በፈተናዎች የተወጠረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

0
1539

ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮች እያለፈች በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ኢኮኖሚዋ በበርካታ ችግሮች እየተፈተነ ይገኛል፡፡ የኢኮኖሚው መፈተን የገጠሟትን ችግሮች ለማለፍ ለምታደርገው ጥረት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፖለቲካ ጥገኝነት የተለየ አለመሆኑን ተከትሎ፣ በየጊዜው በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ሠለባ እንደሚሆን እና ጉዳቶችን እንደሚያስተናግድ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ብቻ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ኢኮኖሚው ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑ ይገለጻል፡፡ በተለይ ባለፉት ኹለት ዓመታት ክፍለ ኢኮኖሚው ካስተናገዳቸው ከፍተኛ ፈተናዎች መካከል የኮቪድ-19 ተጽዕኖ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እና አሁንም የቀጠለው ጦርነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእነዚህ አገራዊ ችግሮች እየተፈተነና ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደ ስላለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ኢኮኖሚው የገጠመውን ፈተና በማንሳት የዘርፉ ምሁራንን በማነጋገርና የመፍተሔ ሐሳብ የሚሉትን በመጠየቅ የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላለፉት ኹለት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በነዚህ ኹለት ዓመታት ክፍለ ኢኮኖሚው ካስተናገዳቸው ከፍተኛ ፈተናዎች መካከል የኮቪድ-19 ተጽዕኖ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እና አሁንም የቀጠለው ጦርነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከመጋቢት ወር 2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከሠተው ኮቪድ-19 በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ተጽዕኖን ተከትሎ የተባባሰው የዋጋ ግሽበት እና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ሳይፈታ፣ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሉት መሆኑን በተደጋጋሚ በዘርፉ ባለሙዎች ሲገለጽ ይደመጣል። በተደራራቢ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮቹን ተቋቁሞ እንዲያልፍ ከወትሮው የተለየ ሥልት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ቢጠቁሙም፣ የኢኮኖሚው ፈተና አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል።

በተለይ የሰሜኑ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ለመሆኑን፣ በጦርነቱ የወደመው በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት፣ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ሀብት ንብረቱን አጥቶ ተረጅ መሆኑ እና በጦርነቱ ምክንያት የተባባሰውን የዋጋ ግሽበት እንደማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።

በጦርነቱ ከወደመው ሀብት በተጨማሪ ለጦርነቱ የሚወጣው የመንግሥት በጀት እና ከሕዝብ የሚሰበሰበው ሀብት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ የሚባል ዘርፈ ብዙ ጫናዎች እያሳደረ ይገኛል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የመንግሥት በጀት ወደ ጦርነት ወጪ መዞሩ፣ በመንግሥት የሚለሙ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ እና የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዳይቀጥሉ ማድረጉ በኢኮኖሚው ላይ የረዥም ጊዜ ጠባሳ እንደሚሆን እየተገለጸ ነው። የሰሜኑ ጦርነት ቀጥተኛ ሠለባ ከሆኑት ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች መካከል፣ አማራ ክልል በጀቱን ለጦርነቱ ማዞሩን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በክልሉ መንግሥት የሚለሙ የተመረጡ ፕሮጀክቶችን እስከማጠፍ የደረሰ ዕርምጃም ወስዷል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፖለቲካ ጥገኝንት የተለየ አለመሆኑን ተከትሎ፣ በየጊዜው በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ሠለባ እንደሚሆን እና ጉዳቶችን እንደሚያስተናግድ ብዙዎች ይስማማሉ። ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ብቻ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት አንጋፋው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት በበርካታ ፈተናዎች የተወጠረበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ በአሁኑ ስዓት የኢኮኖሚው ዋነኛ ፈተና ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ከጦርነቱ በፊት የነበሩ የኮቪድ-19 ተጽዕኖ፣ የዋጋ ግሽበትና ውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ከጦርነቱ መከሠት በኋላ ተባብሰው መቀጠላቸው፣ ጦርነቱ ኢኮኖሚውን አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ይላሉ።

የጦርነት ኢኮኖሚ
በኢትዮጵያ፣ የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ እስካሁን በዘለቀበት የአንድ ዓመት ከሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ፣ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መጥቷል። ባልዳበረ ኢኮኖሚ ላይ የተከሠተው ጦርነት፣ ቀጥተኛ ሠላባ በሆኑት ክልሎች ላይ ከፍተኛ የሀብት ውድመት አስከትሏል። ጦርነቱ እስካሁን በተካሄደባቸው በአፋር እና በአማራ ክልል አካባቢዎች የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ መውደሙን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ጦርነቱ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ከመስፋፈቱ በፊት ትግራይ ክልል ውስጥ በሚካሔደበት ወቅት ከመንግሥት ሀብት እስከ ግለሰብ ፋብሪካዎች ድረስ የክስተቱ ሠላባ መሆናቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።

ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ መካከል የመንግሥት ሀብት አጠቃቀም ማዛባት እና የሕዝብ ሀብት አጠቃቀም ላይ ችግር መፍጠር መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደምስ(ዶ/ር) ይገልጻሉ። ባለሙያው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት የመንግሥትን የልማት በጀት ወደ ጦርነት እስከማዞር የሚደርስ፣ እንዲሁም ለጦርነቱ ድጋፍ የሚሰበሰበው የሕዝብ ሀብት በኢኮኖሚው የሀብት አጠቃቀም ላይ የሚያሳደርው ጫና ቀላል የሚባል አለመሆኑን ይገልጻሉ።

በጦርነቱ ካጋጠመው የሀብት አጠቃቀም መዛባት በተጨማሪ፣ የችግሩ ሠለባ በሆኑ አካባቢዎች የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ውድመት እንዲሁም፣ የዜጎች ከመኖሪያ ቦታ መፈናቀል በኢኮኖሚው ላይ የረዥም ጊዜ ጠባሳ የሚጥል ነው ብለዋል። በጦርነቱ የተከሰተውን የሀብት ውድመት እና የመሠረተ ልማት መስተጓጎል ተከትሎ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ችግሮች እንደሚከሠቱ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ አለመጠናቀቁን ለአጭር ጊዜ የሕዝብ ኑሮን ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ፣ የረዥም ጊዜ ዕድገትን እንደሚገታ እና ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ በተጨማሪ፣ የጦርነቱ ሠለባ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው እና ሀብቱን ያጣው የማኅበረሰብ ክፍል ግንባር ቀደም የችግሩ ተጋላጭ እንደሚሆን ደምስ ጠቁመዋል። በተከሰተው ጦርነት ሀብቱን ያጣው ሕዝብ ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር መጋለጡን ተከትሎ ረሀብ ሊከሰት የሚችልበት ኹኔታም ሊያጋጥም እንደሚችል ይገልጻሉ።

ጦርነት በርካታ ችግሮች ያስከትላል የሚሉት የምጣኑ ሀብት ባለሙያው፣ የጦርነት ሠለባ ከሆነው ኢኮኖሚና ከሚከተሉት ችግሮች እንዴት መውጣት እንደሚቻል አቅዶ መሥራት ተገቢ ነው ይላሉ። በጦርነት ታሪክ ያለፉ የዓለም አገራት ከጦርነት በኋላ የገጠማቸውን የኢኮኖሚ ሥብራት ለመጠገን ከወትሮው የተለየ ዕቅድ ነድፈው ከችግሩ እንደወጡ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ለዚህ ማሳያ ከኹለተኛውን የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ በጦርነቱ የፈረሱ አገራትን መልሳ ለማቋቃም የተጠቀመችበትን የማርሻል ዕቅድን ያነሳሉ።

አሜሪካ በወቅቱ በጦርነቱ የተጎዱ አገሮችን ለማቋቋም ባዘጋጀችው የማርሻል ፕላን የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ የመልሶ ማቋቋም ዕቅዶችን ወጥና ተግባራዊ ማድረጓን የሚጠቅሱት ባለሙያው፣ በዕቅዱ መሠረት የፈረሱውን መልሳ መገንባት መቻሏን ያስታውሳሉ። በማርሻል ፕላኑ መሠረት የፈረሰውን መልሶ መገንባት፣ ሰብዓዊ ቀውስን መቀነስ፣ ገበያ መፍጠር እና የደኅንነት ሥጋትን መቀነስ የመሳሰሉ ሥራዎች ከአጭር እስከ ረዥም ጊዜ ተግባራዊ በመደረጋቸው ውጤት አምጥቷል ይላሉ። ኢትዮጵያም ጦርነት ያስከተለባትን የኢኮኖሚ ሥብራት የምትቋቋምበትና የምታገግምበት የተቀናጀ ዕቅድም ያስፈልጋታል ሲሉ ይደመጣሉ።

ኢትዮጵያ ከገጠማት የጦርነት ኢኮኖሚ ችግር ልትወጣ የምትችለው ባለድርሻ አካላትን ያካተተ እና የተቀናጀ የመልሶ መቋቋሚያ ዕቅድ በማዘጋጀት ነው የሚሉት ባለሙያው፣ የመልሶ ግንባታ ተዋንያን በግልጽ መለየት አለባቸው ብለዋል። መንግሥት የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታውን ብቻውን የሚወጣው አይደለም የሚሉት ባለሙያው፣ የመልሶ ግንባታ ተሳታፊዎችን በግልጽ በዕቅዱ ውስጥ ማካተት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመሻገር ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ከአጭር እስከ ረዥም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ መሥራት ያለበት ቢሆንም፣ አሁን ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ስሜታዊ ይመስላል ሲሉ ባለሙያው ጠቁመዋል። “በዚህ ረገድ የገዘፈ እንቅስቃሴ አይታይም” የሚሉት የምጣኔ ሀበት ባለሙያው፣ በባለሙያዎች የታገዘ ኹሉን አካታች ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። ባለሀብቶች በመልሶ ማቋቋም የሚኖራቸው ሚና ጉልህ መሆን አለበት የሚሉት ደምስ፣ ድርሻቸውን በዕቅድ አካቶ የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።

የጦርነቱን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች መልሶ ማቋቋማ እና በአካባቢው ረሀብ እንዳይከሰት በፍጥነት የማገገሚያ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸውም ባለሙያው ጠቁመዋል። እንዲሁም መሠረታዊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶችን እና ተቋማትን ወደ ሥራ ማስገባት እና የጉዳቱ ሠለባ የሆነው ማኅበረሰብ ወደማገገም የሚገባበትን ሥራ መሥራት እንደሚገባም አክለዋል።

የጉዳት ሠለባ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በደረሰበት የንብረት ውድመት ራሱን ችሎ መቋቋም አይችልም የሚሉት እኚህ ምሁር፣ የሚያርስበትን በሬ ያጣን ማኅበረሰብ እንዴት ወደ ምርት ማምረት እንደሚገባ በሚገባ አስቦ በአስቸኳይ መደገፍ ይገባል ብለዋል። ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የእርሻ በሬውን ያጣ ገበሬ እንዴት ወደ ግብርና ሥራው መመለስ ይቻለዋል የሚለው ጉዳይ ትኩረት እንዳልተሰጠው እና ቀላል ነገር አድረጎ የማየት ነገር መኖሩን ባለሙያው ገልጸዋል።

“ኢኮኖሚው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ የሚዲያ ሆይ ሆይታ፣ ፖለቲካዊ (ፖለቲሳይዝ) ማድረግ፣ ነገሮችን ሁል ጊዜ እናጋግላቸዋለን፤ በተጨባጩ ዓለም ሊሠራ በሚችል መፍትሔ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ሁሉም የራሱን ይዞ በተናጠል ሲሯሯጥ ታየዋለህ” የሚሉት ባለሙያው፣ በችግሩ ልክ መዘጋጀት፣ መቀናጀት እና ኢኮኖሚውን የፖለቲካ ጥገኛ ከሚያደርጉ አሠራሮች መውጣት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ከታች ያለው ካድሬ ችግራችንም አካሄዳችንም በደንብ የገባው አልመሰለኝም፤ ለፖለቲካ ሥራው ብቻ ነው የሚሯሯጠው” ሲሉም ባለሙያው ጠቁመዋል። በመልሶ ማቋቋም ወቅት ወጣቱን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማሰብ እንደሚገባ የሚጠቁሙት ባለሙያው፣ በጦርነቱ እንዲሳተፍ የተደረገው ወጣት በየአካባቢው አደራጅቶ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲሠራ ማቀድ ያስፈልጋል ብለዋል።

በጦርነቱ የወደሙ ከተሞችን፣ ፋብሪካዎችን እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚሠሩ ሥራዎች በተናጠል ኹሉም በየፊናው ሲንቀሳቀስ የሚታይበት ኹኔታ አዋጭ አይደለም የሚሉት ደምስ፣ ሰከን ብሎ ከፖለቲካ ዕሳቤ በተለየ ኹኔታ የተቀናጀ ዕቅድ አዘጋጅቶ በቅንጅት መልሶ ማቋቋም ይገባል ብለዋል። የወደሙ ፋብሪካዎችን መልሶ ለማቋቋም አንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ብቻውን ሊሠራው አይችልም የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው ይላሉ።

የተቀናጀ እና ወጥ የሆነ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት አገራዊ ግብረ ኃይል ማቋቋም እና በተቀናጀ ኹኔታ መረጃዎችን አሰባስቦ በዕቅዱ መሠረት ወደ ትግበራ መግባት ይገባል የሚሉት ባለሙያው፣ በክልል ደረጃ ጠንካራ ኮሚቴዎችን አደራጅቶ የመልሶ ማቋቋም ሥራወን በቅንጅት መምራት ተገቢ ነው ብለዋል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ወደ አንድ ትሪሊዮን ደርሷል” የሚሉት ባለሙያው፣ በብዛት የሚታየው የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ የሚበጅተው በጀት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ በጀት የፌዴራል መንግሥት በጀት ብቻ አይደለም ይላሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ማለት የተለያዩ የመንግሥት አካላት በክልልና በፌዴራል ያሉ የተመደበላቸውን በጀት ያካትታል የሚሉት ባለሙያው፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት አንድ ትሪሊዮን ተሻግሯል ይላሉ።

“ግዙፍ ኢኮኖሚ ነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ” የሚሉት ደምስ፣ የዚህን ግዙፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በወሬ ብቻ መምራት አይቻልም ይላሉ። በመሆኑም፣ ኢኮኖሚውን በሙያተኞች በታገዘ ዕቅድ እና አሠራር መምራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ኢኮኖሚው ከገጠመው ፈተና እንዲወጣ ጥሩ መዘጋጀት፣ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት መሄድ፣ ዋና ዋና ተዋናዮችን በደንብ ማካተት፣ የፌዴራል የክልል ተቋማትን ማስተሳሰር እና የሀብት ምንጮችን በደንብ መለየት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጦርነቱ ለረዥም ጊዜ ካልቀጠለ ለጦርነት የተገነባውን መከላከያ ኃይል ጭምር ወደ መልሶ ግንባታ እና ወደ መሠረተ ልማት በማስገባት ከችግሩ ማገገም ይቻላል የሚሉት ባለሙያው፣ “ጦርነቱ ከቀጠለ አሁንም ችግር ውስጥ ነው የምንወድቀው” ብለዋል። ባለሙያው አክለውም፣ በታቀደ እና በተቀናጀ ኹኔታ ውጤታማ ሥራ ካልተሠራ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ተናግረዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ካስከተላቸው ጉዳቶች መካከል የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እና የዋጋ ግሽበት መባባሶች ይገኙበታል። ከጦርነቱ መከሰት በኋላ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው ፕሮጀክቶች እንዲስተጓጎሉ ምክንያት እየሆነ መምጣቱ እየተገለጸ ነው።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት
የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ወትሮም የነበረ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በኋላ እየተባባሰ መምጣቱ እየተገለጸ ነው። የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች 2014 ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያቀረቡ በሚገኙበት በዚህ ወቅት፣ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ለዕቅዳቸው መሳካት መሰናክል እየሆነባቸው መሆኑን እየገለጹ ነው።

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ምንጮች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ብድር፣ የዕርዳታ ድርጅቶች እና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሐዋላ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ገንዘብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው የሚሉት ደምስ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከውጭ ምንዛሬ ምንጮች የሚገኘው ገንዘብ የቀነስበት ኹኔታ መኖሩ አንድ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ። ደምስ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ለመሠረታዊ ልማት እና ለተገቢው አገልግሎት በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደልም ይላሉ። በዚህም ውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ እና በባንኮች ኮሚሽን ቁጥጥር ሥር መውደቁ፣ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ እንዳትጠቀም በማድረግ ለውጭ ምንዛሬ ዕጥረት አጋልጧታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በውጭ በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሐዋላ የሚላከው ነው የሚሉት ደምስ፣ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለመሠረታዊ የአገር ልማት ማዋል ይገባታል ይላሉ። ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ለመቅረፍ ኢትየጵያውያን ገንዘባቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት እንዲልኩ በማድረግ ገንዘቡን ለተፈለገው የልማት ሥራ በአግባቡ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንዲሁም፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የውጭ ንግዶች የምታገኘውን ምንዛሬ ለማሳደግ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የምርት መጠን ማሳደግ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ የተመጣጠነ አይደለም የሚሉት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ የምታስገባው ምርት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው በስድስት ዕጥፍ ይልቃል ይላሉ። በመሆኑም፣ የሚታየውን የወጪ እና የገቢ ምርት አለመመጣጠን ማስተካከል እና የውጭ ምንዛሬ ምንጮችን ማጤን እንደሚገባ ባለሙያው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።

የዋጋ ግሽበት
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ አሁን ላይ ደግሞ አባባሽ ኹነቶች ገጥመውታል። ከጦርነቱ መከሠት በኋላ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ከወር እስከ ወር እያሻቀበ ሲሆን፣ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እየፈተነ ይገኛል። ጦርነት የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ እንደሚያደርግ እና የማኅበረሰቡን ኑሮ እንሚፈታተን የሚገልጹት ደምስ፣ የጦርነቱ መራዘም የዋጋ ግሽበቱ እየተባባሰ እንዲሄድ ምክንያት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የ2014 የታኅሣሥ ወር አጠቀላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 35.1 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በምግብ ነክ ግብዓቶች ግሽበት ደግሞ 41.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል። እንዲሁም፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት የታኅሣሥ ወር 2014 ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር 2013 ጋር ሲነጻጸርም የ26.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡

በአንድ ወር ውስጥ ብቻ የታየው የዋጋ ግሽበት ልዩነት በኅዳር ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ33.0 የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወር ልዩነት ወደ 35.1 በመቶ ከፍ ብሏል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የኅዳር ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 38.9 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 41.6 በመቶ ከፍ ብሏል።

ለዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያች ከሚባሉት መካል የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን አንዱ ሲሆን፣ ከጦርነቱ መከሠት በኋላ በተፈጠሩ መስተጓጎሎች የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት የምርት አቅርቦት ዕጥረት ሲያጋጥም ይታያል። በሌላ በኩል ሕገ ወጥ ደላሎች በገበያ ውስጥ የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት ለዋጋ ግሽበት አባባሽ ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here