የአድዋ ድል ዓለም ዓቀፋዊነት

0
1303

ከ125 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአድዋ ድል ጥቁሮች በቅኝ ግዛት ውስጥ በነበሩበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ያለማንም አጋዥነት ጣልያንን ድል ማድረጓ በወቅቱ በመላው ዓለም የተለዬ ተፅዕኖ መፍጠሩ ይነሳል፡፡
ድሉ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ያዩበት የነበረውን መነጽር የቀየረ ከመሆኑም በላይ፣ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁሮችም ለነጻነት የሚያደርጉትን ተጋድሎ በተለዬ ኹኔታ አጧጡፈው እዲቀጥሉ ያደረገው ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ጣልያንን ድል ካደረገች በኋላ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ፡፡

ድሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጸረ-ቅኝ ግዛት ትግሉ የተጫዎተው ሚና የጎላ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የሚገባውን ያህል ቦታ እየተሠጠው አይደለም የሚሉ አሉ፡፡
የአድዋ ድል የአፍሪካ በዓል እንዲሆን እና በዓለም ላይ ያሉ የነጻነት ታጋዮችም ቀኑን እንዲዘክሩት በማድረጉ ረገድ ኢትዮጵያ የሚገባውን ያህል አለመሥራቷን በማንሳት ብዙዎች ወቀሳ ያቀርባሉ፡፡
የአድዋን ድል ዓለመረ አቀፋዊ ይዘት፣ እንዲሁም የድሉን ምንነት ባለሙያ በማናገርና የተለያዩ መዛግብትን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳው ሳሙኤል ታዴ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የነጻነት ጉዳይ ሲሆን፣ ለሌሎች አፍሪካውያን እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች ግን እንደ ሠው መቆጠርንያሳዬ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ብዙ ጥቁሮች ከዚያ ቀድሞ ራሳቸውን እንደ (ነጻ)ሠው ለመቁጠር ይቸገሩ የነበረውነጮ ቅኝ ገዥዎቻቸውትክክለኛ የሠው ፍጥረት እኛ ነን በማለት ይሰብኳቸውና ራሳቸውን እንደ ሠው እንዳይቆጥሩ ያስፈራሩዋቸው ስለነበር ነው የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡
በዚህም ኢትዮዮጵያ ከነጭ ወራሪ ጋር ጦርነት ለማድረግ ማቀዷ ሳይቀር ያስደንቃቸው ነበር፡፡ በጦርነቱም ወቅትኢትዮዮጵያየነጭ ወታደር ገድላ እና ማርካ ነጻና ሉዓላዊት አገር መሆኗን ሲያዩ፣ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁሮች እሷን አብነት በማድረግ ሠው መሆናቸውን ከመቁጠር ባለፈ ለነጻነታቸው መታገል እንደጀመሩ ታሪክ ያወሳል፡፡

ከኹለት መቶ ዓመት በላይ በቅኝ ግዛት ከኖሩት ደቡብ አፍሪካውያን የተገኙት ኔልሰን ማንዴላም፣ ለነጻነት ትግል እንቅስቃሴያቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሱዳን በደረሱ ጊዜ ካዩት ነገር እጅግ ያስገረማቸው ጥቁር አውሮፕላን አብራሪ ኢትዮጵያውያንን ማየታቸው እንደሆነ በወቅቱ ገልጸው እንደነበር ይነገራል፡፡

እንዲሁም፣ከአድዋ ድል በኋላ በርካታ የአፍሪካ አገራትም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ቀለማትን በተለያየ መልኩ መጠቀማቸው የድሉ ውጤት መሆኑን ታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡
በዋልታ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ የሆኑት ተረፈ ወርቁ የአድዋን እና አፍሪካዊ ዕሳቤን በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ በሠጡት ማብራሪያ፣የአፍሪካን ታሪክ፣ ቅርስና ባህል አካቶ የያዘው ፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ ከአድዋ በፊት የነበረ ነው፣ ሆኖም ግን የአድዋ ድል ለእንቅስቃሴው ትልቅ ጉልበት ሆኗል ነው ያሉት፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ በጃማይካና በካረቢያን አገሮች የተጀመረ መሆኑን አንስተው፣ ኢትዮጵያኒዝም በሚባለው ዕሳቤ ውስጥ ጎልተው የሚጠቀሱት ጃማይካዊው ማርከስ ጋርቬይና አፍሪካ አሜሪካዊው ዊሊያምድ ቦይ (Father of Pan Africanism)ደግሞ የአድዋን ድል በላቀ ኹኔታ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴመስፋፋት እንደተጠቀሙበት አመላክተዋል፡፡

በዚህም፣ አውሮፓውያን አፍሪካ ባህል፣ ቅርስ፣ ታሪክ እና የራሷ አስተዳደር የሌላትየጨለማ ምድር አድርገው ይቆጥሯት ስለነበር፣ በእነ ማርከስ ጋርቬይ እንቅስቃሴ ውስጥየኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከግሪክና ከሮም ሥልጣኔ አቻ ነው የሚለውን የጥንታዊ ግሪኮችን ጽሑፍ በመጠቀም እና የአድዋን ድል በማንሳት ለቅኝ ገዥዎችን ምላሽ ይሠጡ እንደነበር ጠቅሠዋል፡፡

ማርከስ ጋርቬይም ዓለም አቀፍ የጥቁሮችን መዝሙር በጻፈበት ወቅት አድዋን እያነሳ ኢትዮጵን ብዙ ጊዜ ይጠቅስ እንደነበር ገልጸው፣ ስለዚህም የአድዋ ድል በዓለም አቀፍ የሠው ልጆች ዘንድ የነጻነት ተምሳሌትና የጥቁሮች በተለይ የነጻነታቸው ዓርማ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ባለሙያው፣ መላው ጥቁሮች በቅኝ ግዛት ሥር በነበሩበት ጊዜ እንዴት ኢትዮጵያውያን ብቻቸውን ድል በማድረግ ነጻነታቸውን ሊያስከብሩ ቻሉ የሚለውን በማካተት የነጻነት ፍልስፍና ሆኖ ሊመረመር ይገባዋል ባይ ናቸው፡፡

ድሉ ነጮችን ያሸማቀቀ፣ ለፓን አፍሪካ እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች የነጻነት ትግል የነበረው ጉልበት ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ የፓን አፍሪካ ኮንፈረንስ ላይ እንዲሳተፉ ጥቁሮች ወደ አጼ ምኒልክ አንድ የሀይቲ ተወካይ ልከው ነበር ይላሉ፡፡
ተወካይ ልከው መሳተፋቸውን ያነሱት ባለሙያው፣ ብዙ መድረኮችም በመላው ዓለም መፈጠራቸውንና በአፍሪካም የፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ተጧጡፈው የቀጠሉት ከአድዋ ድል ማግስት መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በአድዋ ድል ጉልበት ያገኘው የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ወደ ማቋቋም ነው የሔደው የሚሉት ባለሙያው፣ የአድዋ ድል ወደ ጥንታዊ አፍሪካዊ ማንነታችን መመለስ አለብን የሚለውን ዕሳቤ በመፍጠርም ትልቅ የፖለቲካ ፍልስፍና ሆኖ አገልግሏል ሲሉ አትተዋል፡፡

በአፍሪካ ከሚታዎቁት ታላላቅ መሪዎች አንዱ ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመሠልጠናቸውና ኑክሩማህም ኹሌ በንግግራቸው ‹አፍሪካ አንድ መሆን አለባት፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ይሉ የነበሩት፣ በአድዋ ድል የተነሳ መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ድሉ የሚገባውን ቦታ እንዳልተሠጠው ዘርዝረዋል፡፡

ለአብነትም በአፍሪካ ኅብረት ድሉን የሚያስታውስ ምንም ነገር አለመኖሩን ጠቅሰው፣ በትምህርት ተቋሞቻችን፣ በባህልና በፖለቲካም ውስጥ የሚገባውን ሥፍራ አላገኘም ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ብዙ አገሮች ያላቸውን ትንሽ ድል አግነው ያከብሩታል ያሉት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለን የታሪክ አለመግባባትና የተንሸዋረረ የታሪክ ዕይታ ድሉን መጠቀም እንዳልተቻለ ይጠቅሳሉ፡፡

አሜሪካ በቬትናም ለተሸነፈችበት ጦርነት 100 የሚጠጉ ፊልሞችን ሠርታለች፤ እኛ አገር ግን አድዋን በጥልቀት የተመለከተ የጥበብ ሥራ አላውቅም ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ቆንጽላዎች እንኳን ድሉን በባህል መልኩ እንዲያከብሩት ቢደረግ ቢያንስ በአፍሪካ ያለውን ተጽዕኖ ያጎላው ነበር በማለት የገለፁት ባለሙያው፣ በዓለም ያለን ተጽዕኖ አናሳ መሆኑና ለታሪክ ያለን ዕይታ ከአድዋ መጠቀም ያለብን ሳናገኝ እንድንቀር አድርጎናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ100 ዓመት በፊት የዓለም መንግሥታት ማኅበር ብቸኛ አፍሪካዊት አባል አገር ለመሆኗም መሠረቱ የአድዋ ድል መሆኑ የሚረሳ አይደለም፡፡ይህ አባልነቷ ለራሷ ከሚሠጣት ጥቅም ባሻገር፣ በጥቁሮች ዘንድ እንደ ነጻ አገር ለመቆጠር እና ለእኩልነት መታገልን ለማጋጋል ኃይል ሆኖ ታይቷል፡፡

በወቅቱ ‹ለንደን ታይምስ›የተባለ ጋዜጣም ‹‹የኢጣልያኖች በምኒልክ መሸነፍ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ነው፡፡ ይኸም ድል አድራጊነት እስከዛሬ አረመኔ የተባለው በአውሮፓውያን ይናቅ የነበረውን የአፍሪካ መንፈስ የሚቀሰቅስ ነው›› ሲል አስነብቧል፡፡
የአድዋ ድል በአውሮፓ ሲሠማም በየአገራቱ የተለያዩ ስሜት እንደፈጠረ በተለይ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል፡፡ በዚህም ጣልያን በኤርትራ በኩል ፈረንሳይን እየተነኮሰች ታስቸግራት ስለነበር በፈረንሳይ በኩል የፈጠረው ስሜት የደስታ ቢሆንም፣ አንዳንድ ዘረኛ ነጮች ግን የጥቁርን አሸናፊነት አስቆጥቷቸው እንደነበር ጽፈዋል፡፡

በሩስያ አገር ያለው ስሜትም ከፈረንሳይ ጋር ተመሳሳይ እንደነበርና እንዲያውም የመስኮብ መንግሥት ወዳጅነቱን ለመግለጽየቀይ መስቀል ጓድ ወደ ኢትዮጵያ ልኮ በአድዋ ጦርነት የቆሰሉትን በማከም ስለረዳ ከንጉሠ ነገሥቱ ምስጋና እንደተቸረው ተመዝግቧል፡፡
ድሉ በጣልያን አገር በተለይም በሮም ከተማ ሕዝቡን አበሳጭቶ እንደነበርና ተቃውሞ እንዳስነሳም የሚጠቀሰው፡፡ተቃዋሚዎቹም ‹‹ክሪስፒ ይውደቅ፤ ምኒልክ ሕያው ይሁን›› እያሉ ይጮሁ እንደነበርና የአገራቸው ውርደት የተሠማቸው ኹሉ ‹‹አንድ ድል እንጠብቃለን›› ወይም ‹‹አንድ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚደመድም ድል ሳታገኝ ዕርቅ የለም›› እያለ ባራቴሪን በቴሌግራፍ ያጣድፍ ወደነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ቤት ሔደው በመሳድብና ቤቱን በደንጋይ በመደብደብ ያስቸግሩት ነበር፡፡ ክሪስፒም ‹‹የወታደርዎን ደም ጊዜ ጠብቀው ይበቀሉለት›› የሚል ቃል ጽፎ ከሥልጣኑ እንደተሠናበት ተክለ ጻድቅ በመጽሐፋቸው አትተዋል፡፡

ሌሎችነጮችም በጥቁር መሸነፋቸው ከሚያሳቅቃቸው በላይ፣ ሌሎች ጥቁሮችን ለአመጽ ሊያነሳሳ ይችላል በሚል በቅኝ ግዛት አስተዳደራቸው ላይ ችግር ይፈጥርብናል በማለት ፍርሀት አድሮባቸው እንደነበር ተጽፏል፡፡
በተለይ እንግሊዛውያን ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ድል ማድረጓ የበለጠ እንዳሳሰባቸው የሚያመላክተው በዚያው አገር ይታተም የነበረው ለንደን ታይምስ ጋዜጣ ‹‹… የርሱም (የምኒልክ) ድል ማድረግ የመላ አፍሪካ ድል ነው፡፡ ይኽ ዓይነቱ አስተያዬት ወደፊት እያዬለ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች (አፍሪካውያን ዘንድ) ወሬው በንፋስ ክንፍ በረሀውን ሁሉ አቋርጦ በፍጥነት የሚሮጥ ስለሆነ ከጫፍ እስከ ጫፍ አሁንም ታውቋል፡፡

… ስለዚህ ጉዳዩ አደገኛ ስለሆነ በኢጣልያኖች መሸነፍ መደሠት አይገባም፡፡ ይኽ መሸነፍ የኹላችንና የሌሎችም ጭምር መሸነፍ ነው፡፡ የሥልጣኔ መሸነፍም አይደለም፣ የቅኝ አገር ገዥ የሆነችውና የነገይቱም አውሮፓ መሸነፍ ነው… ›› በማለት ነበር ለአፍሪካውያ ንቃት እና የመከላከል ስሜት ስለፈጠረው የአድዋ ድል ያተተው፡፡

የጀርመን ንጉሠ ነገሥትም የኢጣልያን መሸነፍ ጋዜጦች ሲቀባበሉት በሠማ ጊዜ ለማጽናናትና የወዳጅነት ስሜቱን ለመግለጽ ወደ ሮም አቅንቶ የኢጣልያን ንጉሥ እንደጎበኘ ተጽፎለታል፡፡
በጥቅሉ የአድዋ ድል የአፍሪካዊነት ዕሳቤ መሠረት፣በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች የነጻነት ፋና ወጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ይሁን እንጂ፣ የአድዋ ድል እስካሁን ድረስ ያለው አገራዊ ምንነትና ፋይዳም ይሁን፣አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘቱ ምን ድረስ እንደሆነ በሚገባ እንዳልተፈተሸ ይነገራል፡፡ ለዚህም የሚነሱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይ በምሁራን ሳይያዝ የቆዬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድሉን በማደብዘዝ አገራዊ ፋይዳው እንዳይጎላ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ምክንያት በአፍሪካ ያላትን የተሠሚነት አቅም ሳትጠቀምበት እንድትኖር አድርጓት መዝለቁን ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ፍቅሩ ገብረኪዳን ‹‹International Journal of Ethiopian Studies›› ላይ ባሳተሙት ጽሑፋቸው፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፖለቲካ መሪ ተዋናይ ነበረች ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን ያ መሪነት አሁን ላይ በታሪክ፣ ፖለቲካና ግለሠባዊ ኹነቶች ተጽዕኖ ውስጥ ወድቋል ባይ ናቸው፡፡

ሕፃናት እና የአድዋ ድል
የአድዋን ድል ምንነት በተገቢው ኹኔታ ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገርም ይሁን አሁን ካለበት ይበልጥ በማጉላት ዘመናትን እንዲሻገር ለማድረግ፣ሕፃናት ላይ መሥራት ትልቁ መፍትሔ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ የካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት የሕፃናትና ታዳጊዎች ክፍል ኃላፊ ፍጹም ኃይለ ሚካኤል፣ አድዋ የድል በዓል እንደመሆኑ ከቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ የአልሸነፍም ባይነትና አልገዛም ባይነትን ምንነት፣ አባቶቻችን ያሳዩትን ጀግንነት፣ ባህላችንና ዕምነታችን እንዳይበረዝ ያደረጉትን ተጋድሎ ትውልዱ በደንብ እንዲገነዘበው ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለው ትውልድ የአባቶቻችን እና የእናቶቻችንን ገድል በሚገባ የተገነዘበ አይደለም ያሉት ፍጹም፣ ሕፃናት ላይ መሥራቱ ከዚህ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሕፃናትንእንደየዕድሜያቸው በመከፋፈል፣ በቀለም ትምህርት እንዲሁም በፊልምና በሌሎች የማስተማሪያ መንገዶች ቅኝ ግዛትና አልገዛም ባይነት ምን እንደሆኑ በማስተማር የበኩሉን እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህም መደረጉ በወቅቱ አባቶቻችን ወረራውን በምን ዘዴ እንዳሸነፉ፣ ምን እንደተቀሙ፣ ለምን ቅኝ ግዛትን አንቀበልም እንዳሉና ቢቀበሉ ኖሮስ ምን ይከሠት እንደነበር፣ቅኝ የተገዙ አገራት ያጋጠማቸውን በመጥቀስ ታዳጊዎችን ለማስገንዘብ ይረዳል ባይ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕፃናትም በዓሉ በሚከበርበት ወቅት በአደባባዮች ተገኝተው ዕለቱን በሚገልጽ አለባበስ እና ያንኑ የሚያወሱ ግጥሞችን ሲቀባበሉና እና መዝሙሮችን ሲዘምሩ ይስተዋላል፡፡

ለአብነትም በዓሉ ለ125ኛ ጊዜ በሚከበርበት ወቅትበተለይም በአዲስ አበባ፣የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እና የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአድዋ ድል መታሰቢያ በሚከበርበት ወቅት የበዓሉ አንድ አካል ሆነው ሲያከብሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዕለቱም ተሳታፊዎቹ የተለያዩ ሽለላዎችንና ፉከራዎችን እንዲሁም ግጥሞችን ሲደርድሩ ይታይ ነበር፡፡ በዕለቱ ካደረጓቸው ሽለላና ግጥሞቻቸው መካከልም ጥቂቶቹ፡
ኧረ ተው ተመለስ አንተ ነጭ በሬ
ከጠመደ አይፈታም ያገሬ ገበሬ፡፡
ያ ማዶ ተራራ ምነው አኮረፈ
በጀግናው ጎራዴ ደም እያጎረፈ፡፡
ምኒልክ አማኝ ነው ጸሎት አስቀደመ
ኃይሌ አንተነህ ብሎ አድዋ ላይ ቆመ፡፡
ጣይቱ ሴት ነኝ አለች ጦርነት አልወድም
ባገሬ ከመጣ ማንንም አልምርም፡፡

ዘንድሮ ለሚከበርው 126ኛ የአድዋ ድል መታሰቢያም እንዲሁ በሠፊው እየተዘጋጁ ያሉ ታዳጊዎች መኖራቸው ይሠማልና ይህም እጅግ ትልቅ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይገለጻል፡፡

የካቲት 23/1888
የጣልያን ትንኮሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እና በኋላ ላይም የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 የኢትዮጵያን ነጻነት የሚነፍግ ሆኖ በመገኘቱ፣ ከጣልያን ጋር ጦርነት የማይቀር መሆኑን የተረዱት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አስፈላጊ ዝግጅታቸውን ጨርሰው የክተት ዐዋጁን በይፋ 1888 ጥቅምት ወር ላይ ካወጁ በኋላ ዘመቻ እንደተጀመረ ታሪክ ይገልጻል፡፡

የክተት ጥሪው የታወጀው፣ የትጥቅና የስንቅ ዝግጅት የተደረገውም በአዲስ አበባ እንጦጦ ተራራ ላይ በሚገኘው የቀድሞው የንጉሡ ቤተ-መንግሥት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እቴጌ ጣይቱ የውጫሌን ውል እንደማይቀበሉ የተናገሩትም በእዚሁ ቤተ-መንግሥት ሆነው ሲሆን፣ ስንቅና ትጥቅ ከተዘጋጀ በኋላ የመጀመሪያዎቹ የመሀል አገር አርበኞች በጥዋት ተሠባስበው ጦርነቱ ወደሚካሄድበት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ጉዞ የጀመሩትም ከዚሁ ቤተ-መንግሥት እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡
በዘመቻው ወቅት ንጉሠ ነገሥቱና አርበኞች ከተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በተጨማሪም ሌሎች ነገሮችን ወደ ቦታው ይዘው መሔዳቸው ይነገራል፡፡

ለአብነትም በዚሁ ቤተ-መንግሥት አጠገብ ካለችዋ የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውና በአንድ ወቅት በፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ተመርቆ የተከፈተው ሙዚዬም ቤት ውስጥ ያሉ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙትም፣ ንጉሠ ነገስቱና እና ንግሥቲቱ በአድዋ ዘመቻ ጊዜ ለታቦታቱ ማረፊያና ማስቀደሻ ያሠሩት ድንኳን(፣) በእጅ የተጠለፈ የአንድ ግድግዳ መጋረጃ ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ንጉሡ ወደ ዘመቻው ይዘውት ሔደው የነበረና ተመልሶ መጥቶ ሙዚዬም ቤቱ ውስጥ የሚገኝ ሥዕለ ማርያምም አለ፡፡

ዘመቻው ከተጀመረ ከወራት በኋላ በየካቲት 23/1888 የተካሄደውን ጦርነት በተመለከተ በጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ጽሑፍ ላይ እንዲሁ ሠፍሮ ይገኛል፡፡

‹‹ቀኑም ሲነገ የካቲት 23 ቀን የጊዮርጊስ በዓል ነበር፡፡ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ግድም የኢጣሊያ ጦር በድንገት ደረሰ፡፡ 500 ከሚሆኑት በር ከሚጠብቁት ከራስ መንገሻ(ዮሐንስ) ጦር ጋር ገጠመ፡፡ እነዚህም መልሰው ሲዋጉ ኹለት ባሻ ባዙቅ ማረኩና ቢጠይቋቸው ግማሹ ያጼ ምኒልክ ጦር ስንቅ ፍለጋ መሄዱን ስለሰሙ ኢጣሊያኖች በድንገት አደጋ ጥለው ለመዋጋት አራት ዤኔራሎች በአባ ገሪማ በኩል፣ አንደኛው ዤኔራል በማርያም ሼዊቶ በኩል ተሰልፈው ይጓዛሉ ብለው ተናገሩ፡፡ ይኸን ሲሰሙ ከቃፊር ጠባቂዎች አንዱ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ሰፈር እየሮጠ ሲሄድ በመንገድ ቀኛዝማች ታፈሰን አገኘና የያዘውን ወሬ ነገረው፡፡

… ዐጼ ምኒልክም ኢጣሊያኖች ተሰልፈው በጣም ተጠግተው ጦርነቱን ካልዠመሩ በቀር ጦሬን አሰልፌ ኹለተኛ አልወጣም ብለው ስለነበር በከንቱ አሰልፎ ሊያሶጣኝ ሳይሆን ሊዋጋ የመጣ መሆኑን ታምናለህን ብለው ታፈሰን ቢጠይቁት ዛሬስ እርግጥ ነው ብሎ መለሰ፡፡
… እቴጌይቱ በዚህ ቀን የሴትነት ባህሪያቸውን ትተው እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው ወደ ጦርነት ገቡ፡፡ መድፈኞቻቸውም ከቀኛቸው በኩል ጠምደው እየተኮሱ በመካከል የሚዋጋውን የጠላት ጦር ይመቱት ጀመር፡፡
… አቡነ ማቴዎስ የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ ድሉ ተፈጸመ፡፡
የኢትዮጵያም ጦር ከጦርነቱ የሸሸውን የኢጣልያን ጦር የራቀውን በጥይት የቀረበውን በጦርና በጎራዴ እየመታ ፈጀው፡፡››

ጸሐፌ ትዕዛዝ እንደገለጹትም፣ በዕለቱ የሰሌን ቆባቸውን የደፉ ብዙ መነኮሳትም አብረው አርበኞችን ሲያበረቱና ሲያዋጉ ውለዋል፡፡ እቴጌይቱም እንዲሁ ያመነታ ወታደር ሲያዩ ‹‹በርታ! ምን ሆነሀል! ድሉ የእኛ ነው!›› በማለት ያጀግኑት እንደነበር፣ ወታደሩም ኹሉ‹‹ጮማ ላበላኝ ጠጅ ላጠጣኝ ለጌታዬ ለምኒልክ እሞታለሁ›› እያለ ጀብድ ሲፈጽም መዋሉን ጸሐፌ ትዕዛዝ በጹሑፋቸው አስቀምጠዋል፡፡

የጦርነቱን ፍጻሜ ሲገልጹም፣ ‹‹ ዐጼ ምኒልክ ወደ ሠፈር ሲገቡ ጨልሞ ነበር፡፡ ወታደሮቹም ቁስለኛውን በከብት የሞተውን ሬሳ በቃሬዛ አድርገው ወደ ሠፈር መግባት ጀመሩ፡፡ በግራ በኩል ያለው የኢጣልያን ጦር ገና ስላልተሸነፈ በዚያ በኩል ያሉት ጦረኞች እስከ ሌሊቱ አምስት ስድስት ሰዓት ድረስ ሲገድሉ፣ ሲማርኩ ቆይተው በኋላ ተመለሱ›› ይላሉ፡፡

መጨረሻ ላይ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በዚያ በኋላ ጣልያኖች በጥቁር ተሸነፍን የሚለው ስለሚያሳቅቃቸው የተለያዩ ምክንያቶችን ሲያቀርቡ መኖራቸው ይገለጻል፡፡

እንዲሁም፣ የካቲት 23/1988 ከንጋት ጀምሮ እስከ ዕኩለ ሌሊት በተደረገው ተኩስ ብዙ በውል ያልታወቁ እና በተለያዩ ጸሐፍት ቁጥራቸው ከ4 ሺሕ እስከ 7 ሺሕ የሚደርሱ አርበኞች እንደሞቱ እና 10 ሺሕ የሚደርሱ እንደቆሰሉ በታሪክ ተጽፎ ይገኛል፡፡
እነ ፊታውራሪ ገበየሁን የመሳሰሉ ጀግኖችና ሌሎችም በማለቃቸው በተገኘው ድል ከመኩራት ይልቅ ሐዘን ሆኖ እንደነበርም ይነገራል፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝም ይህን ሲገልጹ ‹‹ ከሰልፍ ላይ ስለቀሩት እጅግ አጥብቆ ሀዘን ሆነ›› ይሉና ስለ ንግሥቲቱ ሐዘን ሲናገሩም ‹‹ብርሃን የመሰለ ፊታቸው አጥላስ (ጥላት) እስኪመስል አለቀሱ›› በማለት አስፍረዋል፡፡

ሆኖም ይህ ኹሉ የደረሰው ዕልቂት ለአገር ነጻነት የተከፈለ ዋጋ በመሆኑ ሐዘኑን ቀለል የሚያደርግ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝም ‹‹እንደ ተኩሱ ብዛት፣ እንደ ቀኑ እርዝመት ሰው ሞተ ብሎ ያዘነ የለም፡፡ ባሏም፣ ልጅዋም፣ ወንድሟም የሞተው እንኳን አልጋው ቆመልን ነው እንጂ፣ ባሌ ልጄ ወንድሜ ሞቱብኝ ብሎ ያዘነ የለም›› በማለት የዘመኑ አርበኞች የደረሰውን ጉዳት ከአገራቸው ነጻነት አንጻር እንዴት ቀለል አድርገው እንደገለጹት አሳይተዋል፡፡

አጼ ምኒልክ እና የአድዋ ድል
አንድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል የነበሩ ሰው ከአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሚከተለውን ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ‹‹በአንድ ወቅት አሜሪካን አገር የሚገኝ የጦር ትምህርት ቤት ውስጥ ልማር ገብቼ ነበር፡፡ ክፍል ውስጥ ገብተን ቁጨ እንዳልን አስተማሪያችን መጡና የዕለቱን ትምህርት ጀመሩ፡፡ ከዚያም የምኒልክን ፎቶ ስክሪን ላይ አወጡና የአድዋ ጦርነት ጊዜ ያወጁትን የክተት አዋጅ በተለያዩ ዕይታ በመተንተን ያስተምሩን ጀመር›› በማለት ነጮች የአጼ ምኒልክን የጦር ስልት በጦር ትምህርታቸው ላይ አካተው ወታደራዊ ሳይንሳቸውን ለማጠናከር እንደሚጠቀሙበት አውስተዋል፡፡

ይህም የንጉሡን የላቀ ጥበብ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ አሜሪካኖች እንደተረዱት እና የበለጠም እንደተጠቀሙበት ከማሳየቱ ባሻገር፣ የአድዋ ድል እንደ አገር በደንብ እንዳልተሠራበት የሚያሳይ ትልቅ ጥቆማ አለው፡፡

የአድዋ ጦርነት በአጼ ቴዎድሮስ፣ በአጼ ዮሐንስ ወይም ደግሞ በአጼ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ዘመን ጊዜ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ አሸናፊ ትሆን ነበር ወይ የሚል ክርክርም ይነሳል፡፡ በዚህም እነዚህ ነገሥታት የኢትዮጵያን ሕዝብ የማስተባበር አቅምና ሌሎች የጦርነት ቅድመ ኹኔታዎችን የማስተዋል ብቃት የአጼ ምኒልክን ያህል አላቸው ወይ ለማለት አያስደፍርም የሚሉ አሉ፡፡

እንዲሁም የንጉሠ ነገሠቱ ሚስት ሳይቀር የነበራቸው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አልነበረምና ከላይ ለተጠቀሱት ሦስቱ ነገሥታት የንግሥት ጣይቱን ዓይነት በፖለቲካ ዕሳቤ የበሰሉ ሚስቶች ያልነበራቸው በመሆኑ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱትም ሞልተዋል፡፡ ይህም የሕዝብን አቅም ከመዘንጋት እና ንጉሡን ከማግነን የመነጨ ሳይሆን ጦርነት ኹሌም በጥበብ የተሞላ መሪ የሚፈልግ በመሆኑ ነው፡፡

‹‹ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጸሐፋቸው ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ይህን ሐሳብ ሲያጠናክሩም፣ ንጉሡ የክርስትያን ደም በከንቱ አይፍሰስ፤ ጦርነት አይበጀንም እያሉ ጣሊያንን ያዘናጉ ነበር ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እውነት ግን የክርስትያን ደም በከንቱ እንዳይፈስ ፈልገው ሳይሆን በቂ የጦር መሣሪያ እስከሚያከማቹ፣ ከራሷ ከጣሊያን የነበረባቸውን አንድ ሚሊዮን የማሪያ ትሬዛ ብድር እስከሚከፍሉና በደቡብ ያለውን ግዛታቸውን እስከሚያስፋፉ በተለይም አስቸግሮ የነበረውን የወላይታን ገዥ ጦናን ልክ እስከሚያስገቡ ነበር ይላሉ ተክለ ጻድቅ በሐተታቸው፡፡

ይህ ኹሉ የንጉሠ ነገሥቱን የላቀ የመሪነት ብቃት እና ለአገራቸው ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ የአድዋ ድል በሚታሠብበት ዘመን ኹሉ ዳግማዊ አጼ ምኒልክን አለማንሳት እንደማይቻል ማሳያ ነው፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here