የቁም እንስሳት የውጭ ንግድን የሚቆጣጠር እና ዝቅተኛ ዋጋ የሚወስን መመሪያ ተዘጋጀ

0
1740

ለውጪ ገበያ በሚቀርቡ የቁም እንስሳት አገራዊ ጥቅምን ለማስከበር እና በመስኩ እየታየ የሚገኘውን ከዋጋ በታች አሳንሶ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳጣትና የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋትን መግታት ያስችላል ተበሎ የታመነበት መመሪያ በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መዘጋጀቱ ታውቋል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ መመሪያ የመሸጫ ዋጋን የተከተለ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የግብይቱን ጤናማነት መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትን ታሳቢ ያደርገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ላኪዎች የእንስሳት የግብይት ዋጋ ወቅታዊና ተዓማኒ መረጃዎች እንዲኖራቸው ማድረግ በማስፈለጉ መመሪያው እንደተዘጋጀ ተጠቅሷል።

መመሪያው ከጥር 1/2014 ጀምሮ ተፈጻሚ የሆነ ሲሆን፣ ይህንን የቁም እንስሳት አነስተኛ የዋጋ ተመን መመሪያ ለማውጣት ሰባት ከሚሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ማለትም ብሔራዊ ባንክ፣ ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች እና ነጋዴዎች ማኅበራት እና የግብርና ሚኒስቴር በቦርድ አባልነት የተሳተፉበት ነው ተብሏል።

ቦርዱ በየወሩ እየተገናኘ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ለውሳኔ ያቀርባልል። ተወስኖ ሲጸድቅም ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚያደርግ በመመሪያው ተደንግጓል። መመሪያው ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳትን ጤና በመመርመር የጤና መስፈርት ለሚያሟሉት የቁም እንስሳት የጤና ምስክር ወረቀት ለላኪው እንዲሰጥ እና በተጨማሪም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳቱ የተሟላ መረጃና ሰነዶች ያላቸው መሆኑን እንዲያረጋግጥ ያዝዛል።

በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተዘጋጀው መመሪያ መሠረት፤ ከ320 ኪሎግራም እና ከዛ በታች ለሆነ የዳልጋ ከብት ወይፈን ዝቅተኛ የመሽጫ ዋጋ 650 ዶላር ሆኖ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከ320 ኪሎግራም በላይ ለሚመዝን 750 ዶላር ዝቀተኛ የመሸጫ ዋጋ እንዲሆን አስቀምጧል።

በተመሳሳይ 500 ኪሎግራም እና ከዛ በላይ ለሚመዝን ግመል 550 እና 750 ዶላር ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ሲያስቀምጥ፣ የበግ እና ፍየል ከ65 እስከ 85 የአሜሪካን ዶላር ለውጪ ገበያ መሸጫ ዋጋ አድርጎ አስቀምጧልል። ይህ ዋጋም እስከ መጋቢት 30/2014 ደረስ ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል።

የእንስሳት ሀብት ልማት እና ጥበቃ ባለሙያ ሳሙኤል አሰፋ (ዶ/ር) መመሪያው የቁም እንስሳት ንግድ ሰታንዳርድ የሚሰጥ መሆኑ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን ሊጨምር ይችላል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሆኖም በዚህ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎችም ሆነ ነጋዴዎች በዘመናዊ እና በተደራጀ መልክ የከብት ማርቢይ እርሻ ሥራን ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩበት የተሻለ ምርት እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያስቻላል ብለዋልል። ከተወሰኑ የወጭ ንግድ ላይ ከተሰማሩ ተቋምት በስተቀር ዘመናዊ የከብት ማርቢያ ጋጣ ያላችው አለመኖራቸው አገሪቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አላስቻላትም ብለዋል።

‹‹መመሪያው የኮንትሮባንድ ንግዱን መቆጣጠር የሚቻልበትን አቅጣጫ አላስቀመጠም።›› የሚሉት ባለሙያው፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት የስጋ ምርትን ወደተለያዩ አገራት በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መላክ ላይ የተሰማሩ ተቋማት በእጥረት ምክንያት በሚሊዮን ዶላሮች ወጪ ያቆሟቸውን ቄራዎች ለመዝጋት መገደዳችውን ሳሙኤል (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በ2021 ሩብ ዓመት ብቻ ከኢትዮጵያ 35 ሺሕ 280 ከብት ወደ ጎረቤት አገር ሶማሊያ በሕገ ወጥ መንገድ መውጣቱን ጠቁመው፣ ይህም ከስድስት በመቶ በላይ ጭማሪ እያሳየ እንደሚቀጥል ሳሙኤል አስረድተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here