የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ረቡዕ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማስጀመራቸውን ተከትሎ፣ የሩሲያ ወታደሮች የዩክሬን ድንብር አቋርጠው በግዛቷ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ነው፡፡
ፑቲን የዩክሬን ወታሮች መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደቤታቸው እንዲመለሱም ያሳሰቡ ሲሆን፣ “ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ዕቅድ የላትም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ሆኖም ግን ሩሲያ ፊት የሚቆም ማንኛው ኃይል ካለ የሚሰጠው ምላሽ የከፋ ይሆናል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ዩክሬን በበኩሏ “ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሙሉ በሙሉ ወረራ መፈጸም ጀምረዋል” በማለት ከሳለች። የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደምየትሮ ኩሌባ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “በሠላማዊ የዩክሬን ከተማዎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ በተጀመረ በኹለተኛው ቁን ሩሲያ የዩክሬንን 11 የአየር ኃይል ጣቢያዎችን ጨምሮ፣ 74 ወታደራዊ ዒላማዎችን ማውደሟን አስታውቃለች፡፡ የአየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያዎችን ጨምሮ 18 ራዳሮችን ማጋየቱንም የሩሲያ ጦር ገልጿል፡፡
ከኹለቱ አገራት ጦርነት መጀመርን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከስምንት ዓመት ብኋላ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ንረት ተከስቷል፡፡ ከጦርነቱ መጀመር ብኋላ አንድ በርሜል ነዳጅ 105 ዶላር መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ የሩሲያ የጦር ጀቶችንና ሂሊኮፕተሮችን በግዛቷ ውስጥ መትታ መጣሏን አስታውቃለች፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድይምይር ዘለንሰክይ መዋጋት ለሚፈልግ አገሪቱ ዜጋ መሣሪያ እንደሚያስታጥቁ የገለጹ ሲሆን፣ አገሪቱ የአየር ክልሏን በመዝጋት የሲቪል በረራዎችን አቋርጣለች፡፡ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ ዩክሬን 40 ወታደሮችና 10 ንጹኃን ዜጎች እንደሞቱባት ገልጻለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና አሜሪካን ጨምሮ ጦርነቱ እንዲቆም እየተማጸኑ ነው፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ጦርነቱ እንድታቆም ጫና ለመፍጠር የተለያዩ ማዕቀቦች በሩሲያ ላይ እየጣሉ ነው፡፡ ባይደን በይፋዊ ማኅበራዊ ገጻቸው ከዩክሬን ጎን መሆናቸውን ገልጸው፣ በሩሲያ ላይ ጫና ማሳደራቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014


