ኢትዮጵያ በመንግሥት የአስተዳደር ሥርዓት በተለያዩ ጊዜያት በሚገጥሟት ችግሮች ለዘመናት እየተፈተነች የመጣች ቢሆንም አሁንም ገና ከፈተና አልወጣችም። ኢትዮጵያን 27 ዓመታት በመራው በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር(ኢሕአዴግ) ሥርዓት ላይ በተለይ ከ2008 ወዲህ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ በ2010 ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር፣ ሕዝብ የጠላውን ሥርዓት እንደሚያስቀር እና የኢትዮጵያን ችግር እንደሚያቃልል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
ይሁን እንጅ፣ ኢትዮጵያ ከነበረባት ችግር መውጣት ቀርቶ የተባባሰ ግጭት እና ጦርነት ውስጥ ገብታለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሕአዴግን አክስመው ብልጽግናን መመስረታቸውን ተከትሎ ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥት አፈንግጦ ወደ ትግራይ መግባቱ ኢትየጵያ ለገባችበት ጦርነት ምክንያት ሆኗል።
ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ፣ በተለይ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት የጸጥታ ችግሮት ተባብሰው በመቀጠላቸው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። አገሪቱ በነዚህ የጸጥታ ችግሮች እና በጦርነት በተወጠረችበት ኹኔታ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መምጣቱን የሚያሳዩ አዝማሚያዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ብዙዎች እየገለጹ ነው።
መንግሥት ለጸጥታ ችግሮች መፍትሔ ማበጀት አለመቻሉን ተከትሎ የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት አለመከበሩ፣በአዲሱ የዐቢይ አስተዳደር ተስፋ ጥሎ የነበረው ሕዝብ የጠበቀው ነገር ሳይሆን ሲቀር ያለው ዕምነት እየተሸረሸረ እንደሚሄድ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነትን በተመለከተ ባለፉት አራት ዓመታት የነበሩ ኹነቶችን በማስታወስ እና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያን ሐሳብ በማካተት ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አደርጎታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነቱ እና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሠቱ ግጭቶች ዕልባት አለማግኘታቸውን ተከትሎ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መምጣቱን ብዙዎች እየገለጹ ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ግልጽ እና አሳማኝ መረጃ አለማቅረቡ ሲሆን፣ በተለይ ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚወስናቸው ውሳኔዎች የሕዝብን ፍላጎት ያላማከሉ እና የሕዝብን ይሁንታ ያላገኙ ናቸው የሚል ትችት በመንግሥት ላይ በርትቷል።
መንግሥት በቂ መረጃ ለሕዝብ ማቅረብና የሕዝብን ፍላጎት ያማከለ ግልጽ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት የሚሉ ሐሳቦች በማኅበረሠቡና ምሁራኑ በብዛት ቢንሸራሸርም፣ እስካሁን የሚፈለገውን ያክል አሳማኝ መረጃ እና ግልጽነት ከመንግሥት እንዳልመጣ እየተነገረ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ ሐሳብ የሠጡ ምሁራን በሕዝብ በኩል ለሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጋጣሚ በሚገኙባቸው መድረኮች ላይ የሚሰጧቸው ሐሳቦች አሳማኝና በቂ አለመሆናቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት ግልጽ ያልሁኑ አካሄዶችን ለሕዝብ ማብራራት እንዳለበት ጠይቀዋል።
በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች ላይ መንግሥት በግልጽ ለሕዝብ ማብራሪያ የሚሠጥበት ኹኔታ አናሳ መሆኑን ተከትሎ፣ ከሕወሓት ጋር በድብቅ እየተወያያ ነው የሚሉ ሐሳቦች ይሠማሉ። መንግሥት ከሕወሓት ጋር እየተነጋገረ ነው የሚሉ መረጃዎች በውጭ ሚዲያዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደርሰው ቢሆንም፣ ስለ ጉዳዩ ግለጽና አሳማኝ መረጃ በመንግሥት በኩል አለመሠጠቱ በሕዝቡ ውስጥ ጥርጣሬ የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑ እየተነገረ ነው።
ኢትዮጵያ በየጊዜው እየተቀሰቀሱ ለዘመናት አብረዋት የቆዩ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መጥተው በተለይ ከ2008 ወዲህ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተባባሰው የጸጥታ ችግር እና የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት በ2010 ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስተዳደር ችግሩን ያረግበዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ ከታሠበው በተቃራኒ ኾኖ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ካጋጠሟት ግጭቶች በተጨማሪ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።
በተለያዩ አካባቢዎች የተከሠቱ ግጭቶች “የለውጥ መንግሥት” ከተባለው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር መምጣት በኋላ ተባብሰው ቀጥለዋል። በተለይ በቤኒሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ክልል የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች መባባሳቸውን ተከትሎ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕይወታቸውን ገብረዋል። በሌሎች አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም፣ በኹለቱ ክልሎች ያለው ችግርና የንጹኃን ዜጎች ግድያ መቆሚያ ያጣ ሆኖ መቀጠሉ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋጋጥ ኾኖ ሳለ፣ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱን አልተወጣም የሚለው ሐሳብ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ምሁራን በተደጋጋሚ የተንጸበረቀ ሐሳብ ነው። በዚህም ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ዕምነት ዕያጣ እና ቀድሞ የነበረው ተስፋው እየተመናመነ መምጣቱን ብዙዎች በተለያየ መንግድ እየገለጹት ነው።
የመንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት በተለይ የፌድራል ሥርዓት በሚከተሉ አገራት፣ በአካባቢ፣ በክልል እና በአገር አቀፍ ደረጃ ከሕዝብ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት አገር በሚያስተዳደር መንግሥት እና በሕዝብ መካከል የሚኖረውን ግኝኑነት ዕጣ ፈንታ የሚወስን መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጸሐፊዎች ይገልጻሉ። ስለ መንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት የተጻፉ ጽሑፎች እና ጥናቶች እንደሚሳዩት የመንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት፣ በመንግሥት ሕዝብ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያብራራሉ።
ስኮት ካትሊፕ የተባለ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ተመራማሪና ጸሐፊ “የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት የሥልጣን መሣሪያ ነው” ይላል። ካትሊፕ እንደሚለው፣ አንድ አገር የሚያስተዳድር መንግሥት ከሕዝብ ጋር በሚያገናኙት ሚዲያዎች በኩል ውጤታማ “የሕዝብ መረጃ” ማድረስ ካልቻለ የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት የሥልጣን መሣሪያ መሆን አይችልም ይላል።
ሚካኤል ቱርነይ የተባለ ዓለም አቀፍ የኮሙኒኬሽን አማካሪ እና ጸሐፊ በግል ድረ-ገጹ ላይ “የመንግሥት ሕዝብ ግንኙነት” በሚል ርዕስ ባሠፈረው ጽሑፍ “ዲሞክራሲያዊ መንግሥታት የሕዝብን አስተያየት ሊያንፀባርቁ እና ዜጎቹ በደንብ አውቀው በተሻለ ሁኔታ ሊሠሩ ይገባል” ይላል። መንግሥት ከሕዝብ ጋር የሚኖረው ግንኙነት፣ የመግባባት እና ያለመግባበት አቅሙ ከዜጎች ጋር የሚኖረውን የወደፊት ግንኙነት ይወስናል ይላል ጸሐፊው።
የአራት ዓመታት “እንዘጭ እንቦጭ”
ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት የገዛው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር(ኢሕአዴግ) መንግሥት በሕዝብ ዘንድ የገጠመውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለን ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁ ብኋላ፣ መጋቢት 24/2010 ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት አራት ዓመት ሊሞላው አንድ ወር ከግማሽ ይቀረዋል።
በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረውን ችግር ለማርገብ የመፍትሔ አካል ለመሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው እና የዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዩ መድረኮች የሚያንጸባርቋቸው ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን የሚያጎሉ ሐሳቦች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አደርጓቸዋል። በዚህም የሕዝቡን ችግር እንደሚፈቱ እና ኢትዮጵያን የተፈታተናትን የጎሳ ብሔርተኝነት እንደሚቀርፉ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።
ኢሕአዴግን ከመሠረቱት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደሕዴን) መካከል ዋና የሆነው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቀስ በቀስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ጋር ተቃርኖ መጀመሩ የሚታወስ ነው። ይህንኑ ተከትሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ከሕወሓት ጋር የከረረ ልዩነት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ችግሩ ጥቅምት 24/2013 ከቃላት መወራወር አልፎ ወደ ኃይል ጦርነት ተቀይሯል።
ኢሕአዴግን አፍርሶ ብልጽግና ፓርቲን የመሠረተው የዐቢይ መንግሥት በተለይ ኢትዮጵያ በግልጽ ጦርነት ውስጥ ከገባች ብኋላ፣ በሕዝብ ዘንድ ተጥሎበት የነበረው ተስፋ ቀስ በቀስ እየተመናመነ እና የኢትዮጵያም ችግር እየተባባሰ መምጣቱን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።
የሰሜኑ ጦርነቱ በተለዋዋጭ ኹነቶች ታጅቦ አንድ ዓምት ከሦስት ወራት አስቆሯል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችም እየተባባሱ የዜጎችን ሞት፣ መፈናቀል እና ንብርት መውደም ማስቆም አልተቻለም።
አሁን አሁን “የለውጥ መንግሥት” ከተባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ችግር ተመልሶ መጣ የሚሉም ብዙዎች ናቸው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ተስፋ የተጣለበት ለውጥ መምጣቱ ቀርቶ ኢትዮጵያ አክሳሪ ጦርነት ውስጥ መግባቷ እና የጸጥታ ችግሮች ተባብሰው የዜጎች ሞት መቀጠሉን ነው።
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ከበደ ይማም(ዶ/ር) በመንግሥታት አስትዳድር ሦስት ዓይነት የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። እነዚህም አሳታፊ፣ ግማሽ አሳታፊ እና የማያሳትፍ እንደሚባሉ የሚገልጹት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በወቅቱ የነበረው ኹኔታ “አሳታፊ ዓይነት መስሎ፣ ኋላ እየባሰ መጣ” ይላሉ። መጀመሪያ የነበረው ኹኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ መምጣቱ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እንድሸረሸር በር እንደሚከፍት ይገልጻሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ሥልጣን እንደተረከበ በሕዝብ ዘንድ የነበረው የለውጥ ተስፋ በታሰበው ልክ አለመሔዱን እና የተጠበቀውን ውጤት አለማምጣቱን ይገልጻሉ። የነበረው ለውጥ በተጠበቀው ኹኔታ አለመሔዱን ተከትሎ፣ ሕዝብ የጠበቀውን ሲያጣ በሥርዓቱ ላይ ዕምነት የማጣት እና የግንኙነት መሻከር ያጋጠመበት ኹኔታ መኖሩን ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ አስተዳደሩ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አጥቷል ለማለት ጥናት እንደሚያስፈልግ የገለጹ ሲሆን፣ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ሕዝብ የሚፈልገውን መረጃ በግልጽ ማስረዳት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ምንን እንኳን መንግሥት ኹሉን ነገር ለሕዝብ ግልጽ ያደርጋል ባይባልም፣ ግልጽ ማድረግ የሌለበትን ነገር ከነምክንያቱ ማሳወቅ እንደሚገባው ይገልጻሉ። መንግሥት የሚወስናቸው ውሳኔውች የሕዝቡን ዘለቂ ጥቅም የሚያስጠበቁ መሆን አለባቸው የሚሉት መምህሩ፣ ውሳኔዎች በስሜት ሳይሆን በጥናት ላይ ተመርኩዘው መወሰን እንዳለባቸው ይጠቁሟሉ። እንዲሁም በሕዝብ በኩል ቅሬታ የሚፈጥሩ ነገሮች እና ግልጽ የማይሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ፣ ከስሜት በጸዳ ኹኔታ መረዳት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ጦርነት ጋር በተገናኘ በግልጽና በድብቅ ሊካሄዱ የሚችሉ ድርድሮች ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ አንዳንድ ጊዜ በድብቅ የሚደረጉ ደርድሮች ኋላ ላይ ሌላ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለዋል። በመሆኑም በመንግሥት በኩል የሚሠሩ ሥራዎች በጥናት የተረጋገጡ እና የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም ያሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የመንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት በመግባባት ላይ የተመሠረ መሆን አለበት የሚሉት መምህሩ፣ ግንኙነቱ መልካም እንዲሆን መንግሥት መጀመሪያ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ዓለበት ብለዋል። በአሁነ ጊዜ በዋናነት በመንግሥት ላይ የሚነሳው ጥያቄ፣ “መንግሥት ሥልጣኑን በአግባቡ አልተጠቀመም የሚል ነው” የሚሉት መምህሩ፣ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ብለዋል።
“ሥርዓት አልበኝነት እየመጣ ነው” የሚሉት ፖለቲካ ሳይነስ መምህሩ፣ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ካልተወጣ በሕዝብ ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነት እየተሸረሸረ ይሔዳል ብለዋል። መንግሥት በሕግ የተሠጠውን የሕግ ማስከበር ኃላፊነት በትክክል ማስከበር አለበት። መንግሥት ከሕዝብ ጋር ካልተግባባ እና መስጠት ያለበትን አገልግሎት በአግባቡ ካልሰጠ ግንኙነቱ እየተሸረሸረ እንደሚሄድ መግንዘብ አለበት ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌሎች አገሮች አንጻር ሲታይ ካልበዛበት ችግር ተሸክሞ የሚሔድ ሕዝብ ነው” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ መንግሥት ሥራውን በአግባቡ ከሠራ ሥርዓት የሚያከብር ሕዝብ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵ ሕዝብ ችግርን ተሸክሞ መኖር ይችልበታል ያሉት መምህሩ፣ ከመንግሥት የሚጠብቀው መሠረታዊ የሕዝብ ጥቅምና መበቶችን ማስከበር ነው ብለዋል። በመሆኑም መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መሠረታዊ መብት በተሠጠው የሕግ ሥርዓት መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል።
መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማስከበር ካልቻለ የሕዝብ ተስፋ በተሸረሸረ ቁጥር አመኔታ እንደሚያጣ ጠቁመው፣ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት ባለፈ ባለሥልጣናቱ ገለልተኛ ሆነው ሕዝቡን ማገልገል አለባቸው ብለዋል። አሁን የሚታየው ችግር የመንግሥት ባለሥልጣናት ሆነው የሆነ ቡድን እና ወገን ደጋፊ ሆነው ሕዝቡን በዕኩል ዐይን ያለማገልግል ነው የሚሉት መምህሩ፣ ባለሥልጣናት ከዚህ ወገንተኝነት ካልወጡ ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ እንደሚሄድ ተናግረዋል።
ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እንዳይሸረሸር እና መተማመን እንዲኖር ሁሉንም በሕግ፣ በሥርዓትና በእኩል ዐይን የሚያገልል ቁርጠኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መፈጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ሕዝብን በሕግና በሥርዓት የማያገለግል እና ለማገልግል ቁርጠኛ ያልሆነ የመንግሥት ባለሥልጣን የመንግሥት ችግር መሆኑን የሚጠቁሙት መምህሩ፣ “የመንግሥት ባለስልጣናት ከወገንተኝነት መውጣት አለባቸው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀ የሥነ-መንግሥት ታሪክ ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን፣ ከዚህ በፊት የነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቶች ውድቀትና ስኬት በታሪክ ይነገራል። በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እና የሕዝብን ፍላጎት ያከበረ መንግሥት ከሕዝብ ጋር አብሮ መዝለቅ ይችላል። የሕዝብ እና የመንግሥት ግንኙነት ለአንድ አገር እድገትም ይሁን ውድቀት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገለጻል።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014



