚህም አልፎ መገዳደል እየተበራከተ ዘርፈ ብዙ ውድመት ወደሚያስከትለው ጦርነት ጥግ ይደርሳል ይላሉ።
ታዲያ በአውራምባ ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ ያስተዋሉት ነገር በማኅበረሰቡ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር፣ በውይይት ይፈታል እንጂ ችግሩ ከብዶ ወደ ጥላቻ እንደማያመራ ነው።

መጣላት የሚጸነሰው ውይይት ግብ ሳይመታ ሲቀር ነው። ውይይት ከግብ የማይደርሰው ደግሞ ጥፋትን ላለማመን በሚደረግ አጉል ድርቅና ነው የሚሉት አራጋው፣ ባደጉበት አካባቢ ያለው ኹሉም የማኅበረሰብ አባል በውይይት ወቅት ጥፋቱን ለመቀበል ቀና እንደሆነ ይናገራሉ።

ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በሌላ አካባቢ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያኖች ሠላምና ፍቅር፣ መተሳሰብና መረዳዳት የሰፈነባት፣ የወቅቱ የእርስበርስ መነቋቆር ያልተጋባባት አውራምባን፣ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች አርዓያ ሊያደርጓት ይገባል ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ላይ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሕገ-መንግስትም ሆነ በኃይማኖት ደረጃ ስለመከባባር፣ ስለመፈቃቀር፣ ስለአንድነት፣ ስለመተጋገዝ፣ ችግርን በውይይት ስለመፍታት፣ በልዩነት ስላለ አንድነት፣ ዘርን፣ ጎሳን፣ ኃይማኖትን ከፍና ዝቅ አድርጎ ስላለማየት እና መሠል ጉዳዮች የሚሰብኩ በርካታ አስተምህሮዎችና የጸደቁ ሕግጋት ባለጸጋ ናት።

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ካሉ ሕግጋት መካከል እንኳ ለአብነት ብንጠቅስ፣ በአንቀጽ 25 የእኩልነትና በልዩነት ያለመታየት መብት የማይጣሱ ተብለው የተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶች መካካል አንዱ ነው።

የሰው ልጅ በሕይወት የመኖር መብት የተደነገገው በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሆነ ይነገራል። ለዚህም የዓለም አቀፍ የዜጎችና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 4(2) ከተካተቱት ሊጣሱ የማይችሉ መብቶች መካከል በአንቀጽ 6 የተቀመጠው የመኖር መብት ተጠቃሽ ነው።
ነገር ግን፣ ሕግጋቱ ተጻፉ እንጂ ተግባር ላይ የመዋላቸው ጉዳይ ቅዠት ሆኖ የቀረ ይመስላል። ባለንበት ወቅት የተጻፉ ሕግጋት የማይከበሩ ሁነው ይታያል። የአውራምባ ማኅበረሰቦች ግን የተጻፉትን ሕግጋትን ከመተግበር አልፈው፣ የራሳቸው ሕግና ደንብ አጽድቀው ሠላምን በመስበክ በፍቅር የሚኖሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ለሌሎች ዓለም አገራት አርዓያ የሚሆኑ ናቸው።

ቀሪዎቹ የማኅበረሰብ ክፍሎች ግን ይህ ዓይነቱ ተግባር ከሕይወታቸው በመለየቱ ምስቅልቅል ባለች ጎዳና ውስጥ ለማለፍ እየተገደዱ ይመስላሉ።

በመሆኑም፣ አገራችን ምንም እንኳ በውሉ የተደነገጉ ሕግጋት ድሃ ባትሆንም፣ የደነገገችውን ሕግ በተግባር የማዋል ባህል ግን እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ፣ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በተለይም ከ2013 ጀምሮ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የሕግ ጥሰቶች ማሳያዎች ናቸው።

ታዲያ ችግር ሲፈጠር እያንዳንዱ ግለሰብ ለምን እንዲህ ሆነ? ብሎ ከመጠየቅና ሌሎችን ከመኮነን በዘለለ ‹‹እኔስ ሕጉን አክብራለሁ?›› ብሎ ራስን የመጠየቅ ልምዱ እየቀነሰ መምጣቱ፣ አሁኗ ላይ ኹሉ ነገር ለተመሰቃቀለባት ኢትዮጵያ ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል።

ለጦርነት፣ ለጠብ፣ ላለመግባባት፣ ብሎም እርስበርስ ለመናቆር የሚያበቃን ከሰው ይልቅ ገንዘብን ማስቀደም፣ ከሌሎች ጥቅም ይልቅ የራስን ጥቅም የማስበለጥ ስግብግብነት መሆኑንም ብዙዎች ይስማሙበታል። ከዚህም በተጨማሪ የተደነገጉ ሕጎች ተግባር ላይ አለማዋል ሌላኛው ዋነኛ ችግር መሆኑ በአጽንዖት ይነገራል።

ሕግን መጻፍና በተግባር መኖር ለየቅል ናቸው የሚሉት የአውራምባ ማኅበረሰብ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እናነይ ክብረት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ አለመጣላትንና ክስን እንደ ቆሻሻ መጠየፍ ከባድ ቢሆንም ይቻላል ይላሉ።

የአውራአምባ ማኅበረሰብ ለድፍን 50 ዓመት ወደ ፍርድ ቤት ያቀና ክስ የላቸውም የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ፣ ማኅበረሰቡ ይህን ለማድረግ የቻለው ከሰው ይልቅ ገንዘብን ወይም ሥልጣንን ስለማያስቀድም ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ ሰዎች በጎ እንዲሠሩ፣ ሠላም እንዲሰፍን በርካታ ነገሮች ይወራሉ፤ ነገር ግን ቃሉን በተግባር መኖር እንጅ ስለሠላም ሕጎችን ማወቁ ብቻ ዕርባና የለውም ይላሉ እናነይ።

አውራምባ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ቋንቋ፣ አመለካከት፣ ዕምነት ያላቸው ዥንጉርጉር ዜጎች የሚኖሩባት ቀበሌ ናት። ቢሆንም ግን፣ ‹‹ልዩነት ውበት ነው›› እንዲሉ የሐሳብ መቃረን ቢኖርም በውይይት ይፈታል የሚል ዕምነታቸው ሠላምን አስፍኖ ለመኖር እንዲችሉ አድርጓቸዋል።

የአውራምባ ማኅበረሰቦች ሥራን የሴት የወንድ ብለው እንደማይከፋፍሉ ሲነገር መስማት እየተለመደ ከመምጣቱም ባሻገር፣ የአካባቢው የመልካም ሥም መገለጫ ሆኗል። ይህን በተመለከተም በመስኩ የተሠማሩ ምሁራን ያጠኗቸው ሥራዎች ምስክር ናቸው።

ዛሬ ዛሬ ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩ መጥተዋል። ሰው ለሰው ያለው ፍቅር እየቀዘቀዘ ጥላቻ እየተስፋፋ የሚስተዋልበት ወቅት ላይ ስለመሆናችን አብዛኛው ሰው ይስማማበታል። ማኅበረሰብን ከጭፍን መጠላት አልፈን በጅምላ ወደ መገዳዳል ደረጃ ከደረሰ ሰንበትበት ብሏል።

የዘርፉ ባለሙያዎች አሁን ያለውንና የድሮውን ጦርነት ሲያነጻጻሩ፣ ‹‹ድሮ የሚካሄደው ጦርነት ንጹኃን ሰዎች እንዳይጎዱ የመፋለሚያ ቦታ ተመርጦ፣ የተማረከ እጁን ከሠጠ በኋላ ሽንፈቱን ተቀብሎ በአሸናፊው የሚመራበት፣ ውጤቱን መሸነፍና መሸናነፍ ያደረገ ነበር›› ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማሉ።

አሁን ላይ ነገሮች በተቃራኒው ሆነዋል፤ ጦርነቱ ንጹኃን ላይ ያነጣጣረ፣ ማንነትን ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ የጦርነት ቀጠና ባለበት አካባቢ የሚገኙ በርካታ ማኅበረሰቦች እየተናገሩ መሆናቸው አይዘነጋም።

ይህ ዓየነት ችግር ባለባት አገር ውስጥ ሆነው ከጥላቻና ከመገዳዳል ርቀው፣ ፍቅራቸውን እንደ ባህር ዳር ሳር እያለመለሙ የሚገኙ እንደ አውራአምባ ማኅበረሰብ ያሉ ዜጎችም አልጠፉም።

በአውራአምባ ማኅበረሰብ ለድፍን አምሳ ዓመታት ማኅበረሰቡ ተካሶ ወደ ፍርድ ቤት የቀረበበት ወቅት እንደሌለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይመሰክራሉ። በማኅበረሰቡ ውስጥ ለአምሳ ዓመታት ያህል ፍርድ ቤት የቀረበ ክስ ተመስርቶ አያውቅም የሚሉት የማኅበረሰቡ መሥራች ዙምራ ኑሩ ናቸው።

ዙምራ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ከሆነ፣ በእነዚህ አምሳ ዓመታት ውስጥ ማኅበረሰቡ በጸብ ምክንያት ተካሶ ወደ ፍርድ ቤት አቅንቶ የማያውቀው የሚያጣላና የሚያካስስ ጉዳይ ጠፍቶ ሳይሆን፣ ልዩነታቸውን በውይይት የመፍታቱን ጉዳይ ከቃላት በዘለለ ተግባር ላይ ስለሚያውሉት ነው።

በብዙኀኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚስተዋለው ጥፋት ያጠፋ ወይም አንድን ግለሰብ የበደለ ሰው ‹‹አዎ በድያለሁ ከማለት ይልቅ›› ራሱን/ራሷን ነጻ ለማድረግ ሲጣጣር ነው። አንዳንዶች በሦስተኛ ወገን ሲነገራቸው እንኳን ጥፋተኝነታቸውን አምነው ለመቀበል የልቦናቸውን በር ቀድመው ሲዘጉ መመልከት በሕብረተሰቡ በኩል እንደ ባህል የተወሰደ ይመስላል።

ታዲያ የአውራአምባን ማኅበረሰብ እስካሁን ድረስ እንዳይካሰሱ ያደረጋቸው ምስጢር ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ዙምራ ኑሩ ሲመልሱ፣ በሰዎች መካካል አለመግባባት ሲፈጠር የተከሠተውን የማያግባባ ችግር አጉልቶ ከማየት ይልቅ፣ ቁጭ ብሎ በመወያየት መፍትሔ ስለሚገኝ ነው ይላሉ። ለአውራምባ ማህበረሰብ ተፈቃቅሮ መኖር ዋነኛ ምስጢሩ ይህነው ሲሉ ነው ዙምራ የሚናገሩት።

አክለውም፣ “መጣላት እንደሚቻለው ኹሉ አለመጣላትም ይቻላል። ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አንድነት፣ መተጋገዝ ያለመጣላት ፍሬዎች ናቸው። መገዳደል፣ መነቋቆር፣ መካሰስ የመጣላት ውጤቶች ናቸው። ታዲያ ካለመጣላት መልካም ነገር ካገኘን፣ ከመጣላት የምናገኘው ደግሞ ክፉ ከሆነ፣ ጥላቻ ለምን መልካም ነገሮችን ይቀማናል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

‹‹ከምንጣላ ይልቅ ባንጣላስ፣ መጣላቱንም አለመጣላቱንም የማድረጉ አቅም አለን፤ ባንጣላ ምን እንሆናለን›› የሚሉት ዙምራ፣ ከተጣላን ደግሞ ጥላቻ ያሳደረብንን ጉዳይ መጥላት እንጂ ወገናችንን ጠልተን መግደል ይቅርና መካሰስ የቂሎችና የሠነፎች የዕብደት መገለጫ ነውና ሊቆም ይገባል ሲሉ ያወግዛሉ።

እንደ ዙምራ ገለጻ ከሆነ፣ መጣላት ያለብን ከወገናችን ጋር እንድንናቆርና እንድንካሰስ ምክንያት የሚሆኑብንን ነገሮች ነው እንጅ ሰዎችን አይደለም። ይህም በሰዎች መካካል ያለው መተሳብሰብ፣ መፈቃቀር፣ ተግባብቶ መኖርን ያጎለብታል ሲሉ ነው የገለጹት።

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግና ፌዴራሊዝም መምህር የነበሩት ሲሳይ መንግስቴ በሰኔ ወር 2006 ያጠኑት ጥናት፣ ላለፉት 42 ዓመት ሊባል በሚችል ደረጃ፣ የአውራአምባ ማኅበረሰብ ‹‹አባል የሆነ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ተጣላሁ፤ ድንበር ተገፋብኝ፤ ንብረት ተሠረቀብኝ ወይም ተዘረፈብኝ፤ በአጠቃላይም የአስተዳደር በደል ደረሰብኝ ወይም ፍትሕ ተጓደለብኝ ብሎ ለፖሊስ ሪፖርት አድርጎ ለፍርድ ቤት ክስ የሚያቀርብበትና በሌላ ሦስተኛ ወገን ፍትሕ ለማግኘት ሲል ወርቃማ የሆነውን የሥራ ጊዜውን የሚያባክንበት አንዳች ምክንያት እንዳይኖር ሲያደርግ ቆይቷል›› ሲሉ አስቀምጠዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here