“ንጹሓን የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን ወደሥራ ገበታቸው መመለስ ችሮታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑ ይታወቅ!“:- እናት ፓርቲ

0
641

ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ንጹሓን የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን ወደሥራ ገበታቸው መመለስ ችሮታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑ ይታወቅ! ሲል እናት ፓርቲ አሳሰበ።

ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትናንት መግለጫ አውጥቷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ኢትዮጵያ አገራችን በቅርቡ ከገባችበት የሕልውና ጦርነት ጋር ተያይዞ ቍጥራቸው ቀላል የማይባል የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን በፌዴራልና በተለያዩ ክልሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል።

ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ሂደቱ ሕግንና ሕግን ብቻ የተከተለ እንዲሆን አበክሮ ሲያሳስብ ቆይቷል፤ አሁን ላይ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታሥረው የነበሩ አንዳንዶች እየተለቀቁ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡

በእርግጥ ማናችንም ከአገር ሕልውና በታች ነንና ለምን ተጠረጠሩ ሳይሆን በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የፍርድ ሂደታቸው ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ ሆኖና ተፋጥኖ ነጻ እንዲወጡ አበክረን ጠይቀናል፡፡ አሁንም ወንጀለኛውን ለማግኘት ሲባል ብዙ ንጹሓን እንዳይንገላቱ ሕግ አስከባሪውና የፍትሕ ተቋማት አበክረው እንዲሠሩበት ለመጠየቅ እንወዳለን፡፡

በሌላ በኩል እነዚህ በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ እንዲሁም በቁጥጥር ሥር ሳይውሉ ከሥራ ገበታ ታግደው በቤት እንዲቆዩ የተደረጉ ንጹሓን ወደየሚሠሩባቸው መሥሪያ ቤቶች ሲመለሱ በአግባቡ እንዳልተስተናገዱ፣ ደመወዛቸው እንደተቋረጠ እና አንዳንድ ቦታዎች ይባስ ብሎ “በእናንተ ቦታ ሌላ ሰው ተተክቶበታል” በሚል ማን አለብኝነት ለተጨማሪ እንግልት እንደተዳረጉ መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡

እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ዘመድ አዝማድና ተወላጅ ለመሰብሰብ፣ ለማሸማቀቅ፣ ወዲህም ኪስ ለማደለብ የሚሯሯጡ አካላት ተግባር ርካሽና ትሕነግ ካደረሰው በደል ያልተናነሰ ነገር እንደፈጸሙ ሊያውቁት ይገባል፡፡

እንዲህ ያለውን እኩይ ድርጊት በሰማ ጀሯችን ደግሞ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በቤተክርስቲያኗ ሥር ተቀጥረው ሲያገለግሉ የነበሩና ከሥራና ደመወዝ ታግደው የቆዩ ወገኖቻችን ውዝፍ ደመወዛቸው ጭምር ተከፍሎ ወደየሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ያስተላለፈው ውሳኔ ፓርቲያችንን ያስደሰተና አርዓያነት ያለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ሌሎች ተቋማትም ይህን አርዓያነት ያለው ተግባር ተከትለው ምንም ወንጀል ሳይፈጽሙ በትውልድ ሥፍራቸው ምክንያት ብቻ ከሥራ እንዲሁም ከሥራና ደመወዝ ታግደው ያሉ የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ፓርቲያችን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ ይህንን በዜጎች ላይ በሰበብ አስባብ የሚደርስ እንግልት ማስወገድ ችሮታ ሳይሆን የዜጎች መብት የመንግስት ደግሞ ግዴታ መሆኑን ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይህን ሕግን ሽፋን አድርጎ በንጹሓን ላይ የሚፈጸም ሰብዓዊ መብት ጥሰት በቅርበት በመከታተል ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም እናት ፓርቲ የጥቂቶች ስብስብ የሆነውና አገር ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን ትሕነግና አምላኪዎቹን በገቡበት ጉድጓድ ገብቶ የሚገባቸውን ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ የማያወላውል አቋም ያለው መሆኑን እየገለጽን ከዚህ በመለስ በሰበብ አስባቡ የታሠሩ ንጹሓን ወገኖቻችንን ሁኔታ በቅርበት በመከታተል፣ በማነጋገር፣ የሕግ ድጋፍ ጭምር የሚያገኙበትን አግባብና በኑሮ የተጎዱትን ለማገዝ የአቅሙን ያህል ጥረት እንደሚያደርግ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ
እናት ፓርቲ
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here