ሐሙስ የካቲት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አህመድ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከሕብረቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር በብራስልስ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባኤ ለመሳተፍ ትናንት ቤልጂየም ብራስልስ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል እና ከሕብረቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ጋር የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ወዳጅነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያለውን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለህብረቱ አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸውንም ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ በመንግስት በኩል የተለየዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ማስታወሳቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን መንግስት ያደረጋቸውን ጥረቶች ማብራራታቸውንም ሚኒስትር ዴታዋ ገልጸዋል፡፡
መንግስት በርከት ያሉ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሃት ቡድን ግን አሁንም በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ንጹሃን ዜጎችን ለሞት እየዳረገ፣ ብዙዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ መሆኑን ጭምር እንደገለጹላቸውም ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቡድንን ጥፋት ተገንዝቦ ሊያወግዘው እንደሚገባ መግለጻቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በህብረተሰቡ ላይ ትልቅ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በውይይቱ ላይ ማንሳታቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ አፋጣኝ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች በርካታ መሆናቸውን በመግለጽ መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የህብረቱ አመራሮችም የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጀመረውን ጥረት አድንቀው፤ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
መንግስት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳቱንም የህብረቱ አመራሮች ስለማድነቃቸው ሚኒስትር ድኤታዋ አውስተዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




