የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የ2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደላት ግለሰብ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተገለፀ

0
918

አርብ ጥር 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት 2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደላት ግለሰብ ፍርድ ቤት መቅረቡን የከተማዋ ፓሊስና ዩኒቨርስቲው ለቢቢሲ አማርኛ አስታወቁ።

በዩኒቨርስቲው ተማሪ የሆነው ተጠርጣሪና ሁለት ሌሎች ተማሪዎች ከፅጌረዳ ግድያ ጋር በተያያዘ ማክሰኞ ዕለት በአርባ ምንጭ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን የ15 ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር በድሩ ኢሪጎ ገልጸዋል።

ፅጌረዳ ግርማይ በስለት በተፈጸመባት ጥቃት የተገደለችው ሰኞ ጥር 23/2014 ምሽት በግቢው ቤተ መጻሕፍት አካባቢ መሆኑን በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር አዳነ ኦኬ አስረድተዋል።

ጥቃቱ በጩቤ የተፈጸመ ሲሆን፣ ጡቷና ጎኗ አካባቢ ላይ በተደጋጋሚ ተወግታ ሕይወቷን ለማትረፍ ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ብትወሰድም ልትተርፍ እንዳልቻለች ተናግረዋል።

ግድያው የተፈጸመው ጥር 23/2014 ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው በዩኒቨርስቲው የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት 2ኛ ዓመት ተማሪና ከፅጌረዳም ጋር በአንድ ዲፓርትመንት የሚማሩ እንደነበሩና፣ የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች እየተሰሙ እንደሆነም በድሩ ተናግረዋል።

ፅጌረዳ ከዚህ ቀደም ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነት እንደነበራትና ይህንንም ግንኙነት በማቋረጧ የተነሳ ነው የሚሉ፣ እንዲሁም ተጠርጣሪው ፅጌረዳን ለፍቅር ግንኙነት ፈልጓት ፈቃደኛ ባለመሆኗና ይህንንም እምቢታዋን በበጎ መልክ ባለመውሰድ በስለት ወግቷታል የሚል መረጃን ሰብስብዋል።

አብራት ዶርም የምትኖር ጓደኛዋንም ዋቢ አድርገው በድሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ለፍቅር ግንኙነት እንደሚፈልጋት እና ፅጌረዳም እምቢተኝነቷን እንደገለጸች፣ ከዚያ በኋላም ምንም አይነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከአካባቢው ፖሊስ የተገኘው መረጃ የጥቃቱ ሰለባና ተጠርጣሪው የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ያመለክታል።

ተጠርጣሪው ለፅጌረዳ በሚደውልላት ወቅት የእሱን ስልክ እንደማታነሳና ምላሽም እንደማትሰጠው በድሩ መረጃ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ።

ግድያው በተፈፀመበት ምሽት ላይ ተጠርጣሪው የእሱን ስልክ ስለማታነሳ በሁለት በምታውቃቸው ወንድ ተማሪዎች አማካይነት ከምሽት አራት አስከ አምስት ሰዓት ባለው ፅጌረዳን ያስጠራታል።

ፅጌረዳም በግቢው ወደሚገኘው የካምፓሱ አስተዳደር ህንፃ አካባቢ ወይንም ቤተ መጻሕፍት አካባቢ እንድትመጣ አደረጋት።

ከደረሰች በኋላም ሁለቱን ተማሪዎች እንዲርቁና “ያለንን አለመግባባት በግል እንፈታለን” የሚል ምክንያት ሰጥቷቸው ትንሽ ራቅ ማለታቸውን በድሩ ይናገራሉ።

ብዙም ሳይርቁ ፅጌረዳ ጩኸት እንዳሰማችና በያዘው ስለትም እንደወጋት ገልጸዋል። ተማሪዎቹ ተሯሩጠው እንደመጡና ጩኸቱንም ሰምተው የካምፓስ ፖሊስና የደኅንነት አባላት በአካባቢው ደርሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ ተጠርጣሪው እና ስልክ ደውለዋል የተባሉት ሁለት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ በድሩ አስረድተዋል።

በወቅቱም ፅጌረዳ ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በአስቸኳይ እንድትደርስ ቢደረግም ህክምና እየተደረገላት ህይወቷ አልፏል። በነገታው ጥር 24/2014 ዓ.ም አስከሬኗ ወደ ትውልድ ቦታዋ ወልቃይት አዲ ረመፅ ተሸኝቷል።

በግድያው የተጠረጠረው ተማሪ ከደብረ ብርሃን ከተማ የመጣና፣ ከዚህ በፊት የዲሲፒሊን ችግሮች እንደነበሩበት ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከዚህ ቀደም ሴት ተማሪዎች ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርስብናል ብለው ለዩኒቨርስቲው መናገራቸውንና “አስቸጋሪ” የሚባል ባህርይ እንደነበረውም በድሩ የዩኒቨርስቲውን መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ሴት ጓደኛው የነበረችው ተማሪ ከእሱ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርስቲውን እንደለቀቀችና ሌሎች ሁለት ሴት ተማሪዎችም እንዲሁ ለዩኒቨርስቲው አመልክተው ጉዳዩ በዲሲፒሊን እንደታየና ማስጠንቀቂያዎችም ተሰጥተውት ነበር ብለዋል።

“ኃላፊዎቹ ተጠርጣሪውን በተመለከተ ለተግባቦት ምቹ አልነበረም እንዲሁም ማስጠንቀቂያዎችና ምክርም ተሰጥቶት ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

አመልክተው የነበሩት ሁለቱ ተማሪዎች ተመርቀው እንደወጡም በድሩ ይናገራሉ። ተጠርጣሪው ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ምክርና ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሲሆን ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርስ እንደነበር ገልጸዋል።

የፅጌረዳ ግድያ ከብሔሯ/ከማንነቷ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ መነሳቱን ጠቅሶ ቢቢሲ ለዳይሬክተሩ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፤ “ጉዳዩ የፖለቲካ ባይሆንም እንኳን ፖለቲካዊ ትርጉም እንዲሰጠው የሚሞክሩ ይኖራሉ ለዚህ ትርጓሜ መስረት የለውም“ ሲሉ በድሩ አስረድተዋል።

ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ወይም ጥላቻ አድርሶ ቢሆን ኖሮ መነሻ ሊሆን ይችል ነበር የሚሉት በድሩ፣ ነገር ግን የተጠርጣሪው ባህርይ ከዚያ ሩቅ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ይህ ሁኔታ በፅጌረዳ ቦታ ማንኛዋም ሴት ብትሆን ሊደርስ የሚደርስ ጥቃት ነው በማለት “ከብሔር ጋር የተያያዘ ነው የሚያስብል ምንም አይነት ጠንካራ ምክንያት የለም። ያለውን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብንገነዘበውና ይህንን ጉዳይ የፖለቲካዊ ይዘት ለመስጠት የሚሞከረው ነገር ተገቢ አይደለም” ይላሉ።

ዩኒቨርስቲው የተማሪዋን ሞት አስመልክቶ ባወጣው የሃዘን መግለጫ ተማሪ ፅጌረዳ በወልቃይት ጌታቸው አዘናው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰናዶ ትምህርቷን ከተከታተለች በኋላ፣ በመስከረም 2012 ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ እንደተመደበችና በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነበረች።

ተማሪ ጽጌረዳ ከአባቷ ግርማይ ገብረመድኅን እና ከእናቷ ያበሻ ያዘዘው በወልቃይት ወረዳ በአድ ረመጽ ከተማ በ1993 መወለዷን የሕይወት ታሪኳ አመልክቷል።

የ20 ዓመቷ ወጣት ፅጌሬዳ ግርማይ ሥርዓተ ቀብር ትናንት ጥር 26 ቀን 2014 በዳንሻ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here