‘እርጥብ’

0
762

እርጥብ በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እየተለመደ የመጣ የምግብ ዓይነት ሲሆን በብዛት የሚገኘው በየሰፈሩ በሚገኙ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የምግብ አገልግሎት በሚሰጡት ሱቆች ውስጥ ነው፤ በተለምዶ ‘አርከበ ሱቅ’ በመባል በሚታወቁት ትንንሽ ምግብ ቤቶች ናቸው። ሌላው የእርጥብ መገኛ አዳዲስ ሕንፃዎች በሚገነቡበት አካባቢዎች ሲሆን ሠራተኞቹን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። እርጥብ በተለይ የቀን ሠራተኞችን፣ የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች እንዲሁም ተማሪዎች የሚገኙበት አካባቢ በብዛት እንደሚገኝ የአዲስ ማለዳ ቅኝት ያመለክታል።

በተለይ አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችበት ቀበና መድኀኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኙት ምግብ ቤቶች እርጥብ በብዛት እንደሚሸጥ ታዝባለች። ቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት በመደዳ በተደረደሩት አብዛኛዎቹ አነስተኛ መመገቢያዎች ውስጥ እርጥብ ይሸጣል። የቤቶቹ ተመጋቢዎች በትንንሽ ወንበሮች ላይ ቁጭ ብለው ያዘዙትን እርጥብ ሲመገቡ ማየት በተመልካች ላይ ሆድ የማላወስ፣ የመመገብ አምሮት ማናር ወይም ከዚህ ከፍ ካለም ምራቅ በአፍ እንዲሞላ ያስገድዳል።

እርጥብን ለመሥራት በዋናነት ድንች፣ ዘይት ቃሪያና ሚጥሚጣ ለግብዓትነት ሲያገለግሉ ለማባያነት ደግሞ ዳቦ አብሮ ይቀርባል። አርጥብን ሰርቶ ለምግብነት ለማድረስ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ የሚፈጅ ሲሆን አሰራሩም ድንቹ በመጥበሻ ላይ በዘይት ሳይደርቅ በለስላሳው እንዲጠበስ ይደረጋል፤ የተጠበሰው ድንች ከሚጥሚጣና ቃሪያ ጋር እንዲዳመጥ ይደረጋል። በመጨረሻም ከዳቦ ጋር በሳህን ተደርጎ ለበላተኛው ይቀርባል። እርጥብ አዘገጃጀቱ ቀላል ዕይታውም ለዓይን ሳቢ የሆነ ምግብ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

የአንድ እርጥብ ዋጋ በአማካኝ ከ13 እስከ 16 ብር ሲሆን መጠኑም ለአንድ ሰው በቂ ነው። ከተበላም በኋላ ሆድን ያዝ አድርጎ ረጅም ሰዓት የምግብ ጥያቄ እንዳይነሳ ማድረጉ በተመጋቢዎቹ ተመራጭ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው።

እርጥብን የሚያዘጋጁት ትንንሾቹ ምግብ ቤቶች ሁሉም በሚያስብል ደረጃ የሚጠቀሙት በተለምዶ ‘ማሙሽ’ ተብሎ የሚቆላመጠው የዘንባባ ዘይትን ነው። በባለቢጫው ጀሪካኑ ዘይቱን ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ፀሐይ እንዲቀልጥ መደረጉ ለቁልምጫ ስሙ ምክንያት ሆኗል።

ይህንን ዘይት አብዝቶ መጠቀም ለከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያጋልጥ የጤና ባለሙያዎች በሰፊው ይመክረሉ። ይሁንና እርጥብን አብዝተው የሚመገቡም ሆኑ አዘጋጅተው ለሽያጭ የሚያቀርቡትም ግንዛቤው አላቸው። ነገር ግን ከአቅማቸው ጋር በተያያዘ አማራጭ ማጣት እንዳስገደዳቸው ይነገራሉ።

ዓለም አሰፋ ከትንንሾቹ ምግብ ቤቶች ባለቤት አንዷ ነች። ቁመቷ አጠር ያለ፣ መካከለኛ ቁመትና ውፍረት ያላት ነገር ግን ሆዷ በመግፍቱ እርግዝናዋን የሚያሳብቅ ሴት ነች። ዘይቱን በተመለከተ “ዘይቱን አብዝቶ አብዝቶ መጠቀም እኛንም ሆን ደንበኞቻችንን በሽታ ሊያጋልጠን እንደሚችል እናውቃለን። ነገር ግን ዘይቱ መጠቀም አቆምን ማለት ከመተዳደሪያ ሥራችን ተፈናቀልን ማለት ነው” ስትል ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች። ዓለም ምክንያቱንም ስታብራራ የሚቀልጠውን ዘይት በፈሳሹ ቀይረን ከምናዘጋጅ ሥራችንን በገዛ ፈቃዳችን እንዳቆም ይቆጠራል ምክንያም እርጥብን የሚበላልን አናገኝምና ብላለች። በአጭሩ የእሱንም ሥራ ማጣት የደንበኞቻቸውንም ፍላጎት መንጠቅ እንደሚሆን ለማመልከት።

እርጥብን መተዳደሪያቸው አድርገው ቀበና መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚኖሩት መካከል አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እንደሚሉት ከሆነ እርጥብን በአካባቢያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሰርታ ለሽያጭ ያቀረበችው በልዩ የምትባል ሴት ወይዘሮ ስትሆን ለአካባቢው ኅብረተሰብ እርጥብ ሽጦ ኑሮውን እንዲገፍ ምክንያት መሆኗንም ይናገራሉ። “በቀን በአማካኝ ከ10 እስከ 15 እርጥብ በ13 ብር እንሸጣለን” የምትለው ዓለም “ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሯችንን ግን አልለወጠውም” ብላለች። “ስለዚህም ትርፉን አስበን ሳይሆን ዛሬን አስበን ነው የምንሰራው” በማለት የኑሯቸውን ሁኔታ ልብ በሚነካ ቋንቋ ገልፃዋለች።

ሌላው ከንጽሕና ጋር በተያያዘ በአካባቢው የሚገኙት እርጥብ ሻጮች በር ላይ የእጅ መታጠቢያ ቢኖርም ምግቡ የሚሠራበት እያንዳንዱ ግብዓትም ሆነ የቤቱ የንጽሕና ጉድለት ተመጋቢውን በሙሉ እምነት እንዲበላ አይጋብዝም። ከዚህም ይባስ ብሎ ምግቡ የሚዘጋጀውም ሆነ ተመጋቢው የሚቀመጥበት ቦታ አንድ ላይ መሆኑ እንዲሁም የምግቡ ማብሰያዎቻና ማቅረቢያ ዕቃዎች ንፁህ መሆን ከሚጠበቀባቸው በታች ስለሆኑ ተጠቃሚው ለጤና ችግር የሚጋለጥበት መሆኑን ታዝበናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here