የምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢው መንግሥት ጣልቃ ከገባ ስልጣን እለቃለሁ አሉ

0
1705

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሠብሳቢ መስፍን አርአያ(ፕ/ር) መንግሥት በኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ኃላፊነታቸው እንደሚለቁ አስጠነቀቁ፡፡
የኮሚሽኑ ሠብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን ለመንግሥት ማሳሰቢያ የሠጡት የካቲት 16/2014 በተካሄደው የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን መጀመሪያ የሥራ ትውውቅ መድረክ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል ሆነው እንዲሠሩ ኃላፊነት የሠጣቸው ሕዝቡ በመሆኑ ሙሉ ጊዜያቸውን ሠጥተው በኃላፊነት መንፈስ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን እና ከሚዲያውና ሌሎች አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም፣ የአስፈፃሚው አካል ወይም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር ዕምነታቸው መሆኑን ጠቁመው በኮሚሽኑ አሠራር ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ ግን ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው እንደሚለቁ አሳስበዋል፡፡
የኮሚሽኑ አባላት በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ ለሚሠራው አገራዊ ምክክር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮዎችን በማካተት እና በሕዝቡ መካከል ብዙ የባህል ትስስሮች ስላሉ ዕድሉን ለሕዝቡ በመስጠት፣ እንዲሁም በማወያየት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች በውይይት በሚፈታበት ኹኔታ ላይ አበክረው እንደሚሠሩም መግለጻቸው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት በመሥራት የተሠጠውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታገሰ ጫፎ አሳስበዋል፡፡
በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንድ አካል መሆናቸውን ጠቁመው፣ የምክክሩ ባለቤት ሕዝቡ ስለሆነ ትክክለኛ ውሳኔ የሚጠበቀው ከሕዝቡ እንደሆነም አፈ ጉባኤው ተናግረዋል፡፡ አክለውም ኮሚሽኑ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊው የሠው ኃይል፣ ቢሮ እና ግብዓቶች ሊሟሉለት ስለሚገባ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር አስፈለጊው በጀት እንደሚመደብም ጠቁመዋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here