አርብ የካቲት 4 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ግሎባል አሊያንስ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ መሆኑ ተገለጸ።
ድርጅቱ በሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ለመጀመር ትናንት የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጧል።
እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምረው የሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ህይወት ሽመልስ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ትምህርት ቤቱ በአንድ ክፍል እስከ 120 ተማሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ እያስተማረ ይገኛል።
ትምህርት ቤቱ የመማሪያና አስተዳደር ክፍሎች ጥበት በተጨማሪ የውሃና የመጸዳጃ ቤት ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ችግር ተማሪ የመቀበል አቅሙን እንደገደበበት ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትውልድ ለመቅረጽ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ያለው የግሎባል አሊያንስ ቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ታማኝ በየነ፤ የትምህርት ቤቱን ችግሮች ለመፍታት የድርጅቱን አባላት በማስተባበር በቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግሯል።
ግንባታው እስከ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚፈጅና ሥራው በአፋር ልማት ማህበር በኩል የሚከናወን መሆኑን ጠቅሷል።
የአፋር ክልል ህዝብ ለሀገሩ ያለውን ዘመን የማይሽረው ታማኝነት በተግባር አስተምሮናል ያለው አርቲስት ታማኝ “በውጭ የምትኖሩ ወንድሞቼና እህቶቼ ወገናችሁ ለአገሩ እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በመረዳት በምንችለው ሁሉ ከአፋር ህዝብ ጎን ልንቆም ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
የአፋር ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኑረዲን ሰዲቅ በኩላቸው “ግሎባል አሊያንስና አርቲስት ታማኝ በየነ ከአፋር ህዝብ ጎን በመቆም እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ግብረሰናይ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው የትምህርት ቤት የማስፋፊያ 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለሁለት ብሎክና የአስተዳደር ህንጻን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ያካትት መሆኑን ጠቅሰው፤ ግንባታው በ8 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




