የካቲት 12 የፋሽስት ጣሊያን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር

0
1142

ፋሽስት ጣሊያን የአድዋ ሽንፈቷን ለመበቀል ከአርባ ዓመት ዝግጅት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን በመውረር ሕዝቡን ቁም ስቅል በምታሳይበት ወቅት የካቲት 12/ 1929 አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በጦር አዛዡ ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ ቦንብ ወርውረው ጉዳት ማድረሳቸውን ተከትሎ የጣሊያን ጦር ከ30 ሺሕ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በግፍ መጨፍጨፉን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። ሙሉጌታ ገዛኸኝ የሰማዕታቱን 82ኛ መታሰቢያ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ከታሪክ አጣቅሶ የሚከተለውን ጽሑፍ አዘጋጅቷል።

ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ፊት ታሪካዊ ክብር የተጎናፀፈችበት ዓይነተኛው ምክንያት በሕዝቦቿ የራስ መተማመን ሥነ ልቦና የውጭ ወረራን መመከቷ መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ለመላው አፍሪካውያን በአድዋ ድል የናኘው የአንድነት መንፈስ አንድምታው ለጥቁሮች ወደር ያልተገኘለት ተምሳሌት ሆኖ ዘልቋል።
የቋንቋዎችና ባሕል ስብጥር ባለቤት ታላቋ ኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አፄ ምኒልክ አስቀድመው ለአውሮጳ ኀያላን መንግሥታት በላኩት ጦማር ነጻነት ወዳድ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከቅኝ ግዛት መቅሰፍት ለመታደግ ያላሰለሰ ታሪካዊ ሚና ለመወጣት እንደሚገደዱ በአጽንዖት አስገንዝበዋል።

እንደ ጎርጎርሳዊው አቆጣጠር (እ.ጎ.አ) በ1896 ኢጣሊያ በአድዋ ጦርነት ድባቅ ከተመታች በኋላ የአዲስ አበባ ውል ስምምነት በሚል ቀደም ሲል ተፈርሞ የነበረውን የውጫሌ ውል በማያሻማ ሁኔታ እንዲሰረዝ ብሎም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ‘ኦፊሴላዊ’ እውቅናን ለመስጠት ተገደደች።

ከአራት ዐሥርት ዓመታት በኋላ በእ.ጎ.አ 1935 የፋሽስት መሪ የነበረው ቤኒቶ ሞሶሌኒ በድጋሜ ኢትዮጵያን ለመውረር በቂ ዝግጅት ማድረጉን በይፋ አወጀ። ይህም ኢጣሊያ የነበራትን ግልጽ የቅኝ ግዛት ህልም እውን ለማድረግ እንዲሁም በጥቁሮች የደረሰባቸውን ታሪካዊ የውርደት ማቅ ለመፋቅ ያለመ ነበር። ሆኖም በወቅቱ የመንግሥታቱ ማኅበር (‘ሊግ ኦፍ ኔሽን’) አፍሪካዊት ብቸኛ አባልና የጥቁሮች ተሟጋች የነበረችው አገር በኀያላኖቹ አድራጊ ፈጣሪ እንግሊዝ እና ፈረንሣይ ከፍተኛ ጫናና አድልኦ የተነሳ ኢትዮጵያ ለወዳጃቸው ኢጣሊያ ስግብግብ ፍላጎት ተገዥ እንድትሆን ያጠመዱት ስውር የዘረኝነት ደባ መቼም የሚዘነጋ አይደለም።

እውቁ የታሪክ ምሁር ባሕሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ባሳተሙት ‘የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966’ በሚለው መጽሐፋቸው ሁኔታውን ሲያብራሩ “ኢትዮጵያ እንደ መስዋዕት በግ ተቆጥራ ኀያላኖቹ በቡራኬያቸው ለኢጣሊያ አበረከቷት…” ይላሉ። ኀያላኖቹ ጥቅማቸዉን ለማስጠበቅ የሔዱበት ግልጽ አካሔድ መሆኑ ያስገርማል።

ኢጣሊያ በእጆቿ የሚገኙትን ቅኝ ግዛቶች (ኤርትራ እና ኢጣሊያ-ሶማሌላንድ) እንደ ስትራቴጂ በመጠቀም በቂ ወታደራዊ ዝግጅት ለማድረግና ኢትዮጵያን ለመውረር ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላት በርካታ ፀሓፍትም ይስማሙበታል። አውሮጳውያን የነጮች በላይነት ትምህክት አቅላቸው ተሳክሮ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ብዙ ቢፍጨረጨሩም የነጻነት ወዳድ ኩሩ ሕዝብ ምላሽ ግን አገሩን በጀግንነት ወኔ ለመታደግ በአንድ ልብ መትመሙን ራሳቸው ፈረንጆቹ ታሪክ ዘጋቢዎች ሳይቀር መስክረዋል።

እ.ጎ.አ ከ1935 እስከ 1941 ድረስ በዘለቀው የአምስቱ ዓመታት የፋሽስት ወረራ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለአገራቸው ነጻነት ክቡር ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ምንም እንኳ የአንዳንድ ቀንደኛ ባንዳዎች አካሄድ የአርበኝነት ትግሉን ይበልጥ ያወሳሰበው ቢሆንም ከጠላት ጋር አብረው የራሳቸውን ወገን ያጠቁ እና ያስጠቁ ባንዳዎች ተጽዕኖ ነበር። እነዚህ ወገኖች በአንድም ይሁን በሌላም መንገድ የኢጣሊያ ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሠለባ የነበሩ ናቸው ብል ስህተት አይሆንብኝም።

በተካሔደው ጦርነት ከኢጣሊያ በኩል 300 ሺሕ ወታደሮች፣ 126 የጦር ታንኮች ፣ 325 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 94 መድፎች፣ 6 ሺሕ 286 የጦር ተሽከርካሪዎች የመርዝ ጋዝ ወይም በሳይንሳዊ መጠሪያው ‘ኤፍሪት ጋዝ’ በመጫን ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ ሞሶሌኒ የጦር አዝማቾቹን ባሕር አሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ ልኳል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የመረብን ወንዝ አቋርጦ የመጣው የኢጣልያ ሠራዊት ማይጨው ላይ ማርሻል ኢሚሊዮ ዲቦኖ ሲመራው እንዲሁም ከኢጣሊያ ሶማሌላንድ የደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ዶሎ ኦዶ፣ ጂባሴራ፣ ገናሌ፣ ነገሌ በኩል የዘመተውን ደግሞ ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኖ እንዲያዘምት ተደርጎ በአገራችን ላይ ከባድ ጉዳት፣
ከባድ የግፍ ጭፍጨፋ ደርሷል። ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል እንደልብ የጦር መሣሪያ ግዥ እና ድጋፍ ከውጭ እንዳይገኝ የ‘ሊግ ኦፍ ኔሽን’ ማዕቀብ አላፈናፍን አለ።

 

በተለይም የካቲት 12 ቀን በማርሻል ግራዚያኖ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተጨፈጨፉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥራቸው የትየለሌ ሲሆን ፋሽስቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተስፋ የመቁረጥ እርምጃ እንደወሰዱ ያሳያል። ያች ደም እንደ ጎርፍ የፈሰሰባት የጽልመት ዕለት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ መቼውንም የማይሽር ጠባሳ ትቶ አልፏል።

 

በዚያ የመከራ ወቅት ብቻዋን እየተፍጨረጨረች በተለመደው ፅኑ የአገር ፍቅር ወኔ ተስፋ ልጆቿን በአርበኝነት አሰልፋለች። ይሁን እንጅ በዓለም ዐቀፉ መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የተነፈጉት ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ በስደት ውጭ አገር ሆነው ሁኔታውን ሲከታተሉ የኋላ ኋላ ግልብጥብጡ ስለወጣ ከእንግሊዞች ያላሰለሰ ወታደራዊ እገዛ በማግኘታቸው እና በአርበኞቻችን ብርታት የአገራቸውን ነጻነት ለማስመለስ ችለዋል። ልብ እንበል! ኢጣሊያ በዓለም ሕግ ክልከላ የተጣለበትን የመርዝ ጋዝ ጭስ ተጠቅማ ምስኪኗ አገራችን ራሷን በቅጡ ለመከላከል በቂ ዝግጅት ሳታደርግ ይህንን የመሰለ ሠቆቃ አድርሳለች። በመንግሥታቱ ማኅበር በመተማመን የተጠለለች አባል አገር ለዚህ ግፍ እጣ ፋንታ መዳረግ በታሪክ ዘንድ ትዝብት የሚጭር ነው።

በተለይም የካቲት 12 ቀን በማርሻል ግራዚያኖ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተጨፈጨፉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥራቸው የትየለሌ ሲሆን ፋሽስቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተስፋ የመቁረጥ እርምጃ እንደወሰዱ ያሳያል። ያች ደም እንደ ጎርፍ የፈሰሰባት የጽልመት ዕለት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ መቼውንም የማይሽር ጠባሳ ትቶ አልፏል።

በመከራው የወረራ ዘመን ለአገራቸው የአርበኝነት ተጋድሎ ድል የተከፈለውን መስዋዕትነት የአሁኑ ትውልድ በቅጡ ተገንዝቦ የባንዳ ሴራ ምን ያህል አገርና ትውልድን ለማፈራረስ የኅልውና ፈተና ሆኖ ያስከተለውን ጥፋት ነቅቶ መከላከል ግድ ይለዋል። የኢጣሊያ ቅሪት እስከዛሬም ድረስ በብሔር፣ በሃይማኖት ቁርሾ መከፋፈልና የጥላቻ መንፈስ (‘ፓራኖያ’) እንጂ አንዳች በጎ ነገር የለውም። ስለሆነም የኢጣልያ ፋሽስቶች የሴራ እቅድ የአማራ ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሌላው ጠላት እንደሆነ ተደርጎ በመስበክ እስከዛሬም ድረስ እየደረሠ ያለውን መከራና ውርደት ቀላል አይደለም። የውጭ ወራሪ ጠላትን በመከላከል ኃላፊነቱን እየተወጣ አገሩን ለትውልድ ጠብቆ ያቆየው ሕዝብ የኢጣሊያኖች ቅኝ ግዛት ቀንበር ተግባራዊ እንዳይሆን ያጨናገፈው አማራውና የኦርቶዶክሱ እምነት ተከታይ በ‘ኢትዮጵያኒዝም’ ንቅናቄ ስም ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው በተጠያቂነት መፈረጃቸው በርካታ የታሪክ ማሰረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። የታሪክ ተመራማሪ አልቤርቶ ስባቺ (ፕሮፌሰር) “ኢትዮጵያ በፋሽስቱ ሞሶሊኒ ወረራ ዘመን” የሚለውን መፅሐፍ ስንመለከት በግልጽ ያስረዳል። የፋሽስቶች እኩይ ጥላቻ ሠንኮፍ ከሥር መሠረቱ ካልተመነገለ በስተቀር ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ አደገኛ ነቀርሳነቱ የከፋ የከረፋ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here