እንደወጡ የሚቀሩ ሠዎች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ እና አድማሱን እያሰፋ ከመጣው ከኑሮ ውድነት፣ ከዋጋ ግሽበት፣ ከሥራ አጥነት፣ በሕገ ወጥ አካላት ከሚፈጸም ጥቃትና ዝርፊያ ባሻገር፣ የሠዎች መጥፋትና መሠወር አሳሳቢና ብዙዎችን እያስጨነቀ የመጣ ጉዳይ ነው ፡፡

በዓለም ላይ በየዓመቱ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሠዎች እንደሚጠፉ በየጊዜው የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በዓለማችን ላይ ባለፈው ዓመት ብቻ ከአንድ መቶ ሺሕ ሠዎች በላይ መጥፋታቸው/መሠወራቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት ቁጥራዊ መረጃዎች ከሆነ፣ ባለፈው ዓመት ከጠፉ ሠዎች ውስጥ ወደ 20 ሺሕ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፣ ከ 60 ሺሕ በላይ የሆነውን ቁጥር የያዙት ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡ እንደጥናቶቹ ከሆነ፣ ከነዚህ ከሚጠፉ ሠዎች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ደግሞ ተመልሰው እንደማይገኙ ነው የተገለፀው፡፡

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይ ሲ አር ሲ) ዓለም አቀፍ የመጥፋት ቀንን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ የሚያሳየው፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከ44 ሺሕ በላይ ሠዎች ከአህጉራችን አፍሪካ መጥፋታቸው መረጋገጡን ነው፡፡ ከጠፉት ሠዎች መካከል ከ 45 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕፃናትና ሴቶች መሆናቸው ነው በመረጃው የተገለጸው፡፡

በዓመቱ አፍሪካ ውስጥ ከጠፉት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍኑት ደግሞ ናይጄሪያውያን ናቸው። በናይጀሪያ ወደ 24 ሺሕ የሚጠጉ ሠዎች መጥፋታቸው ተመዝግቧል። በርካታ የጠፉ ሠዎች ቁጥር የተመዘገቡባቸውን ሌሎች የአፍሪካ አገራት ስንመለከት ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ካሜሩን ይገኙበታል።

በኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት ብቻ፣ ከሦስት ሺሕ ሦስት መቶ በላይ ሰዎች ጠፍተዋል በሚል በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥ 64 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው ተብላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ደብዛቸው ጠፍቷል ለተባሉት ለእነዚህ ዜጎች መጥፋት በርካታ ምክንያት የተቀመጠ ሲሆን፣ በዋናነት የፀጥታ ችግሮ፣ ግጭት፣ ሥደት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዋናዋናዎቹ ናቸው።

ድርጅቱ እንዳመለከተው ከሆነ፣ ባለፉት ዓመታት የተከሠቱ ግጭቶችንና ጦርነቶችን ጨምሮ፣ ሌሎች የጥቃት ዓይነቶች በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደብዛቸው ለጠፋ ሠዎች ቁጥር መጨመር ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸው ተነግራል ።
ከዚህ ባሻገር፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በተጣሉ ገደቦች ሳቢያ የጠፉ ተጎጂዎችን ለማግኘት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማቀላቀል የሚደረገው ጥረት መደናቀፉ ቢገለጽም፣ የጠፉ ሠዎች የተረሱ ሠዎች አይደሉም ተብላል ፡፡

በኢትዮጵያ ከአምስትና ስድስት ዓመታት በፊት ብዙ ሠዎች ጠፉ ሲባል የሚሠማውና የሚስተዋለው በክልሎች፣ ወረዳና ቀበሌዎች የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን በመዲናችን አዲስ አበባም ጭምር ሠዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወጡ ሳይመለሱ የሚቀሩበት ዕድል እየጨመረ መምጣቱን በርካታ የከተማዋ ናሪዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህም በርካታ ዜጎችን፣ በተለይም ወላጆችን ለጭንቀት እየዳረገ መምጣቱ በሠፊው ይነገራል፡፡

በአዲስ አበባ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ውጣ ውረዶች ጭምር፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሚኖሩበት አከባቢ ወደሌሎች አገራት የሚሠደዱና የሚጠፉ ሠዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡
እነዚህ ‹ጠፉ› የተባሉ ሠዎችን ቤተሰቦቻቸው በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ፣ መንገድ ላይ በሚለጠፉ በራሪ ወረቀቶችና ሌሎች ልዩልዩ አማራጭ ዘዴዎች ጭምር ሲያፈላልጉ ማየትም እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው ፡፡

በተለይ ባለፉት አንድ እና ኹለት ዓመታት ውስጥ፣ በመዲናዋ ዜጎችን እያስጨነቁ ከመጡ፣ ነገር ግን ብዙም ትኩረት ካልተሠጣቸውና ዕይታ ከተነፈጋቸው ጉዳዮች መካከል የሠዎች መሠወር/መጥፋት ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ሠዎች ሕግን በማያከብሩ አካላትም ጭምር የሚገደሉበት ኹነት እንዳለ የብዙዎች ትዝብት ነው ።

ምንም እንኳ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እነዚህ ተደጋጋሚ የሕግ ጥሰቶች እንዲቆሙና መንግሥት ሕግንና በሕይዎት የመኖር ሠብዓዊ መብትን እንዲያስከብር፣ ወንጀል ፈፃሚ አካላትንም ለሕግ እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ቢወተውቱም አጥጋቢ መፍትሔ ተገኝቷል ለማለት ግን አያስደፍርም ፡፡

ስለጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ከሠጡት መካከል የሥነ-ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሻረው አለማየሁ አንዱ ናቸው። ሻረው፣ በአዲስ አበበ ከተማ በየጊዜው ሠዎች ከቤት እንደወጡ የሚጠፉበት ኹኔታ በሥፋት እንደተስዋለና ብዙ ቤተሰቦችንም ለጭንቀት እየዳረገ መምጣቱን እንደታዘቡ ያስረዳሉ፡፡

ወጣቶችና በዕድሜ የገፉ ሠዎች የሚጠፉበትም ዕድል እንዳለ የጠቀሱት ባለሙያው፣ በብዛት ከመኖሪያ አካባቢያቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከቤት እንደወጡ ሳይመለሱ የሚቀሩትና የሚጠፉት በጉልምስና እና በልጅነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሠዎች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ለዚህ ደግሞ ከጉልምስና ዕድሜ ጋር ተያይዞ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያነሱት የሥነ ልቦና ምሁሩ፣ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ሥሜታዊ ለውጦች በነዚህ ወጣቶች ላይ በሚከሰቱበት ወቅት የሚረዳኝ ሠው አይኖርም ብለው ስለሚያስቡ፣ ከቤተሠቦቻቸው ጋር ጭምር የማይስማሙበት ዕድል ሊሠፋ ኹሉ ስለሚችል ለመጥፋት ይጋበዛሉ ባይ ናቸው።

በተመሳሳይ የቤተሠብ አባላት፣ ሕፃናት ፣ሴቶች፣ እንዲሁም ወጣቶች ላይ የስሜት መለዋወጥ በሚያስተውሉበት ወቅት፣ ከማማከርና ስለጉዳዩ ጠይቆ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ፣ እሰጥ-አገባ ውስጥ በሚገቡበትና ያልተፈለገ ውሳኔ በሚያስቀምጡበት ጊዜ፣ ልጆች ለመጥፋት ተገፋፍተው ከቤተሰቦቻቸው ሊለዩና ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወጡ ሊቀሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ሠፊ ነው ብለዋል።

የሥነ ልቦና ባለሙያው የሚጠፉ ሕፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶችን ለመታደግ የሚያስችሉ ኹለት ነጥቦችን እንደመፍትሔ ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመሪያ የሚሉት በቅድሚያ ወላጅና ቤተሠብ፣ ሕፃናት ሴቶችና ወጣት ልጆች ላይ የተለያዩ የስሜት መለዋወጦች ሲያስተውሉ ምክር ቢሠነዝሩ፣ ለመጥፋት ገፊ የሚሆኑ ምክንያቶችን ሊቀንሱ የሚችሉበት ኹኔታ እንደሚኖር ነው የተናገሩት።

ባለሙያው በኹለተኛነት ያነሱት ባለሙያዎችን እና የመጠለያ ተቋማትን ጉዳይ ነው፡፡ ባለሙያው፣ ሠዎች ከጠፉ በኋላ ሥነ ልቦናቸውን የሚያክሙና ስሜታቸውን ሊረዱ የሚችሉ ባለሙያዎች ፣ እንዲሁም ሊሰበስቧቸው የሚችሉ መጠለያ ተቋማት በመንግሥት በኩል ቢሟሉና በሥፋት ቢዘጋጁ የተሻለ እንደሆነ አመላክተዋል። ይህ ዓይነቱ ዕድል በኢትዮጵያ የሚስፋፉ ከሆነ የሚጠፉ ሠዎችን መታደግ እና ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎችን መፍጠር እንደሚቻል ያምናሉ ።

በኢትዮጵያ ዜጎችን ለመታደግ እየተገነቡ ያሉ ተቋማት በወጣትነትና በጎልማሳነት ላይ የሚገኙ አካላትን የሚያገለግሉ ናቸው ያሉት ሻረው፣ የወጣቱን ጥያቄና ነባራዊ ኹኔታ ያገናዘቡ የመዝናኛና ማስተማሪያ ተቋማት መንግሥት ቢገነባ የተሻለ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አያይዘውም፣ ብዙ ጊዜ እየጠፉ ያሉ ሠዎች በምን ዓይነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ናቸው? ከየት አከባቢና በምን ዓይነት ምክንያት ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ላይ ተንተርሶ መንግሥት ሠፊ ጥናት ማካሄድና ውጤቱንም ለሕብረተሠቡ ማሳወቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሠዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወጡ ሳይመለሱ በሚቀሩበት ወቅት፣ ቤተሰቦቻቸው ለፀጥታና ለፍትሕ አካላት ማሳወቅ ቀዳሚ ሥራቸው ሊሆን ይገባል የሚሉት ደግሞ የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው፡፡
ዜጎች ራሳቸውን በዕውቀት፣ በመረጃና በግንዛቤ የማዳበር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ በፀጥታና በፍትሕ አካላት በኩልም የሠዎች አያያዝ ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራር ቢኖር ጥሩ እንደሚሆን ያሠምሩበታል፡፡

ባለሙያው አክለውም፣ በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው ከሚጠፉ ከሕፃናት ሴቶችና ወጣቶች ባሻገር፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወጡ በፀጥታ አካላት ተይዘው የሚታሠሩና ለጊዜው የት እንዳሉ የማይታወቁ ሠዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ታዝቢያለሁ ባይ ናቸው፡፡
ከዚህ አንፃር፣ ሕገ-መንግሥቱ ዜጎች የአካል ደኅንነትና ነፃነት እንዳላቸው ስለሚደነግግ፣ ሰዎች በሕጉ መሠረት መያዝ ካለባቸው ያሉበትን ማሳወቅ የሕግ አካላት ግዴታ ነው፡፡

ሠዎች በሕግ አስከባሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸውም ሆነ ከሥራቸው እንደወጡ በሚቀሩበትና በሚያዙበት ጊዜ ለምን ተጠረጠርኩና ለምን ተያዝኩ የሚሉበት ዕድል ባይኖርም፣ ሕጉን ባልጠበቀ መንገድ ከሆነ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ በመሆኑ ዜጎች መብታቸውን ሊያስከብሩና ሊጠይቁ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የፍትሕና የፀጥታ አካላት ለዜጎች መብት መከበር ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ጥጋቡ፣ ከዚህ ባለፈ ሠዎች በምን ዓይነት ወንጀል እንደተጠረጠሩ ሳይነገራቸው በፀጥታ አካላት የሚያዙበት ኹኔታ መሥፋፋቱና ዜጎችን ለፍትሕ ሳያቀርቡ ሠውሮ ማቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይሠመርበት ባይ ናቸው ፡፡

የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ አክለውም፣ ዜጎች በሕግ አካላት ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የፍትሕ ውሳኔ ሳይሠጣቸው ኹለት ወርና ከዚያ በላይ ታስረው የሚቆዩበት ኹኔታ ሊስተካከል ይገባዋል ብለዋል፡፡ የዜጎች መብትና ነፃነት ሰብዓዊና ሕጋዊ ጉዳይ በመሆኑ፣ የፀጥታና የፍትሕ ተቋማት ይህን አለማክበራቸው የሕገ-መንግሥት ጥሰት ስለሚያስከትል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው የጠየቁት፡፡ ዜጎችም በፀጥታ አካላትም ሆነ በሌሎች ግለሰቦች ተገደው በሚያዙበት ወቅት፣ ያዥዎቻቸውን ማንነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ እንዲያሳይዋቸው መጠየቅ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት ፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here